ኮሮናቫይረስ፡ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ የኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር በ50 በመቶ ጨመረ

ዉሃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከወራት በፊት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ቀደም ሲል በበሽታው ሞተውብኛል ያለቻቸው ሰዎች አሃዝ ላይ 1290 በመጨመር በ50 በመቶ ከፍ አደረገች።

የከተማዋ ባለስልጣናት እንዳሉት ይህ አሃዝ ሊጨምር የቻለው አዲስ በተገኙ ቁጥሮችና ከሆስፒታል ውጪ የሞቱ ሰዎችን በማካተቱ ነው።

ቻይና በአገሯ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያደረሰውን ጉዳት ሸፋፍናለች በማለት የተለያዩ ወገኖች ቢከሷትም በበሽታው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንዳልደበቀች በተደጋጋሚ እየተናገርች ነው።

አስራ ሚሊዮን የሚደርስ ነዋሪ ያለት ዉሃን ከተማ ወረርሽኙ ከተከሰተባት በኋላ ለሦስት ወራት ያህል ዝግ ሆና አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መግባትና መውጣት ተከልክሎባት ቆይታ ነበረ።

ከተማዋ የምትገኝበት የማዕከላዊ ቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ባወጣው አዲስ አሃዝ መሰረት በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,869 የደረሰ ሲሆን ይህም በመላዋ ቻይና የሟቾቹን አጠቃላይ መጠን ወደ 4,600 ከፍ አድርጎታል።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ መሰረት ቻይና ውስጥ 84 ሺህ የሚጠጉ የበሽታው ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን በዚህም በዓለም ሰባተኛዋ አገር ሆናለች።

ወረርሽኙ የቻይናን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ የጎዳው ሲሆን በዚህ በአስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ ማሽቆልቆሉ ተነግሯል።

ዛሬ አርብ የዉሃን ከተማ ባለስልጣናት ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት በበሽታው በሞቱ ሰዎች አሃዝ ላይ የተደረገው ክለሳ የቀብር አስፈጻሚዎችና እስር ቤቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች በመካተቱ ነው ብሏል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በቁጥሩ ውስጥ ያልተካተቱት ከሆስፒታሎች ውጪ በቤታቸው ውስጥ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸው የቁጥር ለውጡን እንዳስከተለ ተነግሯል።

ኮሮና
Banner