አሜሪካ በኮሮና ቫይረሰ በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በኮሮና ቫይረሰ በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚ ሆናለች። እስከ ቅርብ ድረስ ጣልያን ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የነበረባት አገር ነበረች።
ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር ሃያ ሺን አልፏል።
በአንድ ቀንም ውስጥ እስካሁን ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በቫይረሱ የሁለት ሺ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።
የኒውዮርክ አስተዳዳሪ አንድሪው ኩሞ በትናንትናው ዕለት የሟቾች ቁጥር መረጋጋትን አሳይቷል ብለው ነበር።
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ 783 ሰዎች መሞታቸውን ካሳወቁ በኋላ አስተዳዳሪው በባለፉት ቀናት ተመሳሳይ ቁጥር በመመዝገቡ ነበር ሁኔታዎች ተረጋግተዋል ለማለት ያበቃቸው።
"በጣም ከፍተኛ ቁጥር አይደለም። የሟቾች ቁጥር ተመሳሳይ ቢሆንም የሚያስደነግጥ ነው" ያሉት አንድሪው "ይህ ቁጥር የሚያሳየን ምን ያህል ሰዎችን ህይወት እንደተነጠቅንና ይህም ያስከተለውን ህመም ነው" ብለዋል።
ከአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ኒውዮርክ የወረርሽኙ ማዕከል ስትሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው 530 ሺ ህዝብ መካከል 180 ሺዎቹ የሚገኙት በኒውዮርክ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ እያንዳንዷ የአሜሪካ ግዛት አደጋንና ቀውስን የመከላከል አዋጅን አስተላልፈዋል።
በትናንትናው ዕለት በእንግሊዝ 917 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎችንም ቁጥር 9ሺ875 አድርሶታል።
የስፔን የጤና ሚኒስቴር 510 ሰዎች መሞታቸውን ያሳወቀ ሲሆን፤ በሶስት ሳምንት ውስጥ ከተመዘገቡት ትንሹ ቁጥር ነው ተብሏል።
በፈረንሳይና በጣልያን የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በፅኑ ህሙማን ክፍል ያሉ በሽተኞች ቁጥር መቀነስን እንዳሳየ ተነግሯል።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የቤት ውስጥ መቆየት ውሳኔን የማስረዘም እቅድ እንዳላቸው ተዘግቧል።
ወረርሽኙ በቻይናዋ ውሃን ታህሳስ ወር ላይ ተነሳ ከተባለ ጀምሮ ከመቶ ሺ ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል፣ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል እንዲሁም ከ400 ሺ ሰዎች በላይም አገግመዋል።














