አዲስ አበባ ውስጥ ፖሊስ የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን ያዘ

ታትሟል

አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤት የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን ደብቀው የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ከግለሰቦቹ ላይ የያዛቸው የጦር መሳሪያዎች መትረየስና ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች መሆናቸውን ገልጾ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችም መያዛቸውንም አመልክቷል።

ፖሊስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሳጥን ተራ ተብሎ በሚታወቅው አካባቢ በሚገኝ የአሮጌ ጫማ ማደሻ ቤት ላይ ባደረገው ክትትልና ከፍርድ ቤት የመፈተሻ ትዕዛዝ በማውጣት ባካሄደው ብርበራ ነው የጦር መሳሪያዎቹን ያዝኩ ያለው።

በዚህም መሰረት ከተጠቀሰው ቤት ውስጥ ሰባት ክላሽንኮቭ እና አንድ መትረየስ ጠመንጃ ማግኘቱን አመልክቶ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ ገልፀዋል።

ፖሊስ የጦር መሳሪያዎቹ ከየት እንደመጡና ለምን ተግባር ሊውል እንደ ነበር ለማወቅ ምርመራውን እያደረገ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው በጊዜ ቀጠሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸው ተገልጿል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሊዘዋወሩ የነበሩ ጦር መሳሪያዎች በኅብረተሰቡ ጥቆማ መያዝ እንደተቻለ ኃላፊው ጨምረው አስታውሰዋል።