በአዲስ አበባ ወታደራዊና የፖሊስ የደንብ ልብሶችን በግለሰብ መጋዘን ውስጥ ተከማችተው ተያዙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የተለያዩ ወታደራዊና የፖሊስ የደንብ ልብሶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎችን በአንድ መጋዘን ውስጥ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ፖሊስ እንዳለው የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ክልል ፖሊሶችን የደንብ ልብስ እንዲሁም የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በመጋዘን ውስጥ ተከማችተው ማግኘቱን ገልጿል።

በተጨማሪም አንድ ቦንብ፣ አንድ ሽጉጥና ከ250 በላይ ጥይቶች አብሮ መያዙን አመልክቶ እነዚህን ወታደራዊ አልባሳትና መሳሪያዎች "አከማችተው" አገኘኋቸው ያለቸውን አምስት ተጠርጣሪዎችንም ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ከበደ አስፋ እንዳብራሩት እፎይታ የገበያ ማዕከል አካባቢ የሚገኝን መጋዘንን የተከራዩ አንዲት ግለሰብ ከወታደራዊና የፖሊስ አልባሳቱ አርማዎች፣ ቀበቶዎች፣ መለዮችን፣ ጫማዎችን፣ ካቴናዎች እንዲሁም ወታደራዊ የውሃ መያዥ ኮዳዎችን አከማችተው መገኘቱን ገልጸዋል።

ኃላፊው በተጨማሪም መጋዘኑን የተከራዩት ግለሰብ ቦታውን ለጫማ ማስቀመጫነት በሚል መሆኑን በምርመራ መረጋገጡን አመልከተው እንዲህ አይነቱን ድርጊት ለመቆጣጠር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የወታደርና ፖሊስ የደንብ አላባሳትን እንዲሁም ቁሳቁሶችን ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ ይዞ መገኘት፣ ማከፋፈልና መሸጥ በሕግ የተከለከለ መሆኑን በመጥቀስ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የሚደረገው ምርመራ መቀጠሉን ተናግረዋል።