ስልጣንን ርስት የማድረግ አባዜ መሪዎችን የሚፀናወተው ለምንድን ነው?

ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለተጨማሪ የሁለት የስልጣን ዘመን እንዲቆዩ የአገሪቱ ህገ መንግሥት ላይ የሚደረገውን ማሻሻያ እንደሚደግፉ ተናግረዋል። አሁን ባለበት ሁኔታ ግን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ይህን የሚፈቅድ አይደለም።

ፑቲን ከአልጄሪያ እስከ ዚምባብዌ ስልጣን የሙጥኝ ካሉ መሪዎች መካከል ናቸው። ሕግ ቀይሮና ጥሶም ጭምር ስልጣንን ርስት የማድረግ አባዜ መሪዎችን የሚፀናወታቸው ለምንድን ነው?

ገንዘብ?

'ምርጫ እንዴት ይጭበረበራል' የሚል መጽሐፍ የፃፉት ፕሮፌሰር ኒክ ቺዝማን መሪዎች ለምን ስልጣን የሙጥኝ ይላሉ? ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ "ቀላሉ መልስ ሙስና ነው። በጣም ገንዘብ ያገኛሉ ስለዚህ ሃብታም ሆኖ ለመቆየት ስልጣን ላይ ይቆያሉ" ይላሉ። ቢሆንም ግን ሌሎች ውስብስብ ነገሮችም እንዳሉ ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት መሪዎች ከስልጣን ሲወርዱ ከገንዘብ ማጣት ይበልጥ መከሰስን ይፈራሉ፤ ይህ ፍርሃታቸው ደግሞ ተገቢ ነው።

በመጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1960 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ከስልጣን የወረዱ 43 በመቶ የአፍሪካ መሪዎች ተከሰዋል፣ ተሰደዋል ወይም ተገድለዋል። ይህ የመሪዎቹ ትልቅ ስጋት ሲሆን ስጋታቸው ግን ይህ ብቻም አይደለም።

የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአጋሮች ምክር

መሪዎች ስልጣን እንዳይለቁ የቤተሰብ፣ የፖለቲካ አጋሮች ፣ ወደ ስልጣን እንዲወጡ የደገፋቸው ፖሊስና ወታደር ጫና ሁሉ አለባቸው። "ስልጣን መልቀቂያ ጊዜዬ ነው ብትል እንኳ በርካቶች በርህን እያንኳኩ ስልጣን ላይ መቆየትህ ያንተ ጉዳይ ሳይሆን ላንተ መስዋእትነት የከፈሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሆነ ይነግሩሃል"

የቀድሞ የዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ስልጣን የሙጥኝ እንዲሉ በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ተፅእኖ ከባድ እንደነበር ያመለክታሉ ፕሮፌሰሩ።

ሮበርት ሙጋቤ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ነገር ግን ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በላይም ስልጣን በመሪዎች አስተሳሰብ ላይ የሚያሳድረው ሌላ ነገር እንዳለ ይናገራሉ።

ዶ/ር ዳቸር ኬልትነር 'የስልጣን ተቃርኖ' በሚለው መፅሃፋቸው ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ብለዋል። እሳቸው ተቃርኖ የሚሉት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ስልጣን የሚወጡ ሰዎች በባህሪያቸው ተግባቢና ተወዳጅ መሆናቸውን ነው።

በቴኒስ ቡድንም ይሁን በኩባንያ ደረጃ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን አመኔታ ያገኛሉ።

በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ሰዎች ስልጣን ሲያገኙ፤ ለአጭር ጊዜ እንኳ ቢሆን ባህሪያቸው ይቀየራል ይላሉ ዶ/ር ከልትነር። ራሳቸውን ተጠቃሚ በሚያደርግ ነገር ብቻ ይጠመዳሉ፣ ሌሎች አዘኔታን ያጣሉ ፤ ሁሌም እኔ ትክክል ነኝ የሚል እምነትም ያሳድራሉ።

ዶ/ር ከልትነር እንደሚሉት እነዚህ ሰዎች ከዚህም አልፎ ስርዓት የለሽ፣ ቁጡ፣ የሌሎች ሰዎችን ንግግር የሚያቋርጡ ፣ የሚናገሩ ሰዎችን አይን ማየት እንኳ የማይፈልጉ ይሆናሉ።

ጥሩ ስሜት

በዚህ ርእሰ ጉዳይ የተሰሩ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ስልጣን ሲያገኙ ምንም ነገር ለማድረግ የሚቆጠቡ አይሆኑም። ከድሃ ህፃናት ይልቅ የሃብታም ህፃናት ልጆች ሱፐርማርኬት ውስጥ እቃ ለመስረቅም ሆነ ያልተለመዱ ፆታዊ ግንኙነቶች ለማድረግ የቀረቡ ናቸው።

የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዎሪ ሙሴቬኒ

የፎቶው ባለመብት, Jack Taylor

አጥኚዎች እንደሚሉት ስልጣን ሱስም ይሆናል፤ ምክንያቱም ስልጣን ካለ ያለገደብ የፈለጉትን በማድረግ ራሳቸውን ማስደሰትን የዘወትር ተግባር የማድረግ ነፃነት አለ። ይህ ደግሞ አእምሯቸውን በሃሴት ይሞላል።

"ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በጣም ደስታ ይሰማቸዋል። በብዙዎች መደነቅ ፤ ትልቅ ክብርና ሞገስ እንደተሰጣቸውም ይሰማቸዋል" የሚሉት ዶ/ር ከልትነር እነዚህ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የነርቭ ስርዓታቸው የተረጋጋና ጤናቸውም የጎለበተ ነው ሲሉ ያክላሉ። በአጠቃላይ ስለ ህይወት የሚሰማቸው ነገር ጥሩ ነው ይላሉ።

ወፈፌነት

ዶ/ር ከልትነር እንደሚሉት ስልጣን ያላቸው ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሆነ የአእምሮ ክፍሉ የተጎዳ ሰው የሚያሳየው ባህሪያት የሚስተዋልባቸው ስሜታዊ ናቸው።

የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌግዛንደር ሉካሼንኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከዚህ ጋር በያያዘ የገጠማቸው የተለየ ነገር እንዳለም "የአእምሮ ጉዳት ያለበት አንድ ሰው ነበረኝ። አንድ ቀን 'እንዴት ነህ? ከትራምፕ የተሻለ ስርዓት ያለኝ ሰው ነኝ' ብሎ ፅፎልኝ ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ።

በሽተኛቸው ያለው ነገር ትርጉም የሚሰጥ እንደሆነ ያምናሉ። መሪዎች እብሪተኛ ሊሆኑ፤ መምራት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ብለው ሊያስቡም ይችላሉ። በዚህ ደግሞ ለአገር የሚበጀውን ነገር ጨርሶ ማየት ላይችሉ ይችላሉ።

እንዲህ ያሉ መሪዎች ሁሌም እነሱን 'እሺ፣ አቤት፣ ወዴት' የሚሉ ሰዎችን ብቻም ይሾማሉ፤ ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎችን ደግሞ ከስልጣን ያወርዳሉ።

ስልጣን ማጣት የሚያስከትለው ከፍተኛ የስነልቦና ጫናም አለ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በተለይም ትልልቅ ወንዶች ስልጣኔን ላጣ ነው ብለው ሲያስቡ ሌላውን ወደ ማጥፋት ይገባሉ።

ስልጣን መሪዎችን የሚያበላሽ ከሆነ ሁሉም ለምን ሙሰኛና ነፍሰ ገዳይ አልሆኑም? በፖላንድ ዋርሶ የስነልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት አሌግዛንድራ ኪሳልክ የስልጣን መገለጫ የሆኑ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን አስቀምጠዋል።

ስልጣን ለጠንካራ ሰዎች የሌሎችንም ሆነ የራሳቸውን ህይወት የመቆጣጠር ስልጣን ይሰጣቸዋል ይላሉ። የሰዎች የራሳቸውን ህይወት መቆጣጠር መቻል ደግሞ በአዎንታዊነት የሚታይ ነው እንደ ዶክተሯ ገለፃ።

ችግር የሚፈጠረው እነዚህ ሰዎች ተቆጣጥረነዋል ያሉትና የሚመሩት አገር ችግር ውስጥ ሲገባ ነው። "ስልጣን ጥሩና ለጥሩ ነገር መዋል የሚችል ነው፤ ግን ስልጣኑ የተገኘበትን ዋጋ መገንዘብ ያስፈልጋል" ይላሉ።

መሪዎች ይህን በሚገባ ቢገነዘቡ ነገሮች ጥሩ ይሆናሉ ሲሉ ይደመድማሉ።