የኬንያው የደኅንነት ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር መከሩ

የፎቶው ባለመብት, @FredMatiangi
በአገራቸውና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት በተመለከተ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አዲስ አበባ ላይ መወያየታቸውን የኬንያው የደኅንነት ሚኒስትር ተናገሩ።
ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር ድንበር የምትጋራው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውንና ከእስላማዊው ቡድን አል ሻባብ ጋር የሚፋለመውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ለመደገፍ ተሰማርቶ ለሚገኘው የአፍሪካ ኅብርት ሠራዊት አዋጥታለች።
የደኅንነት ሚኒስትሩ ፍሬድ ማትያንጊ "በድንበር አካባቢ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ የቀጠናውን መረጋጋት ለማጠንከር በአገራቱ መካከል የትብብር መንገድ ለመፈለግ ያቀደ ውይይት" መሆኑን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፈረዋል።
ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ያደረጉት ውይይት የተካሄደው የሶማሊያ ኃይሎች ከፊል እራስ ገዝ ከሆነችው የሶማሊያዋ ጁባላንድ ግዛት ከመጡ ኃይሎች ጋር በኬንያ ግዛት ውስጥ ከማንዴራ አቅራቢያ ባለ ቦታ ላይ ከተጋጩ ከሳምንት በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የኬንያው የደኅንነት ሚኒስትር ፍሬድ ማትያጊ ወደ ሶማሊያ አቅንተው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ፋርማጆ ሞሐመድ ጋር በመገናኘት የድንበር አካባቢ ጸጥታን ለማጠመናከር ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን አድርገዋል።
ቀደም ሲልም ሶማሊያ ኬንያን በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው በማለት የከሰሰች ሲሆን ጨምራም በድንበር አካባቢም ያለውን መስፋፋት እንድታቆም አስጠንቅቃ ነበር።
በሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ባላቸው የጋራ የውሃ ድንበር ይገባኛል ውዝግብ ምክንያት ከሻከረ ቆየት ብሏል። ይህም የባሕር ድንበር ይገባኛል ውዝግብ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በመጪው ሰኔ ወር ላይ ይሰማል።








