አውስትራሊያ በሰደድ እሳት ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

የአውስትራሊያ ሰደድ እሳት

የፎቶው ባለመብት, MARTIN OLLMAN

የምስሉ መግለጫ, የአውስትራሊያ ሰደድ እሳት
ታትሟል

አውስትራሊያ በገጠማት የሰደድ እሳት ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች።

አውስትራሊያ ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በተነሳ ሰደድ እሳት እየተቃጠለች ቆይታለች። ከካንቤራ ከተማ በስተ ደቡብ አቅጣጫ እየገሰገሰ የሚገኘው የሰደድ እሳት ደግሞ ሰሞኑን የአውስትራሊያ ባለስልጣናትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነግጉ አስገድዷቸዋል።

ባለስልጣናቱ እንደሚሉት አሁን በአካባቢው ያጋጠመው ሰደድ እሳት ምናልባትም ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ አስከፊው ነው።

እስካሁን ባለው ሁኔታም ይሄው አስከፊ ሰደድ እሳት በደቡብ ካንቤራ በኩል 18 ሺህ 5 መቶ ሄክታር ያክል አካባቢ መሬት አውድሟል።

በካንቤራ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎችም በማንኛውም ጊዜ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንዲወጡ ሊደረግ ስለሚችል ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል።

"አካባቢው በ2003 እ.አ.አ ከገጠመው የእሳት አደጋ ወዲህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመው አስከፊ ሰደድ እሳት ነው" በማለት አንድሪው ባር የተባሉ ከፍተኛ ሹም ተናግረዋል።

"በአካባቢውም ከዚህ ሰደድ እሳት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው አሳሳቢ ጉዳይ የለም" በማለት ሹሙ አክለዋል።

በሲድኒ እና ሜልበርን መካከል የምትገኘው ሰደድ እሳቱ ያስጨነቃት አነስተኛ ግዛት 4 መቶ ሺህ አካባቢ ሰዎች ይኖሩባታል።

በ2003 እ.አ.አ በካንቤራ የተከሰተው ሰደድ እሳት 4 ሰዎችን ገድሏል። ሌሎች 500 የሚሆኑ ሰዎች ተጎድተው የነበረ ሲሆን ከ470 በላይ ቤቶች በሰደድ እሳቱ ነደዋል።

ባለስልጣናት እንደሚሉት ታዲያ ባለፈው አርብ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ተከስቶ ከነበረውን የአየር ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል የአየር ጠባይ ተከስቷል።

ሰደድ እሳቱ ምናልባትም የሙቀት መጠኑ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከደረሰ በኋላ በከባድ ነፋስ እየተቀጣጠለ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ሚስተር ባር አስጠንቅቀዋል።

በመሆኑም የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካንቤራ አደጋ እስካንዣበባባት ድረስ ይቀጥላል ብለዋል ባለስልጣኑ።

እሳቱ ለሳምንታት ወደ ከተማዋ እየገሰገሰ ነው የሚገኘቀው። የዛሬ ሳምንት ሃሙስ ሰደድ እሳቱ ስጋት በመፍጠሩ የካንቤራ አውሮፕላን ማረፊያ ተዘግቶ ነበር።

የአውስትራሊያ ሰደድ እሳት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአውስትራሊያ ሰደድ እሳት

በዚያው ቀን ሦስት የአሜሪካ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱ ባለበት ቀጠና በበረዷማው ተራራ አካባቢ ሄሊኮፕተራቸው ተከስክሳ ሞተዋል።

ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ የሰደድ አሳቱ ነጸብራቅ ሰማዩን ወደ ቀይ እንደቀየረው የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲጋራ ሰነባብቷል።

በዚህም ምክንያት ጎብኝዎች ፎቶ ለማንሳት ወደ ሰደድ እሳቱ መጠጋታቸው ባለስልጣናቱ ገደብ እንዲያስቀምጡ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በአውስትራሊያ በተነሳው ሰደድ እሳት ቢያንስ 33 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን ከ11 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰደድ እሳቱ ወድሟል።የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር የአውስትራሊያ ጦር ጥሪ ቀረበለት