የበር መጥሪያ ደወል ኩባንያ ለፌስቡክና ለጉግል መረጃ አሳልፎ እየሰጠ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Amazon Ring
የበር መጥሪያ ደወል ኩባንያ የደንበኞቹን መረጃ አሳልፎ ፌስቡክና ጉግልን ለመሳሰሉ ድርጅቶች አሳልፎ እየሰጠ እንደሆነ አንድ ምርመራ አጋልጧል።
የራሱ አፕሊኬሽን (መተግበሪያ) ያለው 'ሪንግ አፕ' የተሰኘው የበር መጥሪያ ደወል መከታተያ እንዲሁም የደንበኞችን ግላዊ መረጃዎችን መላክ እንዲያስችሉ አድርገው እንደተሰሩ ኤሌክትሮኒክ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን የተሰኘው ድርጅት በሪፖርቱ አመልክቷል።
መረጃው እንደሚያሳየው አምስት ኩባንያዎች የተለያዩ መረጃዎችን ለምሳሌም ያህል የደንበኞችን ስም፣ ደንበኞች ስልካቸውን የሚጠቀሙበትን አድራሻና የሞባይል ኔትወርክን የመሳሰሉ አግኝተዋል ተብሏል።
ኩባንያው ሪንግ በበኩሉ አሳልፎ የሰጠው መረጃ የተወሰነ እንደሆነ ነው።
ኩባንያው ጊዝሞዶ ለተባለው የእንግሊዝ ሚዲያ እንደተናገረው "እንደ ማንኛውም ኩባንያ ሪንግ የሞባይል መተግበሪያውን ለመፈተሽ በዚያውም ያሉትን አገልግሎቶች ለማሻሻል፣ እንዲሁም ደንበኞች በአገልግሎታችን ምን ያህል ረክተዋል የሚለውን ለማየት የሦስተኛ ወገን አገልግሎትን እንጠቀማለን።"
ኩባንያው ይህንን ይበል እንጂ ፋውንዴሽኑ በበኩሉ የደንበኞችን ግላዊ መረጃ መጠበቅ እንደተሳነውና በተለይም ከክትትል ጋር ተይይዞ ኩባንያው ለማንም የማያጋራው መረጃ እንደሆነ ቢገልፅም የተባለው ተግባራዊ አልሆነም ብሏል።
ይህንን መረጃ በማጋራት ደንበኞች በማንኛውም ወቅት የጣት አሻራቸውን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በሚጠቀሙበት ወቅት የትኛውንም እንቅስቃሴያቸውን ለመሰለል አስችሏል ተብሏል።
ኩባንያው የደንበኞችን መረጃን ያቀበለው ለፌስ ቡክ፣ ብራንች፣ አፕስ ፍላየር፣ ሚክስ ፖናልና ጉግል የመረጃ ኩባንያዎች ነው።
የፋውንዴሽኑ ምርመራ እንደሚያሳየው ሪንግ ኩባንያ መረጃዎችን አሳልፎ የሰጠው አንድሮይድ ሶፍትዌሮችን ለሚቀብሉ ስልኮች ነው።
ሪንግ የተባለው የበር መጥሪያ ደወልና ለቤት አገልግሎት የሚውሉ ካሜራዎችን እንዲሁም የደህንነት ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ ሲሆን ባለቤትነቱም የአማዞን ነው።
ኩባንያው ከዚህ ቀደምም ካሜራዎቹንና የደህንነት ቁሳቁሶቹን ለህግ አስከባሪ አካላት ለስለላ ተግባር አውሏል በሚል ተወንጅሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ጎረቤታሞች የስለላ ተግባር እንዲያከናውኑ በር ከፍቷል፤ እንዲሁም ካሜራዎቹም በተለያዩ አካላት እንደተጠለፉ መረጃዎችም በመውጣት ላይ ናቸው።












