ቦይንግ በቢሊዮን ለሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ተዳረገ

ታትሟል

ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ቀውስ ተከትሎ ኩባንያው በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ አይቶት የማያውቀውን ኪሳራ አስመዝግቧል።

ለብዙዎች ህይወት መቀጠፍ የሆነውን የኢትዮጵያና የኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች አደጋን ተከትሎ ከፍተኛ ሽያጭ ላይ የነበሩትን አውሮፕላኖቹን ከበረራ ውጪ ለማድረግም ተገዷል።

በሁለቱ አየር መንገድ አደጋዎችም 346 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በከፍተኛ ሽያጭ ላይ የነበሩትን አውሮፕላኖች ከገበያ ውጪ ማድረጉም 18 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብን እንዲያጣ እንዳደረገው የሚታሰብ ሲሆን፤ ይህም የኩባንያውን የገንዘብ አቅም ክፉኛ እየተፈታተነው ነው።

በዚህ ዓመት ብቻ ለ636 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከሃያ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ተዳርጓል።

የአውሮፕላኖች ሽያጭም በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንደሆነም እየተነገረ ነው። ባለፉት ሦስት ወራት ከሽያጭ 17.9 ቢሊዮን ዶላር ቢያገኝም በንግዱ ዓለም ያሉ ተንታኞች ከገመቱት 21.7 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።

"ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅብን ተረድተናል" በማለትም አዲሱ የቦይንግ ተሿሚ ዴቪድ ካልሃን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ኩባንያው ባስተናገደው ቀውስ ምላሻቸው አጥጋቢ አልነበረም ተብለው የተነሱትን ዴኒስ ሙይልንበርግን በመተካት ነው የተሾሙት።

"በአሁኑ ወቅት ሙሉ ትኩረታችን 737 ማክስ ደህንንቱ በተጠበቀ መልኩ የሚመለስበትንና ቦይንግ በህዝቡ ዘንድ ያተረፈውን በጎ ስምም ለመመለስ ነው" ብለዋል ካልሃን።