ለትራምፕ "አፍሪካውያን ይወዱዎታል" ያሉት ቢሊየነር ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካዊው ቱጃር ፓትሪስ ሞትሴፔ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አፍሪካውያን ይወዱዎታል" በሚለው ንግግራቸው ውርጅብኝን ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ቢሊየነሩ ይህንን የማስተባበያ ይቅርታ እንዲጠይቁ የተገደዱትም "እርስዎን ለአፍሪካውያን ቃል አቀባይ ማን አደረገዎት?" የሚሉ ከፍተኛ ትችቶችን ተከትሎ ነው።
"እነዚህን የተለያዩ አስተያየቶች ሰምቼያለሁ፤ ለንግግሬም ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።
ባለሀብቱ በስዊዘርላንድ ከተማ ዳቮስ የዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ፎረም ወቅት እራት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው አድናቆታቸውን ያዥጎደጎዱላቸው።
"አፍሪካ አሜሪካን ትወዳለች፤ አፍሪካውያን ይወዱዎታል፤ አሜሪካ እንድትጠናከር እንፈልጋለን። እርስዎም እንዲበረታቱ እንፈልጋለን" በማለት ቱጃሩ ፍቅራቸውን ገልፀዋል።
ቱጃሩ በእራቱ ወቅት በፎርብስ መጽሔት ከትራምፕ ጋር በቢዝነሱ ዓለም ውስጥ የላቀ አእምሮ ተብለው መስፈራቸውን ጠቅሰው ከፕሬዚዳንቱ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታም አጋርተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው "ድንቅ ሥራ እየሠራህ ነው" ብለዋቸዋል።
ቪዲዮውም በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋርቷል።
የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚና ለጥቁሮች ነፃነት የሚታገለው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ የተሰኘው ፓርቲ ንግግራቸውን "ከራስ ወዳድነታቸውና ከአፍቅሮተ ንዋይ የመነጨ ነው" ብሎታል።
"የባለሀብቱ ንግግር ለጥቁር አሜሪካውያን ስድብ ነው፤ ምክንያቱም በሳቸው ዘረኝነት በቀጥታ የተጎዱ የማህበረሰቡ ክፍል በመሆናቸው" በማለት በወቅቱ ፓርቲው መግለጫ አውጥቶ ነበር።
ሞትሴፔ በበኩላቸው ይህ ንግግራቸው በትራምፕ አስተዳደርና በአፍሪካውያን የፖለቲካና የንግዱ መሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳለጥ ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።
"ደቡብ አፍሪካም ሆነ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት አመራሮች ፀረ- አሜሪካዊ የሆነ አስተሳሰብ አላቸው። በዚህም ምክንያት የውጭ ኢንቨስተሮችንም ሆነ የስራ ፈጠራም ለማምጣት አዳግቶናል" በማለት በመግለጫቸው አትተዋል።
ይህ ንግግራቸው ከፍተኛ የሆነ ሽንቆጣ እንዲያተርፉ አድርጓቸዋል፤ በዚህም ምክንያት "እኔ ማንም ወክዬ መናገር አልችልም፤ ራሴን ብቻ ነው መወከል የምችለው" ብለዋል።
የ57 አመቱ ቱጃር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ተፅእኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ከሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራሞፋሳም ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው ተዘግቧል።
በጎርጎሳውያኑ 2008 ፎርብስ በዓለም ቱጃሮች ዝርዝር ውስጥ ያካተታቸው ሲሆን የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ለመሆንም በቅተዋል።
አንጡራ ሃብታቸውም 2.4 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
በተለያየ ጊዜ ባደረጓቸው ንግግሮች "ዘረኛ" ናቸው ተብለው የሚጠሩት ትራምፕ የአፍሪካ ሃገራትን አፀያፊ ስድብ በመስደባቸው ከፍተኛ ውርጅብኝን ማስተናገዳቸው የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ትራምፕ ላደረጉት "አፀያፊና ዘረኛ ንግግር" ይቅርታ እንዲጠይቁ ብሏቸው ነበር።
ብዙዎችን ያስቆጣ ስድባቸውን ተከትሎም የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዎሪ ሙሴቪኒ " ትራምፕን እወደዋለሁ፤ አፍሪካውያንን በግልፅ ነው የሚነግረን" ማለታቸው ብዙዎችን አስደምሞ ነበር።
በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁት ትራምፕ የሰላም የኖቤል ሽልማቱ የሚገባኝ ለኔ ነው ማለታቸው ብዙዎችን ያስደነቀ ጉዳይ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል።












