የኢራን አውሮፕላን ተንሸራቶ የመኪና መንገድ ላይ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Twitter
አንድ የኢራን የመንገደኞች አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር ተንሸራትቶ ከማኮብኮቢያ አስፋልት ወጥቶ አውራ ጎዳና ላይ መታየቱ እያነጋገረ ነው።
ደግነቱ ከ135 ተሳፋሪዎቹ አንድም ሰው ክፉ አልነካውም። ይህ የሆነው በደቡብ ምዕራብ ኢራን መሻሂር በምትባል ከተማ ነው።
የካስፒያን አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከቴህራን ነበር የተነሳው። መሻሂር በምትባለው ከተማ ለማረፍ ሲሞክር ግን ጎማዎቹ ከሆድ እቃው ሙሉ በሙሉ መውጣት አልቻሉም። አደጋውም የተፈጠረው በዚህ ምክንያት ነው ተብሏል።
አውሮፕላኑ የመኪና አውራ ጎዳና ላይ ወጥቶ መንገደኞቹ ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ የሚያሳዩ ምሥሎች በማህበራዊ ድራ አምባ ላይ ሲታዩ ነበር የዋሉት።
የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን የአቪየሽን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ችግሩ የተፈጠረው አብራሪው ለማረፍ የሞከረው ከተመደበለት ሰዓት ዘግይቶ ነው። በዚህም ምክንያት ማኮብኮቢያውን ሊያገኘው አልቻለም።
አንድ በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበረ ጋዜጠኛ በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው የማክዶነል ደጋላስ ስሪት የሆነው አውሮፕላኑ የኋላ ጎማ በመሰበሩ አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲል አስፋልት ለአስፋልት ለመንፏቀቅ ተገዷል።
እንዳለመታደል ሆኖ ኢራን በርካታ የአውሮፕላን በረራ እክሎች የሚገጥሟት አገር ናት። በፈረንጆቹ 2019 የካቲት ወር ላይ 66 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ሞተውባታል። በ2011 እንዲሁ የኢራን አየር መንገድ ሌላ አደጋ ገጥሞት በርካቶች ሞተዋል።
ይህን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት 2 የኢራን አየር መንገዶች የአየር ክልሉን እንዳይጠቀሙ አግዷቸዋል።
ኢራን በስህተት የዩክሬን አውሮፕላንን በሮኬት መትታ የጣለቸውም በቅርቡ ነበር።












