ኢራናዊያን ''ውሸታም'' ያሉትን መንግስት በመቃወም አደባባይ ወጡ

ኢራናዊያን ተቃዋሚዎች
የምስሉ መግለጫ, ኢራናዊያን ተቃዋሚዎች
ታትሟል

የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን ኢራን በስህተት መትታ ብትጥለውም በወቅቱ የሰጠችው መረጃ ግን አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቴክኒክ ችግር መሆኑን የሚገልጽ ነበር። ነገር ግን የአሜሪካ ባለስልጣናት አውሮፕላኑ የተመታው በራሷ በኢራን ነው የሚል መረጃ ማውጣታቸውን ተከትሎ "አዎ ተሳስቼ የመታሁት እኔ ነኝ" የሚል ምላሽ ኢራን ሰጥታለች።

ይህ ያላስደሰታቸው ኢራናዊያን ታዲያ ባለስልጣናትን "ውሸታም" እያሉ በማውገዝ በመዲናዋ ቴህራን አደባባይ ወጥተዋል። 176 ተጓዦችን የያዘውን አውሮፕላን እንደመታችው ያመነችው ከ3 ቀናት በኋላ ነው።

ጉዳዩ ድርብ ድል የሆነላት አሜሪካ በኢራን መሪዎችና ዜጎች መካከል የተፈጠረው መወጋገዝ ደስታ ያጫረላት ትመስላለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው "አስደናቂ የተቃውሞ ሰልፍ" በማለት ለሰልፉ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

ረቡዕ ዕለት ወደ ዩክሬን ኬቭ ይጓዝ የነበረው PS752 የተሰኘው የመንገደኞች አውሮፕላን ተመትቶ የተከሰከሰው ኢራን የአሜሪካ የጦር መንደሮችን ደብድቤያለሁ ካለች ከሰዓታት በኋላ ነው።

ቢያንስ ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ እንደሆኑ የተነገረላቸው ተቃዋሚዎቹ የጀኔራል ሶሉማኒን ፎቶ በመያዝና ዋሽተዋል ያሏቸውን ባላስልጣኖቻቸውን በመርገም ነበር ተቃውሟቸውን የገለጹት።

መንገድ የዘጉ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ፖሊስ የአስለቃሽ ጭስ መጠቀሙንና ሰልፈኞቹም "ሞት ለውሸታሞች'' እያሉ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ሲዘዋወር ቆይቷል።

አንዱ ኢራናዊም "አስነዋሪ ድርጊቱን ፈጽመው ድጋሜ የሚዋሹ የአገሬን ሰዎች መቼም ይቅር አልላቸውም" ብሏል።

ተቃውሞውንና የኢራንን የዕምነት መግለጫ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትርምፕ በእንግሊዝኛና በፋርስ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት "ስቃይ ላይ ለሚገኙት ኢራናዊያን የፕሬዝዳንትነት ስልጣኔን ከተረከብኩበት ቀን ጀምሮ ከናንተው ጋር የቆምኩ መሆኔን እንድታውቁት፤ መንግሥቴም አብሯችሁ እንደሚቆም ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

"የምታደርጉትን የተቃውሞ ሰልፍ በቅርበት እየተከታተልነው ነው፤ ያላችሁ ተነሳሽነት የሚደንቅ ነው" በማለትም ሰልፉን አበረታትተዋል።

የካናዳው ፕሬዝዳንት ጀስቲን ትሩዱ "እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ግድያ እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ ግልጽ ምርመራ ሊኖር ይገባል" ብለዋል። ተጠያቂነትና ፍትህ ሰፍኖ እስከሚያዩ ድረስ እጅግ የተጎዱት ካናዳዊያን አይተኙም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ደግሞ "አሰቃቂ" ባሉት በዚህ የአውሮፕላን ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሁሉም ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።