''ኢራን የዩክሬኑን አውሮፕላን በስህተት ተኩሳ ጥላለች'' የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን

የተከሰከሰው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

176 ሰዎችን አሳፍሮ ሰጓዝ የነበረውና ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነው አውሮፕላን በስህተት ተኩሳ የጣለቸው ኢራን ነች ሲል የአሜሪካ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ሀላፊ 'ሲቢኤስ' ለተባለው የዜና ድርጅት አሉት እንደተባለው ከሆነ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን በኢራን ሚሳኤል ነው ተመትቶ ወደቀው።

ዩክሬን ቀደም ብላ አውሮፕላኑን እንዲከሰከስ ያደረገው ከኢራን የተተኮሰ ሚሳኤል ሊሆን እንደሚችል ግምት አስቀምጣ የነበረ ሲሆን ኢራን ግን ሊሆን አይችልም በማለት አጣጥላው ነበር።

ሲቢኤስ የጠቀሳቸው ከፍተኛ የደህንነት ሀላፊ አውሮፕላኑን ያጠቁ የሁለት ሚሳኤሎች ድምጽ ከተሰማ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ሶስተኛ ሚሳኤል እንደተከተለ ከሳተላይት የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

በሌላ በኩል 'ኒውስዊክ' በበኩሉ አንድ የፔንታጎን ከፍተኛ ሀላፊና የኢራቅ የደህንነት አባልን ጠቅሶ እንደዘገበው የዩክሬኑ አውሮፕላን ተመትቶ የወደቀው ሩሲያ ባመረተችው 'ቶር' በሚባል ሚሳኤል ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትናንት ባስተላለፉት መልእክት ''ከዚህ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ጥርጣሬ አለኝ። የሆነ ሰው ስህተት ሳይሰራ አይቀርም'' ብለው ነበር።

የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ አውሮፕላን ቴህራን ከሚገኘው ኢማም ኮሜይኒ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው የተከሰከሰው።

አውሮፕላኑ ጉዞውን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አድርጎ ነበር የተነሳው።