170 ሰዎችን የጫነ የዩክሬን ቦይንግ አውሮፕላን ኢራን ውስጥ ተከሰከሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዩክሬን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 800 አውሮፕላን ከ170 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ ጉዞ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ኢራን ውስጥ መከስከሱን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የኢራን ቀይ መስቀል ማሕበር የተረፉ ሰዎች ይኖራሉ ብሎ መገመት አዳጋች ነው ብሏል።
አውሮፕላኑ ከ170 በላይ ተሳፋሪ መንገደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች አሳፍሮ ከቴህራን እንደተነሳ ታውቋል።
የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ አውሮፕላን ቴህራን ከሚገኘው ኢማም ኮሜይኒ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው የተከሰከሰው።
አውሮፕላኑ ጉዞውን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አድርጎ ነበር የተነሳው።
በቴህራን የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት የሆነው የሞተሩ ብልሽት መሆኑን በመግለጽ የአሸባሪ ጥቃት ነው ሚለው ከትርጣሬ ውጪ ነው ሲል አስታውቋል።።
"ባለን ቅድመ መረጃ መሠረት ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያቱ ሞተሩ ላይ ያጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት ነው። አሁን ባለን መረጃ የአሸባሪ ጥቃት ነው የሚለው ከግምት ውጪ ነው"
በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት 82 ኢራናውያን፣ 63 ካናዳውያን፣ 11 ዩክሬናውያን፣ 10 ሲውዲናውያን፣ አራት አፍጋኒስታናውያን፣ ሶስት እንግሊዛውያን፣ ሶስት ጀርመኖች እና የበረራ ሠራተኞች መሆናቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቫዲም ፕሪስታኮ ገልፀዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ አደጋው ሥፍራ የተላኩ ሲሆን አውሮፕላኑ ከማረፊያው ብዙም ሳይርቅ ነው የተከሰከሰው ተብሏል።
የዩክሬን መንግሥት አደጋውን የሚያጣ ቡድን ማዋቀሩን እና ለሥራ ጉብኝት ወደ ኦማን አቅንተው የነበሩት ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ ጉብኝታውን አቋርጠው ወደ ኪዬቭ መመለሳቸው ተነግሯል።
ዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ወደ ኢራን የሚያደርገውን በረራ ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ መሰረዙን ግልጿል። የአየር መንገዱ ፕሬዝደንት የተከሰከሰው ቦይንግ 737-800 አፕሮፕላን የተሰራው እአአ 2016 እንደነበረ እና በታቀደለት መሰረት ጥገና የተካሄደለት ባለፈው ሰኞ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በታሪኩ አስከፊ አደጋ አጋጥሞት አያውቅም። ፕሬዝደንቱም አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት ምንም አይነት የቴክኒክ ችግር ምልክት እንዳልታየበት ገልጸዋል።













