አሜሪካ አየር መንገዶቿ በኢራቅና ኢራን አየር ክልል ላይ እንዳይበሩ አገደች

የፎቶው ባለመብት, FlightRidar24
የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የአሜሪካ አየር መንገዶች በኢራቅ፣ ኢራን እና በኦማን ባህረ ሰላጤ እንዳይበሩ አሳስበ።
ይህ የአቪዬሽን አስተዳደሩ ማሳሰቢያ የወጣው ኢራን በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ካምፖች ላይ የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ካደረሰች በኋላ ነው።
በኢራቅ የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር መኖሪያዎች ከኢራን በተወነጨፉ የባሊስቲክ ሚሳኤሎች መደብደባቸው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትርም አረጋግጧል።
የኢራን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ጥቃቱ የተፈፀመው ለቃሲም ሱሊማኒ ግድያ ምላሽ ነው ብሏል።
በተያያዘ ዜና የዩክሬን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 800 አውሮፕላን 180 ሰዎችን አሳፍሮ ጉዞ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ኢራን ውስጥ ዛሬ ጠዋት መከስከሱን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአውሮፕላኑ አደጋ ከኢራንና አሜሪካ ውጥረት ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኑር አይኑር እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ፍላይትራዳር24 የተሰኘው የአውሮፕላኖችን የበረራ አቅጣጫ ጠቋሚ መሰረት የአሜሪካው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ክልከላውን ሲያወጣ በርካታ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያላደረጉ በረራዎች በተጠቀሰው የአየር ክልል ላይ በረራ ሲያደርጉ ነው።
የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ይህን ክልከላ ከማድረጉ በፊት ዋና መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ አየር መንገዶች በኢራን እና በኦማን ባህረ ሰላጤ የአየር ክልል ላይ እንዳይበሩ አግዶ የነበረ ሲሆን፤ በኢራቅ አየር ክልል ላይ ደግሞ ከ26ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ እንዲበሩ መክሮ ነበር።
ቻይና አየር መንገድ፣ ሲንጋፖር አየር መንገድ እና ደቡብ ኮሪያ አየር መንገድ በበረራዎቻቸው ላይ የኢራቅ እና ኢራን አየር ክልሎችን እንደማይጠቀሙ አስታውቀዋል።
















