በፈረንሳይ ከሱፐርማርኬት አንወጣም ያሉት ደንበኞች በፖሊስ እንዲወጡ ተደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ ውስጥ ከሱፐርማርኬት አንወጣም ያሉት ደንበኞች በፖሊስ እንዲወጡ ተገደዋል። ፖሊስ በጉዳዩ እጁን ያስገባው ደንበኞች በማስታወቂያው መሰረት ቴሌቪዥን በቅናሽ ካልተሸጠልን በማለታቸው ነው።
'ጌንት ካሲኖ' በመባል የሚታወቀውና በደቡባዊ ሞንፔሌ ከተማ የሚገኘው ሱፐርማርኬት በ 399 ዩሮ የሚሸጠውን ቴሌቪዥን በስህተት 30.99 ዩሮ የሚል ዋጋ በመለጠፉ ነው ከደንበኞቹ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የገባው።
ምንም እንኳን ዋጋው በስህተት የተጻፈ መሆኑን ድርጅቱ ቢገልጽም ደንበኞች ግን ካልገዛን አንወጣም ብለዋል። ድርጅቱም ከመሸጫው ዋጋ ባነሰ አልሸጥም በማለት ከደንበኞቹ ጋር እሰጥ ገባ ውስጥ ገብቷል።
በመጨረሻ ግን እልህ የተጋቡት ደንበኞች የመውጫ በሩን በመዝጋታቸው ፖሊስ ተጠርቷል።
በርካታ የፖሊስ አባላትም በቦታው በመድረስ ተጠቃሚዎቹ ከሱፐርማርኬቱ በግድ እንዲወጡ አድርጓል።
በአካባቢው የነበረ አንድ ግለሰብ ለፈረንሳይ ሚዲያዎች ሁኔታውን ሲያስረዳ ''በርካታ ሰዎች በጌንት ካሲኖ ሱፐርማርኬት ውስጥ ነበሩ። አንወጣም ብለው ሲያስቸግሩ ፖሊሶች መጥተው አስወጧቸው'' ብሏል።
አንዳንድ አካባቢው ነዋሪዎችም ሁኔታውን በመተንቀሳቃሽ ምስል በማስቀረት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጋርተውታል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በሀገሪቱ የንግድ ሕግ መሰረት ማንኛውም ሻጭ በሚሸጠው እቃ ላይ በለጠፈው ዋጋ እንዲሸጥ ያስገድዳል። እቃዎቹ ሲታሸጉ አንዳንድ መረጃዎች ቢሳሳቱም እንኳን ሲል ያክላል ሕጉ።
እንደዚህ አይነት የዋጋ ስህተቶች የተለመዱ ሲሆን መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገው 'ካቲይ ፓሲፊክ' አየር መንገድ አንደኛ ደረጃ መቀመጫዎችን በስህተት በ 675 ዶላር ለደንበኞቹ አቅርቦ ነበር።
ትክክለኛ ዋጋው 16 ሺ ዶላር ቢሆንም አየር መንገዱ ስህተት እንደተፈጠረ በመግለጽ ደንበኞቹን ገንዘብ ጨምሩ እንደማይላቸው አስታውቆ ነበር።












