ለ'መልካም ዕድል' በአውሮፕላን ሞተር ውስጥ ሳንቲሞች የወረወረው ግለሰብ ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"መልካም ዕድል" ለመመኘት በአውሮፕላን ሞተር ውስጥ ሳንቲሞች የወረወረው ቻይናዊ ተቀጣ።
ሉ ቻኦ የተባለው ግለሰብ፤ ባሳለፍነው ዓመት የካቲት ወር በአገር ውስጥ ለሚያደርገው በረራ፤ በምስራቅ ቻይና ከሚገኘው አንጊንግ ቲያንዡሻን አየር ማረፊያ ነበር የተሳፈረው።
ግለሰቡ በአውሮፕላን ለመጓዝ ሲሳፈር የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።
ታዲያ ጉዞው ሰላማዊና የተቃና እንዲሆንለት ለመመኘት ወደ አውሮፕላኑ ሞተሮች ሳንቲሞች ይወረውራል።
እርሱ እንዲህ ዓይነት ችግር ይገጥመኛል ብሎ ባያስብም፤ በአውሮፕላኑ ሞተሮች በአንዱ አቅራቢያ እንደ ቀላል የወረወራቸው ሳንቲሞች ከተገኙ በኋላ ግን አውሮፕላኑ እንዳይበር ታግዷል።
በወቅቱ አንድ የአየር መንገዱ ሠራተኛ በአውሮፕላኑ አንደኛው ሞተር አቅራቢያ ሁለት የቻይና፤ 1 ያን ሳንቲሞች ከተመለከተ በኋላ ነበር በረራው እንዲሰረዝ የተደረገው።
ተሳፍረው የነበሩ የአውሮፕላኑ መንገደኞች እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ የደህንነት ፍተሻም ተካሂዷል። መንገደኞቹም ሌላ ተለዋጭ አውሮፕላን እስከሚመደብላቸው ድረስ ለመጉላላት ተዳርገዋል።
ሉ የተሳፋሪውን እንቅስቃሴን አውኳል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ አስር ቀናትን በእስር አሳልፏል፤ ነገር ግን ጉዳዩ በፍትሐ ብሔር ሕግ የታየው ግለሰቡ ካሳ እንዲከፍል ተወስኗል።
የ28 ዓመቱ ግለሰብ 'ላኪይ ኤር' ለተባለው አየር መንገድ 17,200 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ትዕዛዝ ተላልፎበታል።
በዚህ ድርጊቱም ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤ ፍርዱ የተላለፈበት በቅርቡ ነው።
ግለሰቡም ድርጊቱን መፈፀሙን አልካደም።
ላኪይ ኤር የግለሰቡ ድርጊት ለ17,600 ዶላር ኪሳራ እንደዳረገው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ግለሰቡ በበኩሉ አየር መንገዱ፤ "መንገደኞች ወደ አውሮፕላኑ ሳንቲም እንዳይወረውሩ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቅ ነበረበት" ሲል ተከራክሯል።
በእርግጥ አጉል እምነት ያላቸው መንገደኞች ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመው ሲያዙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በአውሮፓዊያኑ 2017 አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት በፈፀሙት ድርጊት የበረራ ሰዓት መዘግየቱን ጨምሮ፤ በቅርብ ዓመታት በርካታ ተመሳሳይ ክስተቶች አጋጥመዋል።













