ኢራናዊና አሜሪካዊ "ሰላዮች" በእስረኛ ልውውጥ ስምምነት ነፃነታቸውን ተቀዳጁ

የፎቶው ባለመብት, US Embassy Bern
ኢራንና አሜሪካ ባልተለመደ ሁኔታ ባደረጉት የሁለትዮሽ ስምምነት እስረኛ ለመቀያየር ወስነዋል።
ልውውጡ ኢራን ውስጥ "ሲሰልል" የተገኘ አንድ ትውልደ ቻይናዊ የሆነ አሜሪካዊ ተመራማሪና እንዲሁም በአሜሪካ እስር ቤት የነበረ ኢራናዊ ሳይንቲስት መካከል ነው።
ሁለቱም ሃገራት የስለላ ውንጀላውን ክደውታል። የእስረኛ ልውውጡን እወጃ ተከትሎ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደስታቸውን ገልፀዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከሰዓታት በኋላ በትዊተር ገፃቸው ላይ መልዕክታቸው ያሰፈሩ ሲሆን " ፍትሃዊ ስለሆነው ድርድር ኢራንን እናመሰግናለን፤ መስማማት ላይ ልንደርስ እንደምንችልም ይህ ማሳያ ነው" ብለዋል።
አሜሪካዊው ጁዩ ዋንግአ በኢራን መንግሥት በቁጥጥር ስር የዋለው ከሶስት አመታት በፊት ሲሆን የቀረበበት ክስም "ከውጭ ሃገር መንግሥታት ጋር በመመሳጠር" የሚል ነው።
በወቅቱ በኢራን ዩኒቨርስቲ የምርምር ስራውን እየሰራ የነበረው ጁዩ ጥብቅ መረጃዎችን ለአሜሪካና እንግሊዝ ተቋማት ሊሰጥ ነበር በሚል በስለላ ወንጀል አስር አመት ተፈርዶበትም ነበር።
ኢራናዊው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር መስዑድ ሶለይማኒ በበኩሉ በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው አመት ቺካጎ አየር ማረፊያ ላይ ነበር። ኢራን ላይ የተጣለባትን የንግድ ማዕቀብ በመጣስ ለኒውክሌር ፕሮግራም የሚሆን አንዳንድ ቁሳቁሶች ወደ ኢራን ሊያስገባ ሲል ይዘነዋል በሚል ክስ ነው የቀረበበት።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ በመጣው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ምክንያትም ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ ስዊዘርላንድ ሁለቱን ሃገራት በማሸማገል ሚና ተጫውታለች፤ በአፀፋው ሁለቱም ሃገራት ምስጋና ችረዋታል።
በስዊዘርላንድ መንግሥት አውሮፕላን ከቴህራን ወደ ዙሪክ የበረረው ጁዩ ዋንግ ሙሉ የህክምና ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ወደ ሃገሩ ይገባል ተብሏል።
ፕሮፌሰር መስኡድ ሶለይማኒም በተመሰሳይ ወደ ዙሪክ የበረረ ሲሆን ቀጣዩ ጉዞውም ወደ እናት ሃገሩ ኢራን ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Javad Zarif Twitter
የልውውጡንም ሆነ የመለቀቃቸውን ዜና ያበሰሩት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ ሲሆኑ ከፕሮፌሰር መስዑድ ጋር የተነሱትንም ፎቶ በትዊተር ገፃቸው አጋርተዋል።
"ፕሮፌሰር መስዑድ ሶለይማኒ እንዲሁም ጁዩ ዋንግ ተፈትተው ቤተሰቦቻቸውን ሊያገኙ መሆናቸው በጣም አስደስቶኛል" የሚል መልእክትም በትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት መግለጫ "ጁዩ ዋንግ በስለላ ሽፋን ታስሮ ነበር። በአስተዳደራችን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ቢኖር በተለያዩ ሃገራት በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን ነፃ ማውጣት ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጁዩ ዋንግ ባለቤት ሁዋ ኩ በበኩሏ "ቤተሰባችን አሁን ሙሉ ነው። ልጃችን ሻኦፋንና እኔ ሶስት አመታት በሙሉ በሰቀቀን ይህችን ቀን ጠብቀናል፤ የተሰማኝንም ደስታ በቃላት መግለፅ ይከብደኛል። ለረዱን አካላት በሙሉ ምስጋናችን ይድረሳቸው" ብላለች በሰጠችው መግለጫ
የድህረ ምረቃ ትምህርቱን እየተከታተለበት የነበረው ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ ከእስር የመለቀቁን ዜና በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ እንኳን ደህና መጣህ ብለውታል።












