ኡበር ታክሲ 6 ሺህ ጾታዊ ትንኮሳዎችን ይፋ አደረገ

ኡበር የንግድ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዓለም ቁጥር አንድ የዲጂታል ታክሲ አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኡበር በፈረንጆች 2017 እና 2018 ብቻ 6 ሺህ ጾታ ትንኮሳ ጥቆማዎች እንደደረሱት ይፋ አደረገ። ይህ ቁጥር በአሜሪካ ብቻ የተመዘገበ ነው።

ኡበር ይህን ቁጥር ለመጀመርያ ይፋ ሲያደርግ በጾታ ትንኮሳ ዙርያ የያዘውን ቁርጠኝነት ለማጉላት እንደሆነ ተናግሯል።

ኡበር በቅርቡ ለደንበኞቹ ደንታ ቢስ ነው በሚል ሲተች ነበር። በቅርቡም በለንደን የነበረውን የታክሲ ፍቃድ መቀማቱ ይታወሳል።

በሁለት ዓመት ውስጥ 2.3 ቢሊዮን ጉዞዎችን ያደረገው ኡበር የትንኮሳዎቹ ቁጥር 6ሺህ ብቻ መሆናቸውን ከመግለጹ ባሻገር የትንኮሳ ቁጥሩ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግሯል።

ከምሰጣቸው አገልግሎቶች 99.9 የሚሆኑት በሰላም የሚጠናቀቁ ናቸው ይላል ኡበር።

የሚገርመው ታዲያ ጾታዊ ትንኮሳውን ከሚያደርጉት ውስጥ የሚበዙቱ መንገደኞች እንጂ ሾፌሮች አይደሉም።

ኡበት እንዲህ አይነት መረጃ ሲያወጣ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ብዙ ኩባንያዎች እንዲህ አይነት መረጃን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አደጋ ነው፤ የኩባንያውን ስም ያጎድፋል ብለው ያስባሉ፤ እኛ አዲስ የግልጽነት መንገድ መጀመር እንፈልጋለን ብለዋል የኡበር የሕግ ክፍል ባልደረባ ቶኒ ዌስት።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ኡበር ለቢቢሲ እንደገለጸው ከአሜሪካ ገበያው ውጪ እንዲህ አይነቱን አሃዝ በሌሎች አገሮች ምን እንደሚመስል ለመግለጽ ፍቃደኛ አይደለም።