ግማሽ ቢሊዮን ብር የዘረፉት ባለሥልጣን ጥፋተኛ ተባሉ

ታትሟል

ሙስና በተንሰራፋባት ናይጄሪያ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ ተጠሪ የሆኑት የሕዝብ እንደራሴ ኦሪጂ ካሉ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መዝብረዋል በሚል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ይህ ገንዘብ በወቅቱ ምንዛሬ ሲሰላ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያልፋል።

ኦሪጂ ካሉ የገዢው የሙሐመድ ቡሃሪ ፓርቲ አባል ከመሆናቸውም ባሻገር በአገሪቱ ሸንጎ ውስጥ የፓርቲው ተጠሪ ሚኒስትር ነበሩ።

የሙስና ክሱ በፈረንጆች 2007 የተጀመረ ሲሆን በስማቸው በሚገኘው ኩባንያ በኩል አንዳች አሻጥር ሰርተው የመንግሥትንና የሕዝብ ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ዶለዋል በሚል ነበር የተጠረጠሩት።

ገንዘቡ ተመዝብሯል የተባለው እርሳቸው የደቡብ ምሥራቅ አቢየ ግዛትን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ነበር።

ካሉ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሲላቸው ሰውነታቸው ይንዘፈዘፍ ነበር ሲል ጽፏል፤ አንድ የአገሬው ጋዜጣ። ፖሊሶችንም "እባካችሁ እጀ ሙቅ አታጥልቁብኝ" ብለው ሲማጠኑ ነበር።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ለ2ኛ ጊዜ ሲመረጡ ሙስናን ከስሩ ለመመንገል ቃል ገብተው ነበር።