ሰሜን ኮሪያ ትራምፕን በአዲስ መልክ መዝለፍ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ተገናኝተው የመከሩት ኪምና ዶናልድ ለወራት ድምጻቸው ሳይሰማ ቆይቷል። በመሐላቸውም አንጻራዊ ሰላም ወርዶ ሰንብተዋል።
ሆኖም ሰሜን ኮሪያ ድንገት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያነጣጠረ ዘለፋ ጀምራለች።
የኪም ጆንግ ኡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶናልድ ትራምፕን "ነፈዝ ሽማግሌ" ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።
ሰሜን ኮሪያ ዶናልድ ትራምፕን 'ነፈዝ ሽማግሌ' ብላ መጥራት የጀመረችው በ2017 ነበር።
ከዚያ በኋላ እንዲህ አይነት ጸብ አጫሪ ቃላትን ከመጠቀም ተቆጥባ ቆይታለች። አሁን ለምን በአዲስ መልክ እንደጀመረቸው የታወቀ ነገር የለም።
ይሄ በእንግሊዝኛ ዶናልድን "Dotard" ብሎ የመስደቡ ፋሽን የመጣው ኪም ቃሉን መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ሲሆን፤ የእንግሊዝኛ ቃሉ ብዙም የሚዘወተር ቃል ባለመሆኑ የዓለም መገናኛ ብዙኀንን ትኩረት ስቦ እንደነበር ይታወሳል።
'ዶታርድ' የሚለውን ቃል የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት "በእድሜው መጃጀት ምክንያት የማስታወስ አቅሙ የደከመ ነፈዝ" ሲል ይተረጉመዋል።
ኪምና ዶናልድ በሰኔ 2018 ሲንጋፖር እንዲሁም በምናገባድደው የፈረንጆች ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በቪየትናም ተገናኝተው የሆድ የሆዳቸውን ተጫውተው ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን በሁለቱ መሪዎች መሐል አታካራም ይሁን የሰላም ቃላት በነው ሰንብተዋል።
ትራምፕና ዶናልድ ከቪየትናምና ከሲንጋፖሩ የሁለትዮሽ ስብሰባ ወዲህ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ከወታደርዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጠና ላይ ነበር።
ፒዮንግያንግ ለዋሺንግተን እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ አንዳች አዲስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልመጣ ግንኙነቴን በድጋሚ ለማጤን አግደዳለሁ ብላት ነበር።













