ሱዳን የቀድሞውን የአል-በሽር ገዢ ፓርቲ አከሰመች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሱዳን የቀድሞው ፕሬዝዳንት የኦማር አል-በሽር ገዢ ፓርቲን የሚያከስም ሕግ ፀደቀ።
በተጨማሪም የአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ሴቶችን የሚጨቁነውን ሕግንም ሽሯል።
ውሳኔ የተላለፈባቸው ሁለቱ ጉዳዮች፤ የአል-በሽርን አገዛዝ ለመጣል በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1989 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት አል-በሽር፤ ከመንበራቸው እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ ለሦስት አስርት ዓመታት ሱዳንን ገዝተዋል።
ሱዳን በአሁን ወቅት በወታደራዊ እና በሕዝባዊ አስተዳደር ጥምረትና ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዱክ በሚመሩት የሕዝብ ካቢኔ እየተዳደረች ትገኛለች።
የቀድሞው የአል-በሽር ገዢ ፓርቲ (ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ) ሲከስም፤ ባለሥልጣኖች የፓርቲውን ይዞታዎች መውሰድ የሚችሉ ሲሆን፤ ይህንን የሚያስፈጽም ኮሚቴ መዋቀሩም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዱክ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት፤ ውሳኔው "ከሱዳን ሕዝብ የተዘረፈውን ሃብት ማስመለስ ይችላል።"
የሥርዓቱ ምልክቶች ለቀጣይ አስር ዓመታት በፖለቲካው ምንም ተሳትፎ እንደማይኖራቸውም ተገልጿል።
የአል-በሽርን አገዛዝ ከሥልጣን ያወረደው የሱዳን ሙያተኞች ማኅበር ቃል አቀባይ ሳምሂር ሙባረክ እርምጃውን ለቢቢሲ "ታሪካዊ ክስተት ነው" ብለውታል።
ሱዳናዊያን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በሥርዓቱ በመጎዳታቸው፤ ውሳኔው እፎይታ እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።
ሴቶችን የሚጨቁነው አወዛጋቢ ሕግም ተሽሯል። የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ የሸሪዓ ሕግን በአስከፊ ሁኔታ የሚተረጉመው ሕጉ፤ ሴቶች ሠርግ ወይም ሌላም ድግስ ላይ በመገኘታቸው እንዲታሠሩ ያስገድድ ነበር። በየዓመቱ ብዙ ሺህ ሴቶች ለመታሠራቸውም ምክንያት ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዱክ "ሕጉ የዜጎቸን መብት የሚገፍ፣ በዝባዥ እና ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ነበር" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።
"በእነዚህ ሕጎች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው የአገሬ ሴቶችና ወንዶች ሀዘኔታዬን መግለጽ እወዳለሁ" ብለዋል።
አል-በሽርን ከሥልጣን ያስወገደው ተቃውሞ በዋነኛነት ሴቶችን ማዕከል ያደረገ እንደነበረ ይታወሳል። ሱዳን ዓለም አቀፉ የሴቶችን ጥቃት የመግታት ቀንን ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አስባ ውላለች። በርካታ ሴቶች አደባባይ ወጥተውም ድምጻቸውን አሰምተዋል።












