በደቡብ አፍሪካ የተፈፀመው መጤ ጠል ጥቃት ለአፍሪካ ውርደት መሆኑን የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Presidency Nigeria
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የደረሰውን መጤ ጠል ጥቃት ለአህጉሪቱ ውርደት ነው ሲሉ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በደቡብ አፍሪካ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት ነው።
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ናይጄሪያዊያንን ያገኙ ሲሆን የደረሰባቸውን መጤ ጠል ጥቃት ለአፍሪካ ውርደት መሆኑን በቲውተር መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
"በቅርቡ በናይጄሪያዊያንና በሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት አስደንግጦኛል . . . ይህ ለአህጉሪቱ ውርደት ነው።"
ባለፈው ወር በደረሰው ጥቃት በናይጄሪያዊያን ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ተቋማት ላይ ጥቃት ደርሷል።
ከዚህ ጥቃት በኋላም በናይጄሪያና በደቡብ አፍሪካ መካከል መቃቃር ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት በጥቃቱ ማፈራቸውን በመግለፅ ይቅርታ ጠይቀውል።
ሙሐመዱ ቡሃሪ ከናይጄሪያዊያን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ወቅት እንደተናገሩት፤ የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልፀው " እንዲህ አይነት ነገር ዳግም እንዳይከሰት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ" እንደገለፁላቸው ተናግረዋል።
ጆሀንስበርግ ከተማ የውጪ ሀገራት ዜጎች የንግድ ተቋማት ላይ በደቦ በተፈፀመ ጥቃት አስር ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ የውጪ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ጥቃቱ የተጀመረው የዕቃ ጫኝ መኪና አሽከርካሪዎች ከሌላ ሀገራት የመጡ ግለሰቦች ሥራችንን እየነጠቁ ነው በሚል የጅራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ባላት የሥራ እድል የተነሳ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ወጣቶች የሚፈልሱባት ሀገር ናት።
ምንም እንኳ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ቢያድግም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፤ ለዚህም አንዳንድ የአገሪቱ ዜጎች ከሌላ አገር የመጡ ግለሰቦች ሥራቸውን እየነጠቋቸው እንደሆነ ያስባሉ።
በደቡብ አፍሪካ ካሏት ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተጨማሪ 3.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞች እንደሚገኙ የአገሪቱ ስታስቲስቲክስ ቢሮ በቅርቡ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
70 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ደግሞ እንደ ዚምባብዌን፣ ሞዛምቢክንና ሌሴቶን ከመሳሰሉ የደቡብ አፍሪካ ጎረቤት ከሆኑ አገራት የሚመጡ ናቸው።
30 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ሥራ አጥ በሆነባት ሀገር ወጣቶች በአፋጣኝ ሥራ ማግኘት ካልቻሉ መጤ ጠልነትና አመጽ የማይቀሩ ነገሮች መሆናቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ።












