በዩክሬን አውሮፕላን ተከስክሶ አምስት ሰዎች ሞቱ

አደጋው የደረሰበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በዩክሬን የተከሰከሰው አውሮፕላን
ታትሟል

አንቶኖቭ-12 የተሰኘ አውሮፕላን ሊቭቭ ተብላ በምትጠራው የምዕራባዊ ዩክሬን ከተማ አቅራቢያ ተከስክሶ አምስት ሰዎች ሞቱ።

የአደጋው ምክንያትም አውሮፕላኑ ለማረፍ ካቀደበት ከተማ ከመድረሱ በፊት ነዳጅ በመጨረሱ ነው ተብሏል።

አውሮፕላኑ ከስፔኗ ቪጎ ከተማ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል በመብረር ላይ እንደነበረ የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚንስትሩ ቭላዲስላቭ ክሪክሊ ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ሚንስቴር እንዳለው ደግሞ በበረራው ሰባት ሠራተኞችና አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከዕቃ ጋር ተጭኖ እንደነበር ገልጿል። የተጫነው ዕቃ ምን እንደነበር ግን የተባለ ነገር የለም።

የዩክሬኑ ዩኒያን የዜና ወኪል ባሰፈረው መረጃ መሰረት አውሮፕላኑ የጦር አውሮፕላን ሲሆን፤ ሊቭቭ ከተሰኘችው የዩክሬን ከተማ ነዳጅ ለመሙላት እየገሰገሰ ነበር። ነገር ግን የሞላው ነዳጅ ሊቪቭም ሳያደርሰው ለአደጋ አጋልጦታል።

አደጋው የተከሰተበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በዩክሬን የተከሰከሰው አውሮፕላን

ባለአራት ሞተር የሆነው የሶቪየት ዲዛይን አውሮፕላን፤ ሊቪቭ አውሮፕላን ማረፊያ ለመድረስ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር (1500 ሜትር) ሲቀረው ነው የተከሰከሰው። ከተከሰከሰ በኋላ ምንም አይነት የእሳት አደጋ በስፍራው አላስከተለም።

አውሮፕላኑ ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ አቅራቢያ በአትክልት ስፍራና የመቃብር ቦታ አካባቢ ነው የተከሰከሰው።

አደጋውን ተከትሎ የሊቪቭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለጊዜው ተዘግቷል። በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ሰባት ሰዎች መካከል አምስቱ እንደሞቱ ቢነገርም ቀሪዎቹ ሁለት ሰዎች ስለመትረፋቸውም ሆነ ስላሉበት ሁኔታ የተባለ ነገር የለም።