በአሜሪካ የስድስት ዓመት ህጻናትን በቁጥጥር ስር ያዋለው ፖሊስ ከስራው ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ኦርላንዶ ከተማ ውስጥ ሁለት የስድስት ዓመት ህጻናትን በቁጥጥር ስር ያዋለው የፖሊስ አባል ከስራው መታገዱ ተገለጸ።
ከሁለቱ ህጻናት መካከል አንደኛዋ አስተማሪዋን በቁጣ ተማትታለች በሚል በካቴና እጇ ታስሮ እንደነበረ የህጻኗ አያት ገልጸዋል።
ዴኒስ ተርነር የተባለው የፖሊስ አባል ምንም አይነት ፍቃድ ሳያገኝና እድሜያቸው ያልደረሱን ሁለት ህጻናት በቁጥጥር ስር በማዋሉ ከስራው እንዲታገድ መደረጉን የከተማው ባለስልጣነት አስታውቀዋል።
የአቃቤ ህግ አባላት ደግሞ ከህጻናቱ መዝገብ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር የሚለውን መረጃ ለማስጠፋት እየሰሩ መሆኑ ታውቋል።
ሁለቱም ህጻናት መምህራቸው ላይ አካላዊ ጥቃት በመፈጸም ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።
የፖሊስ ሃላፊው ኦርላንዶ ሮሎን በሰጡት መግለጫ '' ከ11 ዓመት በታች የሆኑ ሶስት የልጅ ልጆች እኔም አሉኝ፤ ይህ በጣም አሳዛኝና አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ቢሯችን እንደዚህ አይነት ስህተቶችን ለማስቀረትና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል'' ብለዋል።
ፖሊስ የህጻናቱን ማንነት ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉት ህጻናት መካከል የአንደኛዋ አያት ''የልጅ ልጄ በደረሰባት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ምክንያት እንቅልፍ መተኛት አቁማለች'' ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።
'' የልጅ ልጄን ከእስር ቤት ለማምጣት ስሄድ የጣት አሻራ መረጃ እየተወሰደ ስለሆነ ትንሽ ደቂቃዎች እንድጠብቅ ተነግሮኝ ነበር። የጣት አሻራ መረጃ የሚለውን ስሰማ ራሴን ልስት ነበር። አንዲት የስድስት ዓመት ልጅ በወንጀል መክሰስ ተቀባይነት የለውም''።
'' ማንኛውም የስድስት ዓመት ህጻን እጁ በካቴና ታስሮ፣ በፖሊስ መኪና ተጭኖ ወደ ማቆያ መወሰድ የለበትም''
የኦርላንዶ ፖሊስ እንዳስታወቀው ዴኒስ ተርነር የተባለው የፖሊስ አባል ከስራው በጡረታ የተገለለ ሲሆን በትምህርት ቤቱ የትርፍ ጊዜ ጥበቃ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበር።












