ደቡብ አፍሪካውያን ጥላቻን ከሚያወግዝ ስብሰባ ረግጠው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ አንድ ታዋቂ የቀድሞ ፖለቲከኛ በቅርቡ የውጪ ሃገር ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን እና ጥላቻን ለማውገዝ ያዘጋጁት የንግግር መርሃግብር በአንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያን ተረብሿል።
ማንጎሹቱ ቡቴሌዚ የተባሉት ፖለቲከኛ ድንገት ነበር በአዳራሹ ከነበሩ ሰዎች ተቃውሞ የተሰነዘረባቸው። በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ወደ አዳራሹ መሃል በመግባት የውጭ ሃገራት ዜጎች ይውጡሉን የሚል መፈክር አሰምተዋል።
ባለፈው ሳምንት ተከስቶ በነበረው አመጽና ዝርፊያ ቢያንስ አስር ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ሁለቱ የውጭ ሃገራት ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ባሳለፍነው ሳምንትም ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 420 ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የገለጸ ሲሆን በሃገሪቱ አንጻራዊ ሰላም ስለመኖሩም ገልጿል።
ነገር ግን እሁድ ዕለት በጆሃንስበርግ ዋና ዋና መንገዶች ላይ '' የውጭ ሃገራት ዜጎች ወደ መጡበት መመለስ አለባቸው'' የሚል መፈክር የያዙ ደበብ አፍሪካውያን ስለመታየታቸው የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
መፈክሩን ሲያሰሙ የነበሩት ግለሰቦች በመቀጠል ቡቴሌዚ ንግግር ያደርጉበታል ወደተባለው ጁልስ ፓርክ ሄደዋል። በአፓርታይድ ዘመን የዙሉ መሪና የኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ ቀድሞው መሪ የነበሩት ቡቴሊዚ በቅርቡ ስለተከሰቱት ስለመረጋጋቶች ንግግር ለማድረግ ተዘጋጅተው ነበር።
በመቀጠልም በጉዳዩ ላይ እንደ አደራዳሪ ሆነው ለመስራት እንዳሰቡ በመግለጽ ''የተፈጸሙት ጥቃቶች ተቀባይነት የሌላቸውና የደቡብ አፍሪካ ስም በአህጉሪቱ ሃገራት ዘንድ እንዲጠለሽ ነው የሚያደርገው'' ብለዋል።
ነገር ግን ትዊተር ላይ በተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መሰረት ጥቂት የማይባሉ ደቡብ አፍሪካውያን ስብሰባውን ጥለው ሲወጡ ታይተዋል።
ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ደቡብ አፍሪካውያን ሥራችንን ወስደበውናል ያሏቸውን ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ላይ ጥቃት አድረሰዋል። አመፀኞቹ የውጭ ሃገር ዜጎች ሱቆችንና ንብረቶችን በመዝረፍ እና በማቃጠል ተጠምደው ነበር።
ብዙ ናይጄሪያውያን እና የናይጄሪያውያን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ የናይጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆፍሪ ኦንዬማ ''ማሰብ የተሳናቸው ወንጀለኞች'' የፈጸሙት ተግባር ነው በማለት መሰል ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆም ማሳሰባቸውም ይታወሳል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ንብረት ላይ የተፈጸመው ዝርፊያና ጥቃትን እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝደንቱ ''ለተፈጸመው ነገር ምንም አይነት ምክንያት ሊቀመጥለት አይችልም፤ ደቡብ አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያንን ማጥቃት አይችሉም'' ሲሉ ተደምጠዋል።
የዛምቢያ ትራንስፖርት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ደግሞ ትልልቅ የጭነት መኪኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረጉትን ጉዞ ለጊዜው እንዲያቆሙ አድርጓል።












