ታንዛንያውያን ደቡብ አፍሪካ የተቆጣጠረችውን አውሮፕላናቸውን ትመልስ እያሉ ነው

ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት የታንዛንያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን አውሮፕላን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንዛንያውያን ከደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ በመሄድ ተቃውሟቸውን እየገለፁ ነው።
ፖሊስም ተቃዋሚዎቹን ለመበተን ሙከራ እያደረገ ነው።
ኤርባስ 220-3 የተሰኘው የታንዛንያ አውሮፕላን ከጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰጠ ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ሳምንት አርብ እለት ነው።
አውሮፕላኗ በቁጥጥር ስር የዋለችው ታንዛንያ ለአንድ አርሶ አደር ያልከፈለችው ካሳ አለ በሚል ነው።
በጎርጎሳውያኑ 1980ዎቹ ታንዛንያ የእርሻ መሬትን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ስታደርግ 33 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዳልከፈለቻቸው የቀድሞ አርሶ አደር አደር ተናግረዋል።
ሁኔታው ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በተለይም ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ጭቆና ስር በነበረችበት ወቅት ድጋፍ የሰጠቻትን ታንዛንያን ውለታ ረስታለች በሚል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
በታንዛንያ መዲና ዳሬሰላምም ተቃውመው የወጡ ሰልፈኞች "አውሮፕላችንን እንዲመለስ እንፈልጋለን" ሲሉም ተሰምተዋል።
አንድ ተቃዋሚ በያዘው መፈክር ላይም "ለነፃነት ታጋዮቻችሁ ምግብ፣ መሬትና ስልጠና ለግሰናችኋል። አሁን ግን ፕሬዚዳንታችሁ ሲሲል ራማፎሳ ጠላቶቻችን እንዲጥሉን እድሉን ሰጥቷቸዋል። ኤይር ባሳችንን ልቀቁ" የሚል መልዕክት ተላልፏል።
ተቃውሞውን ያደራጁት አመራሮች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የዳሬ ሰላም የፖሊስ ኃላፊ ገልፀዋል።
ኃላፊው አክለው ከታንዛንያ የተላኩ ጠበቆችም አውሮፕላኗን ለማስለቀቅ እየሰሩ ስለሆነ ታንዛንያውያን እንዲረጋጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
መሬታቸውና የግብርና እቃ የተወረሰባቸው አርሶ አደር ለዘመናትም ያህል ካሳ እንዲከፈላቸው ቢታገሉም የተከፈላቸው የተወሰነውን ነው።












