አንድ ህፃንን ውሻ ቤት ውስጥ የቆለፈች ናይጄሪያዊት ተያዘች

ታትሟል

የናይጀሪያ ፖሊስ በአንድ ህፃን ላይ ጥቃት የፈፀመችና በውሻ ቤት ውስጥ አስገብታ የቆለፈችበትን ሴት በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ግለሰቧ ድርጊቱን ስትፈፅም የሚያሳው ተንቀሳቃሽ ምስል እንዴት እንደተቀረፀ ግልፅ ባይሆንም በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ የትዊተር ገፅ ተጠቃሚዎችን ያነጋገረ ነበር።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። በድርጊቱ የተደናገጡትም ግለሰቧን ተከታትሎ ለያዘ ሽልማት እንደሚሰጡ አስታውቀው ነበር።

ታዲያ ባለፈው ሐሙስ የናይጀሪያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዶላፖ ባድሞስ ግለሰቧ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሏን በትዊተር ገፃቸው አስታወቁ።

"ተጠርጣሪዋ ግለሰብ በእስር ላይ የምትገኝ ሲሆን ክስ ይመሰረትባታል፤ አሳዳጊውን ያጣው ህፃንም ከአደጋው ተርፎ በሌጎስ የመንግሥት መጠለያ ይገኛል" ሲሉም ቃል አቀባይዋ ገልፀዋል።

በትዊተር ገፃቸው ላይ ካሰፈሩት ፅሁፍ ሥርም በፖሊስ የተቀረፀውንና ህፃኑ ተቆልፎበት የነበረውን የውሻ ቤት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አያይዘዋል።