ሰሜን ኮሪያ አጭር ርቀት የሚምዘገዘግ ባሌስቲክ ሚሳዔል ሞከረች

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ሁለት ሚሳዔሎችን ባህር ውስጥ መተኮሷ ተሰማ። ይህ ሙከራዋ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ብቻ ካደረገቻቸው አምስት ሙከራዎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል።

ለሙከራ የተተኮሰው አጭር ርቀት የሚምዘገዘግ ባሌስቲክ ሚሳዔል ነው ተብሎ እንደሚታመን የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል አስታውቋል።

እንዲህ ዓይነቱ ሙከራ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ደንብን የተላለፈ መሆኑ ተረጋግጧል።

የዚህ መሳሪያ ሙከራ የተካሄደው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን "በጣም ቆንጆ ደብዳቤ" ደርሶኛል ካሉ በኋላ ነው።

ከሙከራው ትንሽ ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግሥት ለተገኙ የመገናኛ ብዙኀን አባላት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ስለደረሳቸው ደብዳቤ ሲናገሩ "በጣም አዎንታዊ መልዕክት ያለው ደብዳቤ ነው። ሌላ ስብሰባ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፤ በጣም ቆንጆ ባለ ሦስት ገፅ ደብዳቤ ነው የፃፈልኝ፤ ማለቴ ተጀምሮ እስኪያልቅ በጣም ቆንጆ የሆነ ደብዳቤ" ብለው ነበር።

ታዲያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር እያደረገች ያለውን የጋራ የጦር ልምምድ አላስደሰታቸውም።

ሚሳዔሉ የተተኮሰው ከምስራቃዊ የሐምሁን ከተማ ሲሆን ያረፈው ደግሞ የጃፓን ባህር ውስጥ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ምስራቃዊ ክፍል ነው።

ሚሳዔሉ 400 ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘግ ሲሆን 48 ኪሎ ሜትር ከፍታ መምዘግዘግ ይችላል ሲሉ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ሰሜን ኮሪያ ሰኔ ወር ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕና ኪም የኒውክለር መሳሪያዎችን ማስወገድ ላይ ዳግም ንግግር ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ በተከታታይ የሚሳዔሎችና የሮኬቶች ሙከራ አካሂዳለች።

የሰሜን ኮሪያ አስተዳደር አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የሚያደርጉት የጦር ልምምድ ያስቆጣው ሲሆን ፕሬዝዳንት ትራምፕና የደቡብ ኮሪያ አቻቸው ሙን ጄይ ኢን ከደረሱበት ስምምነት ውጪ ነው ሲል ይከሳል።

አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጋራ የጦር ልምምዳቸውን ሙሉ በሙሉ የሚጀምሩት ነገ ሲሆን አሁን ገና ዝግጅት እየተካሄደ ነው።

ልምምዱ ሰሜን ኮሪያ እንደ ትንኮሳ ትቁጠረው እንጂ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት ካደረጓቸው ልምምዶች ያነሰ ነው ተብሏል።

ሰሜን ኮሪያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተከታታይ ሙከራዎች ያደረገች ሲሆን ደቡብ ኮሪያ ሙከራው አዳዲስ አጭር ርቀት መምዘግዘግ የሚችሉ ሚሳዔሎች ናቸው ስትል ትከሳለች።

ከዚህ በፊት ሰሜን ኮሪያ የሞከረችው ሚሳዔል 690 ኪሎ ሜትር ድረስ የተወነጨፈ ነበር።