ቤተሰቦቹን የገደለውና ዶክተር ነኝ እያለ ያጭበረበረው ፈረንሳዊ ተለቀቀ

ጃን ክላውድ ሮማንድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ከ26 ዓመታት በፊት በሐሰት ዶክተር ነኝ በማለትና በግድያዎች ዘብጥያ የወረደውና አሁን የ65 ዓመት አዛውንት ሆኖ ከእስር ተፈታ።

ፈረንሳያዊው ጃን ክላውድ ሮማንድ በአንድ ወቅት እርግጥም የህክምና ተማሪ ነበር፤ ለዚያውም በብቃቱ ምሳሌ ተደርጎ የሚታይ።

ነገር ግን በሊዮን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የህክምና ተማሪ ሳለ የዓመቱ ማጠናቀቂያ ፈተና ላይ ሳይገኝ ቀረ። ዩኒቨርሲቲው ፈተናውን በቀጣዩቹ 12 ዓመታት እንዲወስድ እድል ቢሰጠውም ሮማንድ ሳይፈተን ቀረ።

ስለ ጉዳዩ ለሚጠይቁት ጓደኞቹ ግን የህክምና ትምህርት እየተከታተለ እንደነበርና በሂደትም የህክምና ዶክተር እንደሆነ ይነግራቸው ነበር።

18 ዓመታትን እንደ ዶክተር እየተወነ ከማገልገል ባሻገር የዓለም ጤና ድርጅት የህክምና ተመራማሪም እንደሆነ በማስመሰልም ብዙ ነገሮችን አድርጓል። ስዊዘርላንድ ውስጥ ኢንቨስት እያደረገኩ ነው በማለትም ከወዳጅ ዘመድ ከፍተኛ ገንዘብም አሰባስቧል።

በዚህ ፈረንሳያዊ ዶክተር ነኝ ባይ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሁለት ፊልሞች ተሰርተዋል፤ አንድ መፅሃፍም ተፅፏል።

እንደ አውሮፓውያን በ1993 እውነትም ዶክተር አለመሆኑ እየተጋለጠ በመጣበት ጊዜ ነው ግለሰቡ ሚስትና ልጆቹንም የገደለው።

ግለሰቡ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ እየሰራሁ ነው እያለ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ ድንበር አካባቢ እየነዳ ቀናትን ያሳልፍ አንዳንዴም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ቢሮን ይጎበኝም ነበር።

ሲመለስም ለሚስትና ለልጆቹ ስጦታ ይዞ ይመጣ እንደነበር ተነግሯል። ስዊዘርላንድ ውስጥ ኢንቨስት እያደረኩ ነው ብሎ ብር ከተቀበላቸው ዘመዶቹ አንዱ የሮማንድ ስም ከዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች ዝርዝር ውስጥ አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ የግለሰቡ ድራማ መጋለጥ ጀመረ።

በመጨረሻ ሚስቱን፣ የሰባት ዓመት ሴት ልጁን እና የአምስት ዓመት ወንድ ልጁን ገድሎ 80 ኪሎ ሜትር በመንዳት ወደ ወላጆቹ ቤት አመራ። እናትና አባቱን ውሻቸውን ጭምር ገደለ። እንደገና የሚስቱና የልጆቹ አስከሬን ከወደቀበት የራሱ ቤት ተመልሶ አቃጠለውና የእንቅልፍ ኪኒን ወሰደ።

ነገር ግን የነፍስ አድን ሰራተኞች ቦታው ላይ ደርሰው ሮማንድን አተረፉት። ከዚያም ያደረገውን ሁሉ ተናዝዞ በግድያ ክስ ተመሰረተበት።

ለ26 ዓመታት በእስር ላይ ከቆየ በኋላ ከአራት ዓመት በፊት በተሰጠው ምህረት መሰረት ከእስር ወጥቷል።