ህገወጥ የህጻናት ወተት አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የህጻናት ወተት

የፎቶው ባለመብት, NSW Police

ታትሟል

የአውስትራሊያ ፖሊስ እንዳስታወቀው በህገወጥ መንገድ የህጻናት ወተት ወደ ቻይና የሚያዘዋውሩ ስድስት ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር አውሏል።

የተሰረቀው ወተት ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሲሆን ባለፉት 12 ወራት በጥቁር ገበያዎች በውድ ዋጋ ሲቸበቸብ ነበር ተብሏል።

ባለፉት ዓመታት የህጻናት ወተት ሽያጭ የሚቆጣጠር የወንጀለኞች ቡድን በሰፊው ሲንቀሳቀስ እንደነበረና በቻይና ገበያዎች ያለውን ተፈላጊነት በመገንዘብ ትኩረቱን በእሲያዊቷ ሃገር አድርጎ ሲሰራ እንደነበረ ፖሊስ ገልጿል።

'ዋይት ጎልድ' ወይም ነጭ ወርቅ የሚል ስያሜ የተሰጠውና ከአውስትራሊያ የሚዘረፈው የህጻናት ወተት ቻይና ውስጥ እጅግ ተፈላጊ ነው ተብሏል።

አንድ የ31 ዓመት ተጠርጣሪ ከቻይና ሲመለስ በሲድኒ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ሌሎች ሶስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ደግሞ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሳምንታት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከስድስቱ ተጠርጣሪዎች አምስቱ ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል።

ጉዳዩን የሚከታተሉት ዋና መርማሪ ዳኒ ዶርቲ እንደተናገሩት ህገወጥ የህጻናት ወተት ዝውውር ቀለል ያለና እጅግ አትራፊ በመሆኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ጭነቶች ወደ ቻይና ተጓጉዘዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ ፖሊስ የተለያዩ እንክብሎችንና 215 ሺ ዶላር በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጿል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲሀ ደግሞ ብዙ አውስትራሊያውያን ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የሚሆን የወተት እጥረት እንዳጋጠማቸው በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።

አንድ የሃገሪቱ የቴሊቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ከሆነ አውስትራሊያ ውስጥ 30 ዶላር የሚሸጠው አንዱ እሽግ ቻይና ሲደርስ እስከ 100 ዶላር ያወጣል።