ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩስያዊው የቼልሲ ባለቤት ሮማን ብራሞቪች ስዊዘርላንድ እንዳይገቡ ተከለከሉ
ሩስያዊው ቢሊዬነር እና የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት የሆኑት ሮማን አብራሞቪች የስዊዘርላንድ መኖሪያ ፈቃድ ተከልክለዋል።
ቱጃሩ ሩስያዊ ወደ ስዊዘርላንድ እንዳይገቡ ፖሊስ ያገዳቸው ለሃገሪቱ ፀጥታ ስጋት ናቸው በሚል እንደሆነ ዘገባዎች እየጠቆሙ ነው።
የስዊዘርላንድ ፌዴራል ፖሊስ ነው ባለሃብቱ ከህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጉዳይ ጋር ንክኪ ይኖራቸው ይሆናል በሚል የመኖሪያ ፈቃድ እንዲነፈጋቸው ያደረገው።
አብራሞቪች ግን «እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያልፍም አይነካካኝ ብለዋል።»
የግለሰቡ ጠበቃም «ደንበኛዬ ሮማን አብራሞቪች ከህገ ወጥ ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ንክኪ የላቸውም» ሲሉ ጉዳዩን አጣጥለውታል።
ምንም እንኳ የአብራሞቪች ወደ ሃገረ ስዊዘርላንድ መግባት ለደህንነት አስጊ ነው ብሎ ፖሊስ ቢያስታውቅም እስካሁን ያወጣው ዝርዘር መረጃ የለም።
ጠበቃቸው ዳንኤል ግላስል ግን ሁኔታው እንዲህ በሚድያ መራገቡ እንዳበሳጫቸው አልደበቁም።
«የስዊዘርላንድ ፌዴራል ፖሊስ ጥርጣሬውን የሚደግፍ ማስረጃ አላገኘም፤ ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው» ሲሉም ጠበቃው አክለዋል።
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ገደማ ሮማን አብራሞቪች ወደ እንግሊዝ እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር አይዘነጋም።
ይህ ያሳሰባቸው አብራሞቪች 'የእስራኤል ቪዛ ያለው ሰው ወደ እንግሊዝ መግባት ይችላል' የሚለውን ህግ ተጠቅመው የእስራኤል ቪዛ በማውጣት ወደ እንግሊዝ መግባት ችለዋል።
የ51 ዓመቱ 'ልጥጥ' ሮማን አብራሞቪች ሩስያ አሉኝ ከምትላቸው ቱጃሮች አንዱ ናቸው፤ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋርም መልካም ወዳጅነት እንዳላቸው ይነገራል።