ሽመልስ ዐቢይ አሕመድን ያገኘ 'ለት

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ዋሽንገተን ዲሲ የሚገኘው 3506 International Dr NW ጎዳናን ይዞ የብዙ ሀገራት ኤምባሲዎች ተደርድረዋል፡፡
የዮርዳኖስ እና ባህሬን ኤምባሲዎችን ጎረቤት ያደረገው የኢትዮጵያ ኤምባሲም መገኛው ከዚያው ነው፡፡ወደ ኤምባሲው ለጉዳይ ከሚገቡ ከሚወጡት በተጨማሪ አንድ ሽበት ጣልጣል ያደረገበት ፣ኮከብ አልባውን ሰንደቅ ያነገበ፣ አነስተኛ የድምጽ ማጉያ የተሸከመ ሰው ይሄን መንገድ ያዘወትራል፡፡
እርሱ እንደሚለው የኤምባሲው ጠባቂዎች ገና ሲያዩት ፊታቸውን ያጠቁሩበታል፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ሽጉጥ የተመዘዘበት አጋጣሚም ነበር፡፡
ወደ ኋላ የምናነሳው ታሪክ ነው፡፡
ይህ ሰው ሽመልስ ለገሰ ይባላል፡፡ የዲሲው አድባር።
27 ዓመታትን በተቃውሞ
ከ1997 የኢትዮጵያ ዘመን ጀምሮ በዚህ ሥፍራ ያልተገኘባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው፡፡የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚነቅፉ ሰላማዊ ሰልፎች አሉ ከተባለ ሽመልስን በዚያ ማጣት ብርቅ ነው፡፡
"በአጋጣሚ በከተማው ውስጥ ሳልኖር የተደረጉ ሰልፎች ካልሆኑ በቀር ወይም የቤተሰብ አባል በሞት ተለይቶብኝ ካልቀረሁ በስተቀር ሁሉም ሰልፎች ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡" ይላል ሽመልስ።
ከሊቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በተደረገ አንድ ሰልፍ የቤተሰብ አባል በሞት ተለይቶበት መቅረቱን አይዘነጋውም።
ሽመልስ ከሀገር ከወጣ ሃያ ሰባት ዓመታት አልፈውታል፡፡ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር በቡድን በመምጣት፣ ካልሆነም ብቻውን ሰንደቅ ተሸክሞ ከኤምባሲው ፊት ለፊት በመቆም ጮክ ብሎ መፈክር ያሰማል፡፡በእሱ አነጋገር "መልዕክት" ያስተላልፋል፡፡
ብዙ ጊዜ ትዕይንተ ተቃውሞው በሰላማዊ ሁኔታ ይጠናቀቃል፡፡አንዳንዴ ደግሞ ከመንግሥት ደጋፊዎች ጋር እንካ ሰላንቲያ ይፈጠራል።
መስከረም 19 ቀን 2007 ዓ. ም ግን የከፋ ነገር ተፈጠረ።ሽመልስ ከሞት ጋር ሊፋጠጥ ግድ ሆነ፡፡
ለሽጉጥ ሩብ ጉዳይ
ሽመልስ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠቀመውን ሰንደቅ ዓለም ብሎም ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎች በሥራ ላይ እንዳይውሉ የሚከለክለውን የባንዲራ ሕግ አጥብቆ እንደሚቃውም ይናገራል፡፡
ይሄን ለማሳየት የሄደበት መንገድ እና የተከተለው ርምጃ ግን የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረትን ሳይቀር ወስዷል።
"በዚያን ሰሞን በኢትዮጵያዊያን ላይ ለመግለጽ የሚከብደው የሰብአዊ ጥሰት ይደረግ ነበር፡፡ይሄን በመቃወም በኤምባሲው ውስጥ የሚውለበለበውን ባንዲራ አውርደን የኛን(ኮከብ አልባውን) ባንዲራ ለመስቀል ወሰንን፡፡" ሲል ሽመልስ ክስተት የሚያብራርልን በወቅቱ በተለያዩ የአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የተሰራጨው ተንቀሳቀሽ ምስል በማስታወስ ነው፡፡
ባንዲራ የጨበጠው ሽመልስና ጓደኞቹ ጥቁር ሱፍ ከለበሰና ሽጉጥ ከደቀነ የኤምባሲው ባልደረባ ጋር ተፋጠዋል፡፡
በዚያ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሽጉጥ የጨበጠው ግለሰብ ወደ ባንዲራ መስቀያው ምሶሶ የሚያደርጉትን ሊከላከላቸው ሲሞክር ይታያል፡፡«ተኩስ ተኩስ!» ከሚሉ ጩኸቶች መካከል ሦስት ተከታታይ ተኩሶች ድንገት ይሰማሉ፡፡
ከተተኮሱት ጥይቶች መካከል አንዱ ከኤምባሲው ፊት ለፊት ያለውን ዛፍ እንደመታ ከቆይታ በኋላ ባለ ሽጉጡን በቁጥጥር ሥር የዋለውን ፖሊስ ጠቅሰው የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በወቅቱ ሁኔታውን ከዘገቡት ጋዜጦች አንዱ የሆነው "ዋሽንግተን ፖስት" የኤምባሲው ባልደረባ ሰለሞን ታደሰ ገብረሥላሴ የተባለ የ46 ዓመት ጎልማሳ እንደሆነና ከክስተቱ በኋላ በአሜሪካ ሕግ ይከሰስ ዘንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቲክ ያለመከሰስ መብቱን እንዲያነሳ ቢጠየቅ ስላልተስማማ ሰለሞን ከአሜሪካ ምድር እንዲለቅ እንደተደረገ አስነብቧል፡፡

የፎቶው ባለመብት, ScreenShot/YouTube
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና «ይቅርታቸው»
ለየት ባለ የተቃውሞ ድርጊቶቹ አድናቆት እና ወቀሳን ሲያፈራርቅ ለባጀው ሽመልስ ለገሰ፣ከትናንት በስትያ ልዩ ቀን ነበረች።
መንበረ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ እያደረጓቸው ላሉ ነገሮች አድናቆት እየቻራቸው እንደሆነ የሚናገርላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ አሜሪካ እንደሚመጡ ከሰማበት ቀን ጀምሮ አቀባበላቸውን ለማድመቅ ሲሰሩ ከነበሩት መካከል አንዱ መሆኑን ሽመልስ ይናገራል፡፡
ሆኖም እሳቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚደርሱበት አፍታ በፊት ግን እንደተለመደው ከኤምባሲው ባልደረቦች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቶ ነበር።
"ዝግጅቱ እስኪጀምር የኤምባሲው ሪሴፕሽ አካባቢ ቁጭ ብዬ ከጓደኞቼ ጋር እያወራሁ ነበር፡፡ድንገት ግን የኤምባሲው ረዳት ከሴክሬት ሰርቪስ አባላት ጋር በመምጣት ከኤምባሲው እንደወጣ አደረጉኝ›› የሚለው ሽመልስ ፤ከቅጽሩ ከወጣ በኋላ ፈንጠር ብሎ ተቃውሞውን ማሰማት ቀጠለ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥፍራው ደረሱ።
ከዚህ በኋላ የኾነውን እንዲህ ይተርካል።
"በምን ሁኔታ እንደሆነ አላውቅም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጅበው የመጡ ጠባቂዎች ወደኔ መጡ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያናግሩህ ይፈልጋሉ፡፡ 'ካላነገርኩት አልገባም ብለዋል' አሉኝ...፡፡"
"...ያለሁበት ቦታ ራቅ ስለሚል አላዩኝም፣ ድምፄን እንደሰሙ ግን እጠራጠራለሁ። ወደ ግቢው ፍተሻውን አልፌ ስገባ ከባልደረቦቻቸው ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆመው አየሁ፡፡አጠገባቸው ስደርስ ወንድሜ ብለው አቀፉኝ፡፡ ይቅር በለንም ሲሉ አናገሩኝ፣ እኔም 'ምንም ያደረጋችሁኝ ነገር የለም' ስል መለስኩ። "
ሽመልስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ከመድረሱ በፊት ጠባቂዎች ሰንደቁን ሊቀበሉት እንደሞከሩ፣ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተከላከሉለት ሽመልስ በኩራት ይናገራል፡፡
አቅፈው ወደ ውስጥ ካስገቡት በኋላ እሳቸው በሚቀመጡበት ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጥ ደጋግመው እንደጠየቁትና እሱ ግን አክብሮት የተነሳ ከእሳቸው ጋር ለመቀመጥ እንደማይችል በመንገር ሁኔታውን በአድናቆት ሲከታተል ወደ ነበረው ሕዝብ እንደተቀላቀለ ያስታውሳል፡፡
ሽመልስ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ባለቤቱ ወ/ሮ አይዳ መንግስቱ እና ልጁ ዳግማዊ ሽመልስ ሁሌም በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሚደግፉት ይናገራል።
ሽመልስ ካለነርሱ ድጋፍ ይህን እልህ አስጨራሽ የተቃውሞ ቀናትን ስለማለፉ ይጠራጠራል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Ethiotube/Yesuf Ibrahim
ወደ ሀገር ቤት
የዲሲ የተቃውሞ ሰፈር አድባር ሽመልስ ለገሰ አሁን ሀገር ቤት ለመመለስ ነገሮች ምቹ እየሆኑ እንደመጡ ያስባል፡፡
ሁልጊዜ ወደ ሚሟገትላት እና ወደ ሚናፍቃት ሀገር ድንገት ብድግ ብሎ የማይሄድበት ምክንያት በእንጥልጥል የቀሩ የግል ጉዳዮቹ እንደሆኑ ይናገራል፡፡
ወደፊት ግን ለመመለስ የቆረጠ ይመስላል። በዚያ በሚታወቅበት የመፈክር ድምጽ፣ "የግል ጉዳዬን እንዳሳካሁ፣ እገባለሁ ወደ ሀገሬ!' ይላል ሽመልስ፡፡















