ባለፉት 24 ሰዓታት ጋዛ ውስጥ 436 ሰዎች ተገድለዋል፡ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጋዛ ውስጥ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር አንዳስታወቀው የእስራኤል የአየር ጥቃት በቀጠለበት ሁኔታ በአንድ ቀን ውስጥ 436 ሰዎች ተገድለዋል።
ሁለት ሳምንት ባለፈው የአየር ጥቃት ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ5,000 ማለፉ ተገልጿል።
በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 5,087 የደረሰ ሲሆን፣ ትናንት ብቻ የሟቾች ቁጥር በ436 ጨምሯል።
ከተገደሉትመካከል 2,055 ሕጻናት፣ 1,119 ሴቶች፣ 217አረጋውያን እንደሚገኙበትተገልጿል።
በአስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ከ15,273 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ግዛቲቱን በሚቆጣጠረው እና ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ በገባው በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ነው።
እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው የቦምብ ድብደባ ትናንትና ቀን እና ሌሊቱንም የቀጠለ ሲሆን፣ ከጋዛ የወጡ ፎቶዎች የወደሙ ሕንጻዎችን እና በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ከሆስፒታሎች አቅራቢያ ባሉ መንገዶች ላይ ተኝተው አሳይተዋል።
ዛሬ ጠዋት የእስራኤል ጦር ሠራዊት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ 320 ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል። በዚህም የሐማስ ተዋጊዎች የሚገኙባቸው ዋሻዎች እና የቡድኑ የቅኝት ማማዎች ወድመዋል።
የአስራኤል ሠራዊት በሲቪሎች ላይ የደረሰን ጉዳት በተመለከተ በሰጠው ምላሽ፣ ዓለም አቀፍ ሕግን በመከተል “በሲቪሎች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለማስወገድ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ይደረጋል” ብሏል።



















