እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ዘመቻ አጠንክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የአገራቸው ሠራዊት በጦርነቱ የሚያካሂደው ዘመቻ ያለበት ደረጃ “መቀየሩን” በመግለጽ፣ “ተጨማሪ መረጃ አስኪሰጥ ድረስ” ዘመቻው ይቀጥላል ብለዋል። አርብ ምሽት ሠራዊቱ በወሰደው እርምጃ “የጋዛ ምድር ተንቀጥቅጣለች” በማለት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለአንድ ቴሌዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተኩስ አቁም እስኪደረሰ ታጋቾች እንደማይለቀቁ የሐማስ ተወካይ ተናገሩ

    ሞስኮን በመጎብኘት ላይ የሚገኙ የሐማስ የልዑካን ቡድን አባል ከእስራኤል የተወሰዱ ታጋቾች የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረስ ድረስ እንደማይለቀቁ መናገራቸውን አንድ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    የሩሲያው ኮመርሳንት ጋዜጣ አቡ ሐሚድን ጠቅሶ እንደዘገበው ሐማስ ታጋቾችን በሙሉ ለማግኘት ጊዜ ይፈልጋል ብለዋል።

    "አብዛኛዎቹ ሲቪሎች የሆኑ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ውለዋል። በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ፈልገን እስከምናገኛቸው ጊዜ እንፈልጋለን" ሲሉ ሐሚድ ተናግረዋል።

    እስካሁን አራት ታጋቾች "በሰብአዊ ምክንያቶች" በሐማስ ተለቀዋል። እናት እና ሴት ልጃቸው ጁዲት እና ናታሊ ራናን ጥቅምት 20 ሲለቀቁ፤ የ85 ዓመቷ ዮቼቭድ ሊፍሺትዝ እና የ79 ዓመቷ ኑሪት ኩፐር ሰኞ ተለቀዋል።

  2. አሜሪካ የኢራን ናቸው ያለቻቸውን በሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትን በአየር ደበደበች

  3. በምስል፡ የተጎዱ ፍልስጥኤማውያን ወደ ሆስፒታል እየገቡ ነው, ማስጠንቀቂያ፡ እነዚህ ምስሎች ስሜት የሚረብሹ ሊሆኑ ይችላሉ።

    እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓት በጋዛ ሰርጥ ያደረገችውን ድብደባ ተከትሎ የተጎዱ ፍልስጤማውያን ወደ ጤና ተቋማት እየገቡ ነው።

    ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በደቡባዊ ጋዛ ዃን ዩኒስ ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል ሲወሰዱ የሚያሳዩ ምስሎችን የተለያዩ የዜና አውታሮች ይፋ አድርገዋል።

    ማምሻወንም እስራኤል ሌላ ዙር የአየር ድብደባ በከተማይቱ ላይ መፈጸሟ ተዘግቧል። የእስራኤል ጦር ሲቪሎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ከሰሜኑ የሰርጡ ክፍል ወደ ደቡብ እንዲሸሹ ጠይቋል።

    የአየር ድብደባው እና ወረራው ደቡብ ጋዛን ጨምሮ በመላው ጋዛ ሰርጥ ቀጥሏል።

    የተጎዱ ፍልስጥኤማውያን ወደ ሆስፒታል እየገቡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተጎዱ ፍልስጥኤማውያን ወደ ሆስፒታል እየገቡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተጎዱ ፍልስጥኤማውያን ወደ ሆስፒታል እየገቡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  4. እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በርካታ የሐማስ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች

    የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት በጋዛ ሰርጥ በደርዘን የሚቆጠሩ የሐማስ ዒላማዎችን መደብደቡን የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

    የምድር ጦሩ በተዋጊ ጄቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ታግዞ በሹጃ’ያ አካባቢ ዒላማዎችን ደብድቧል። በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሌሎች ቦታዎችም መመታታቸውን መግለጫው ገልጿል።

    ዒላማ የተደረጉትም የፀረ ታንክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ቦታዎች፣ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎች፣ መቆጣጠሪያ ማዕከላት እና የሃማስ ተዋጊዎች ይገኙበታል የተባሉ ቦታዎች መሆናቸውን ጦሩ አስታውቋል።

    ዘመቻው እንደተጠናቀቀ ወታደሮቹ አካባቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን በእስራኤል ሠራዊት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰም አክሏል።

  5. የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ድምጽ ሊሰጥ ነው

    ፋይል ፎቶ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፋይል ፎቶ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ

    የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ አርብ ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም. በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ሊሰጥ ነው።

    የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የእስራኤል እና ፍልስጥኤም አምባሳደሮች ጦርነቱ በዜጎቻቸው ላይ ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ለጉባኤው ንግግር አድርገዋል።

    ድምጽ የሚሰጥበት የውሳኔ ሃሳብ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ተደርጎ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ፣ ተዋጊዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋቶች እንዲከበሩ ጠይቀዋል።

  6. በጋዛ የካቶሊክ መነኮሳት፡ “ሕዝባችንን ጥለን ወደ የትም አንሄድም”

  7. ሁለት ታንዛኒያውያን እና አንድ ደቡብ አፍሪካዊ በሐማስ ታግተዋል- እስራኤል

    በጋዛ ድንበር ላይ የምትገኘው ካቡትዝ ጥቃት አስተናግዳለች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ድንበር ላይ የምትገኘው ካቡትዝ ጥቃት አስተናግዳለች

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በሃማስ ከተያዙት 224 ታጋቾች መካከል ሁለት ታንዛኒያውያን እና አንድ ደቡብ አፍሪካዊ እንደሚገኙበት የእስራኤል መንግስት አስታወቀ።

    ሦስቱም በእስራኤል መንግሥት በስም አልተጠቀሱም።

    በእስራኤል የታንዛኒያ አምባሳደር ሁለት ዜጎቻቸው መታገታቸውን አረጋግጠዋል። ቢቢሲ በእስራኤል ጠፋ የተባውን ታንዛኒያዊ ጆሹዋ ሞልን አባት አናጋሯል። ታንዛኒያዊ ጥቃት በደረሰባት በኪቡዝ የግብርና ተማሪ ነበር።

    ስለልጁ እጣ ፈንታ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው ሐሙስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

    ጥቃቱ ከመድረሱ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ጀምሮ ከልጁ ጋር አለመነጋገራቸውን እና ቤተሰቡ ጭንቀት እንደገባው ተናግሯል ።

    "መብላትም ሆነ መተኛት አልቻልንም። ወደ ገበያ ስሄድ ሰዎች ለምን ክብደት እንደቀነስኩ ይጠይቁኛል" ሲል ገልጿል።

    ከታጋቾቹ መካከል አንዱ ደቡብ አፍሪካዊ ነው ስለመባሉ የአገሪቱ ባለስልጣናት የሰጡት አስተያየት የለም።

    በአጠቃላይ ከ25 አገራት የተውጣጡ የውጭ ዜጎች በሐማስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን እስራኤል ተናገራለች።

    ከተያዙት 224 ታጋቾች 135 ያህሉ የውጭ ዜጎች ሲሆኑ 54ቱ ታይላንዳዊያን መሆናቸው ታውቋል።

    ታጋቾቹ የተወሰዱት የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ወደ እስራኤል ገብተው ቢያንስ 1,400 ሰዎችን ከገደሉ በኋላ ነው።

    እስራኤል በወሰደችው የአየር የአጸፋ ጥቃት 6500 የሚጠጉ ሰዎችን መግደሏን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  8. ባይደን ኢራንን በቀጥታ አስጠነቀቁ

    ፕሬዝዳንት ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢራንን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ዒላማ እንዳታደርግ ኢራንን በቀጥታ ማስጠንቀቃቸውን ዋይት ሃውስ ገለጸ። ለኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ በቀጥታ ከተላለፉ ጥቂት ማስጠንቀቂያዎች አንዱ ነው ተብሏል።

    የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በሰጡት አጭር መግለጫ ላይ “ቀጥተኛ መልዕክት ተላልፏል” ብለዋል።

    ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።

    በአከባቢው ጥቃቶች መበራከታቸውን ተከትሎ 900 የሚጠጉ ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አካባቢው በማቅናት የአየር ኃይሉን ጥበቃ እንደሚያጠናክሩ ፔንታጎን ተናግሯል።

    ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ ቢያንስ 12 ጊዜ፤ በሶሪያ ደግሞ አራት ጊዜ ጥቃት ደርሶባቸዋል ሲል ፔንታጎን ገልጿል።

    ባይደን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮቿ ዒላማ መደረጋቸው ከቀጠለ ምላሽ እንደምትሰጥ አያቶላህን አስጠንቅቀው ነበር።

    መልዕክቱ ስለተላለፈበት መንገድ ግን ተጨማሪ ማብራሪያ አልተሰጠም።

  9. የግጭቱ ሰለባ ሆነው ሞታቸው ያልታመነላቸው የ4 ዓመቶቹ የፍልስጥኤም እና የእስራኤል ሕጻናት

  10. በእየሩሳሌም የታገቱ 224 ሰዎችን ለማሰብ 224 መብራቶች በሩ

    መብራት የማብራት ስነ-ስርዓት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ትናንት ሐሙስ ምሽት በሐማስ የታገቱ 224 ሰዎችን ለማሰብ 224 መብራቶች በእየሩሳሌም ሰማይ ላይ በርተው ታይተዋል።

    “የብርሃን ተስፋ” በሚል መርህ በተዘጋጀው መብራት የማብራት ስነ-ስርዓት ላይ የታጋቾች ማንነትን የሚያሳዩ ስም እና ፎቶግራፎች ቀርበዋል።

    መብራት የማብራት ስነ-ስርዓት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ሐማስ ከእስራኤል አግቶ በቁጥጥሩ ስር ከሚገኙት ታጋቾች መካከል 50 የሚሆኑት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየፈጸመችው ባለችው የአየር ጥቃት መገደላቸውን ትናንት ማስታወቁ ይታወሳል።

    መብራት የማብራት ስነ-ስርዓት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  11. አሜሪካ በሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን በአየር ደበደበች

    የአሜሪካ ጦር ጀት

    የፎቶው ባለመብት, US Department of Defense

    አሜሪካ በሶሪያ የሚገኙ ሁለት ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን በአየር ደብድባ ማውደሟን አስታወቀች።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአየር የተደበደቡት መሠረተ ልማቶች በኢራን እና የኢራን ተባባሪ በሆኑ ቡድኖች ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ናቸው ብሏል።

    በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር አርብ ንጋት ላይ በተፈጸመው የአየር ድብደባ ኢራን ጦር መሳሪያ ለማከማችት የምትጠቀምበት ስፍራ ወድሟል ተብሏል።

    መከላከያ ሚንስትሩ ላሎድ ኦስቲን አሜሪካን ይህን እርምጃ የወሰደችው በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላትን ለመጠበቅ እና በቅርቡ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ላደረሱት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።

    መከላከያ ሚንስትሩ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች በአሜሪካ ጦር ሠራዊት ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የማይቆም ከሆነ አሜሪካ አሁንም ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዷን ትቀጥላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላት እና ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ 12 ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን በዚህም ከ20 የማያንሱ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ፔንታጎን አስታውቋል።

    ኦስቲን ይህን የአየር ጥቃት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ያሉ ሲሆን የአየር ጥቃቱም ከእስራኤል ጋር በቅንጅት የተደረገ አይደለም ብለዋል።

    ይሁን እንጂ ይህ የአየር ጥቃት በመከላከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል።

  12. ፈረንሳይ በሐማስ ጥቃት የተገደሉት ዜጎቿ ቁጥር 35 ደርሷል አለች

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሐማስ ጥቃት የተገደሉት የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር 35 መስረሱን አስታወቀ።

    ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተገደሉት ፈረንሳያውያን ቁጥር 31 እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መገደላቸው እርግጥ ከሆኑት በተጨማሪ 9 ዜጎቹ አድራሻው አለመታወቁንም ገልጿል። ከእነዚህ መካከል በሐማስ እገታ ስር የሚገኙ እንዳሉም ታውቋል።

    የፈረንሳይ ዜጎችን “ከአገታት ለማስለቀቅ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው” ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።

    አድራሻቸው ከጠፋው እና በሐማስ ከታገቱ ሰዎች ቤተሰብ ጋር የቅርብ ግንኙነት እያደረገ እንደሆነ የፈረንሳይ መንግሥት ጨምሮ ገልጿል።

  13. የአረብ አገራት በጋዛ ሰላማዊ ሰዎች ዒላማ መደረጋቸውን አወገዙ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EFE

    በርካታ የአረብ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ እስራኤል እየፈጸመችው ባለው አየር ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን በጋዛ ሰርጥ ዒላማ አድርጋለች በማለት አወገዙ።

    ባህሬን፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሞሮኮ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በጋዛ ሰርጥ የሰላማዊ ሰዎች ግድያን የተቃወሙ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግም ተጥሷል ብለዋል።

    አገራቱ በጋራ መግለጫቸው እራሳን የመከላከል መብት፤ ሕግ መጣሳን እና የፍልስጥኤማውያንን መብት መጣሳን ትክክል አይደርግም ብለዋል።

    አገራቱ በጋዛ ሰርጥ ያሉ ሰዎችን በጅምላ የመቅጣት እና በኃይል የማፈናቀል እርምጃ ያሉትን የእስራኤልን ጥቃት ጨምረው አውግዘዋል።

  14. የሐማስ ልዑክ ሞስኮ እንደሚገኝ ተዘገበ

    የሩሲያ መንግሥት ባጋራው ምስል ላይ ሙሳ አቡ ማርዙክ ታይተዋል (ከግራ ወደቀኝ መጨረሻ)

    የፎቶው ባለመብት, Telegram

    የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ መንግሥት ባጋራው ምስል ላይ ሙሳ አቡ ማርዙክ ታይተዋል (ከግራ ወደቀኝ መጨረሻ)

    የሐማስ ልዑክ በሩሲያ መዲና ሞስኮ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነውን ሪአ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በሞስኮ በጉብኝት ላይ ከሚገኙት መካከል የሐማስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሙሳ አቡ ማርዙክ ይገኙበታል።

    ሩሲያ ከእስራኤል፣ ከኢራን፣ ከፍልስጥኤም መንግሥት እና ከሐማስ ጋር ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ አሁን ለተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ውድቀት ነው ብላለች።

    የቡድኑ አባላት በሞስኮ በሚኖራቸው ቆይታ ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ያገታቸው የሩሲያ ዜጎች በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ንግግር ይደረጋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።

    የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ በበኩላቸው የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ባግጂሪ ካኒ በአሁኑ ወቅት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሞስኮ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

  15. እስራኤል የሐማስ የድኅንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊን ገደልኩ አለች

    የእስራኤል ጦር የሐማስ ቁልፍ መሪ የሆነውን ግለሰብ እያካሄደችው ባለው አየር ጥቃት መግደሏን ገለጸች።

    ጦሩ ገደልኩት ያለው ሻዲ ባሩድ የተባለው ግለሰብ፣ የሐማስ የደኅንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንደነበረ እና በእስራኤል ላይ የተከፈተውን ድንገተኛ ጥቃት ዕቅድ ካወጡት መካከል አንዱ ነው ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በአየር ጥቃት የተገደለው ሻዲ ባሩድ በጋዛ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆነው ያሃያ ሲንዋር ጋር በቅርበት ይሠራ ነበር ብለዋል።

    ያሃያ ሲንዋር ጋዛ ከሚገኙ የሐማስ መሪዎች መካከል በእስራኤል በጥብቅ ከሚፈለጉ ቀዳሚው ነው።

    የሐማስ የደኅንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መገደልን በተመለከተ የሐማስ የጦር ክንፍ የሆነው ቃሳም ብርጌድ አስካሁን የሰጠው ማረጋገጫ ሆነ ማስተባበያ የለም።

  16. ሐማስ ካገታቸው ሰዎች መካከል 50ዎቹ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል አለ

    ሐማስ ከእስራኤል አግቶ በቁጥጥሩ ስር ከሚገኙት ታጋቾች መካከል 50 የሚሆኑት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየፈጸመችው ባለችው የአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታወቀ።

    የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ በተዋጊዎቹ ተይዘው ከነበሩ ታጋቾች መካከል በእስራኤል የአየር ድብደባዎች 50 ያህሉ ተገድለዋል ብለዋል።

    አቡ ኦቤይድ የተባሉት የሐማስ የጦር ክንፍ ቃል አቀባይ 50 ታጋቾች ተገድለዋል ከማለት ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

    ቢቢሲ የዚህን መረጃ ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

    ሐማስ ቅዳሜ መስከረም 26/2106 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን የሆኑ፣ የበርካታ አገራት ዜጎች ያሉበት 224 ሰዎችን ማገቱን እስራኤል ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።

  17. እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብራ የገባችው 'ለቀጣዩ ዘመቻ ዝግጅት ነው' አለች

    የእስራኤል ታንክ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤል ጦር ወደ ተመረጡ የጋዛ አካባቢዎች ረቡዕ ሌሊት ሰብሮ በመግባት ጥቃት የፈጸመው ለቀጣዩ ዙር ውጊያ ዝግጅት ለማድረግ ነው ብሏል።

    እስራኤል ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት በሐማስ ድንገተኛ ጥቃት ከተከፈተባት በኋላ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን በጋዛ ላይ ስትፈጽም ቆይታለች።

    ቴል አቪቭ የአየር ጥቃቱን እያደረሰች በምድር ኃይል በጋዛ በኩል ጥቃት ለመክፍት ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።

    ረቡዕ ሌሊት እስራኤል “በተመረጡ ስፍራዎች” በታንክ የታገዘ ወረራ የፈጸመች ሲሆን፣ ይህ ግን ለቀጣዩ ጦርነት ዝግጅት እንጂ በምድር ኃይል የማደርገው ጥቃት አይደለም ብላለች።

    የእስራኤል ጦር ለሰዓታት በቆየው ዘመቻ በወታደሮቹ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ “አሸባሪዎች ተወግደዋል” ብሏል።

    እስራኤል ጥቃት የፈጸመባትን የሐማስ ቡድንን ከጋዛ ለማጥፋት የዛተች ሲሆን፣ በጋዛ ድንበር ዙሪያ ከ300 ሺህ በላይ ሠራዊቷን እና ከባድ መሳሪያዎቿን በተጠንቀቅ አቁማለች።

    አንዳንድ አገራት እስራኤል ወደ ጋዛ ዘልቃ እንዳትገባ እየወተወቱ ቢሆንም፣ የእስራኤል ሠራዊት ግን በጋዛ ላይ ለሚፈጽመው የእግረኛ ሠራዊት ወረራ ዝግጅት እና የመጀመሪያ ደረጃ ዘመቻዎችን እኣካሄደ መሆኑን ገልጿል።

  18. ኤርዶዋን ምዕራባውያን ፊታቸውን ያዞሩት “የሚፈሰው የሙስሊም ደም” ስለሆነ ነው አሉ

    የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን

    የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለው ጥቃት ምክንያት ምዕራባውያንን አጥብቀው ተቹ።

    ኤርዶዋን በጋዛ “እየፈሰሰ ያለው የሙስሊም ደም በመሆኑ” ምዕራባውያን መንግሥታት እርምጃ እየወሰዱ አይደለም ብለዋል።

    “ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ለምን አይከበርም?” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል። “ጥቅማቸውን የማያስከብር ከሆነ [ምዕራባውያኑ] ዞር ብለው አይመለከቱም። ለምን? ምክንያቱም እየፈሰሰ ያለው የሙስሊም ደም ስለሆነ ነው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ የሰረዙ ሲሆን፣ ባለፈው ወር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁን "እጅ መጨበጤ ይቆጨኛል" ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ለቱርክ ፓርላማ ሲናገሩ እስራኤል በጋዛ “ጭፍጨፋ” እየፈጸመች ነው ያሉ ሲሆን፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ “ለነጻነት” እየታገሉ ነው ብለዋል።

    “ሐማስ አሸባሪ አይደለም። ለዜጎች እና ለመሬታቸውን የሚታገል የነጻነት ድርጅት ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተደምጠዋል።

  19. ማዕከላዊ እስራኤልን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ሮኬቶች ተተኮሱ

    ከጋዛ የተወነጨፉ ሮኬቶች በአሽኬሎን ከተማ ሰማይ ላይ ይታዩ ነበር።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ከጋዛ የተወነጨፉ ሮኬቶች በአሽኬሎን ከተማ ሰማይ ላይ ይታዩ ነበር።

    ባለፉት ሰዓታት ማዕከላዊ እስራኤልን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሮኬቶች ከጋዛ መተኮሳቸው ተዘገበ።

    ይህን ተከትሎ የአየር ጥቃት የማስጠንቀቂያ ደውሎች በአብዛኛው የእስራኤል ክፍል ተሰምቷል።

    የእስራኤል አየር መቃወሚያ ሥርዓትም በሐማስ ተተኩሰዋል የተባሉ አብዛኛዎቹን ሮኬቶች ስለማክሸፉም በስፋት ተዘግቧል።

    ከእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ፔታህ ቲክቫ ውስጥ ሮኬት ወይም የሮኬት ፍንጣሪ ያወደመው ሕንጻ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሸከረከር ነበር።

    የአየር ጥቃት የማስጠንቀቂያ ደውሎች ከተሰሙ በኋላ የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።

    ሐማስ እነዚህን ሮኬቶች የተኮስኩት እኔ ነኝ ብሏል።

    ቡድኑ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።

  20. ጋዛ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉ ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ አለፈ

    በጋዛ የደረሰ ውድመት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ከሦስት ሳምንታት በፊት የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ ማለፉ ተነገረ።

    በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ከቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ወዲህ አስካ ዛሬ ሐመስ ድረስ ጋዛ ውስጥ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ በላይ ሆኗል ብሏል።

    ከእነዚህ ሟቾች መካከል 2 ሺህ 900 የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት በጋዛ የሚገኙ 250 የሐማስ መገኛዎችን ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።