እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ዘመቻ አጠንክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የአገራቸው ሠራዊት በጦርነቱ የሚያካሂደው ዘመቻ ያለበት ደረጃ “መቀየሩን” በመግለጽ፣ “ተጨማሪ መረጃ አስኪሰጥ ድረስ” ዘመቻው ይቀጥላል ብለዋል። አርብ ምሽት ሠራዊቱ በወሰደው እርምጃ “የጋዛ ምድር ተንቀጥቅጣለች” በማለት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለአንድ ቴሌዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሚስቱ እና አራት ልጆቹ የተገደሉበት የጋዛ ነዋሪ

    የልጆቹ አባት የአንደኛውን ልጁን አስከሬን አቅፎ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የልጆቹ አባት የአንደኛውን ልጁን አስከሬን አቅፎ

    በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኘው ጃባሊያ የስደተኞች ከምፕ ላይ በእስራኤል በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንዲት እናት ከአራት ልጆቿ ጋር ተገድለዋል። የልጆቹ አባት ሆስፒታል ውስጥ የአንደኛውን ልጁን አስከሬን አቅፎ ይዞ ሲያለቅስ ይታያል።

    “ዕድሜው ገና ሁለት ወር ተኩል ነው እኮ፣ ምን አጥፍቶ ነው?” ብሎ ለሮይተርስ የተናገረው አባት፣ “ሰው ገድሏል? አቁስሏል? ሰው አግቷል? ቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሁሉም ምንም የማያውቁ ልጆች ናቸው” በማለት ስተገደሉት ልጆቹ ተናግሯል።

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሰሜን ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው በመውጣት ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።

    ሚስቱ እና ልጆቹ የተገደሉበት አባትም “በታንክ በላዬ ላይ ቢሄዱብኝ እንኳን፣ ቤቴን ለቅቄ ወደየትም አልሄድም” ብሏል።

    “አሁንም በፈረሰው ቤቴ ላይ ድንኳን ሰርቼ እዚያው ነው የምኖረው።”

  2. በእስራኤል- ጋዛ የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የጋዛ ጦርነት ሶስት ሳምንት ሊቀሩት ጥቂት ቀናትን ይዟል። በቅርብ ሰዓታት የነበሩ ጉዳዮችን እንዳስ

    • የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰሜናዊ ጋዛ 'ዒላማ በተደረጉ ቦታዎች ላይ የታንክ ወረራ መፈጸሙን አስታውቋል።
    • በርካታ "የአሸባሪ መቀመጫዎች፣ መሰረተ ልማትና ተከላካይ መተናል" ብሏል። - ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በጋዛ ላይ የእግረኛ ወረራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን በድጋሜ ቢናገሩም ወቅቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
    • የተባባሩት መንግሥታት በጋዛ ያለው ነዳጅ በሚቀጥሉት ሰዓታት ውስጥ ተሟጦ ሊያልቅ እንደሚችል ጠቁሞ በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሎች ለድንገተኛ ህክምናዎች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብሏል።
    • የአውሮፓ ህብረት አመራሮች በጋዛ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ይቻል ዘንድ ውጊያው ለአፍታ እንዲገታ ጥሪ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
    • የአለም ጤና ድርጅት ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች በህክምና ምክንያት እንዲለቅ ጠየቀ።
    • የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በእስራኤልና ፍልስጥኤማውያን መካከል ግጭቱ ከተነሳበት በፊት ወደነበረው ወደቀድሞው ሁኔታ መመለስ አይቻልም ሲሉ ተደምጠዋል።
  3. 'በጋዛ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም'- ተመድ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያንን ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቋን ተከትሎ የተባባሩት መንግሥታት በጋዛ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም የሚል ምላሽ ሰጠ።

    "ቀያቸውን ለቀው መሸሻ ላጡ ወይም መንቀሳቀስ ለማይችሉ ሰዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት ምንም ለውጥ አያመጣም" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ቢሮ የፍልስጥኤም አስተባባሪ ሊን ሄስቲንግስ ተናግረዋል።

    "መሸሻ መንገዶች በቦምብ ሲደበደቡ፣ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ጋዛ ያሉ ፍልስጥኤማውያን በጦርነት ማዕከል ውስጥ በሆኑበት፤ በህይወት ለመቆየት መሰረታዊ ነገሮች ሲታጡ፤ ከጦርነቱ በኋላ ለመመለስ ዋስትና በሌለበት ሁኔታ በርካቶች ፈታኝ ምርጫዎች ብቻ ይቀራቸዋል" ብለዋል።

    "የትኛውም የጋዛ ቦታ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም" ሲሉም አክለዋል። ጦርነቱ በአለም አቀፍ ህግ መመራት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

    "ይህም ማለት ሲቪሎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እና መቆየትም መረጡ ወይም መሸሽ መፈናቀል ለህይወት መቆያ የሆኑ መሰረታዊ አቅርቦቶች ሊሟላቸው ይገባል" ብለዋል። ታጋቾችንም በተመለከተ "ሁሉም ታጋቾች በአስቸኳይ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ ይገባል" ብለዋል።

  4. ጋዛ ከጦርነቱ በፊት እና አሁን- ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች

    የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ሶስት ሳምንታት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ነው የቀሩት።

    ሐማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።

    በዚህ አየር ጥቃት አንዳንድ የጋዛ ሰፈሮች ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ተቀይረዋል።

    ጋዛ ከጦርነቱ በፊት እና አሁን ያለችበትን የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎችን ቢቢሲ አግኝቷል። ከታች ያለው የመጀመሪያው ምስል በሰሜናዊ ጋዛ የምትገኘው ቤይት ሃኑን መስከረም 29/ 2016 ዓ.ም የተወሰደ ነው።

    ሁለተኛው የሳተላይት ምስል ከመጀመሪያው ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ የተወሰደ ነው።

    ጋዛ ከጦርነቱ በፊት እና አሁን- ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች
  5. የእስራኤል ጦር በጋዛ ‘ዒላማ በተደረጉ ቦታዎች’ የታንክ ወረራ ፈጸመ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰሜናዊ በጋዛ ‘ዒላማ በተደረጉ ቦታዎች’ በታንክ ወረራ መፈጸሙን አስታወቀ።

    ይህ ወረራ የተፈጸመው “ለውጊያው ቀጣይ ክፍል ለመዘጋጀት” መሆኑን ገልጿል።

    “ብዙ የአሸባሪ መቀመጫዎች፣ መሠረተ ልማትና ታንክ ተከላካይ ሚሳኤል መተናል” ሲልም አክሏል።

    ወረራውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል መከላከያ ኃይሉ ለቋል።

    “ወታደሮቹ ከዚያ ወጥተው አሁን ወደ እስራኤል ግዛት ተመልሰዋል” ብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቴሌቭዥን በተላለፈ ንግግራቸው የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመሬት ወረራ ለመፈጸም እየተዘጋጁ መሆናቸው ገልጸዋል። መቼ እንደሚፈጸም ግን ይፋ አላደረጉም።

    እስራኤል 1.1 የጋዛ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ለቀው እንዲወጡ ባለፈው ሳምንት መግለጿ ይታወሳል።

    ሆኖም ግን ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በደቡባዊ ጋዛ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት፣ ከጋዛ በስተሰሜን ካለው መኖሪያው ሸሽተው ከወጡ ፍልስጥኤማውያን መካከል የተወሰኑት ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ።

  6. ተመድ በነዳጅ እጥረት ምክንያት የጋዛ ስራው ሊቆም ይችላል አለ

    በጋዛ ላይ የደረሰው ውድመት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብቻታለሁ ባለችው የጋዛ ሰርጥ ነዳጅ እንዳይገባ በመከልከሉ ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ችግር እንደገጠመው አስታወቀ።

    በነዳጅ እጥረት ምክንያት በጋዛ እየሰጠ ያለው የሰብዓዊ አገልግሎት በሰዓታት ውስጥ ሊቆም እንደሚችልም ገልጿል።

    ተቋሙ በጋዛ ውስጥ ምን አይነት የሰብዓዊ አገልግሎት መስጠት ይችላል በሚለውም ላይ በሚቀጥሉት ሰዓታት ውሳኔ ላይ እንደሚደርስም ነው ያስታወቀው።

    የተባባሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም ስደተኞች ኤጀንሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተቋሙ ምናልባትም አገልግሎቱን መቀነስ አለበት ብለዋል።

    "ተቋሙ አገልግሎቱን እንዲቀጥል የሚላክልን የነዳጅ አቅርቦት ይኖራል ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። መጪዎቹ ሰዓታት ወሳኝ ናቸው" ሲሉም ነው ለቢቢሲ የተናገሩት

    ነዳጅ ካልገባልን "ፈታኝ የሚባል ውሳኔ ላይ መድረስ አለብን ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እርዳታ ለሚያስፈልገው የጋዛ ስርጥ ነዋሪ ሰብዓዊ ድጋፋችንን መቀነስ" ብለዋል።

    "ነዳጅ ወደ ጋዛ ካልገባ ውሳኔያችንን ዛሬ (ሐሙስ) የምናሳውቅ ይሆናል" ብለዋል።

  7. እስራኤል ‘አሸባሪ አገር’ ናት ያለችው አየርላንዳዊት ከሥራ ተባረረች

  8. የእስራኤል እግረኛ ጦር ጋዛ ሲገባ ከሐማስ ምን ሊገጥመው ይችላል?

  9. በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጉቴሬዝ ከዋና ፀሐፊነታቸው እንዲለቁ በድጋሚ ጠየቁ

    አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ዙሪያ ዛሬ [ረቡዕ] የሰጡትን ማብራሪያ ተከትሎ በድርጅቱ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን በቁጣ በሰጡት ምላሽ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሥልጣን እንዲለቁ በድጋሚ ጠይቀዋል።

    “ዋና ፀሐፊው የተናገሩትን ቃል መልሰው አለማስተባበላቸው፣ እንዲሁም ይቅርታ ለመጠየቅ አለመቻላቸው ለመንግሥታቱ ድርጅት ውርደት ነው” ሲሉ አምባሳደሩ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

    ኤርዳን የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝን “እውነታን በማዛባት እና በመጠምዘዝ” ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ለፈጸመው የጭካኔ ጥቃት እስራኤልን ከሰዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

    “ሐማስ ለፈጸመው ድርጊት እስራኤልን ጥፋተኛ አድርገው ማቅረባቸውን ከተናገሯቸው ቃላት ሁሉም ሰው በደንብ ሊረዳው ይችላል፣ ወይም ወደዚህ ጭፍጨፋ የመራውን ‘የኋላ ታሪክ’ በተመለከተ ያላቸውን መረዳት ያሳያል።

    “የትኛውም ‘የኋላ ታሪክ’ በንጹሃን ላይ የሚፈጸምን ግድያ ማስረዳት እንደማይችል የማይረዳ ዋና ፀሐፊ፣ ዋና ፀሐፊ ሊሆን አይችልም” ሲሉ አምባሳደሩ ጉቴሬዝ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ በድጋሚ ጠይቀዋል።

  10. ጉቴሬዝ ንግግራቸው በፈጠረው ውዝግብ መደንገጣቸውን ተናገሩ

    አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ዋና ፀሐፊው ዛሬ (ረቡዕ) ከሰዓት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ማክሰኞ ዕለት በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ያደረጉት ንግግር በፈጠረው ውዝግብ እንዳስደነገጣቸው ተናገሩ።

    ጉቴሬዝ በንግግራቸው ውስጥ “የሐማስ ጥቃት እንዲሁ ያለምክንያት የተከሰተ አይደለም” በማለት “ፍልስጥኤማውያን ለ56 ዓመታት በማያፈናፍን ወረራ ውስጥ ቆይተዋል” ብለው ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ተቆጠተው፣ ዋና ፀሐፊው ከዓለም አቀፉ ድርጅት ኃላፊነታቸው እንዲለቁ ከመጠየቅ በተጨማሪ ለተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቪዛ አስከመከልከል ደርሰዋል።

    ኒው ዮርክ ውስጥ የፀጥታው ምክር ቤት ማክሰኞ ዕለት ያተካሄደውን ስብሰባ ጉቴሬዝ ሲከፍቱ ሐማስ የፈጸመውን “አሰቃቂ እና አጋጥሞ የማያውቅ” ያሉትን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙ በመግለጽ፣ ሆን ተብሎ የተፈጸመውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ ጉዳት ወይም ማገት በምንም ሁኔታ ምክንያት የሚቀርብለት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት እና አስራኤል ለመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ቪዛ መከልከሏን ተከትሎ በሁኔታው መደንገጣቸውን አስታውቀዋል።

    ጉቴሬዝ ዛሬ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ንግግራቸው “በሐማስ የተፈጸመውን የሽብር ተግባር ምክንያታዊ ያደረኩት ያህል” ከአላግባብ ትርጉም እንዲይዝ በመደረጉ መደንገጣቸውን ገልጸዋል።

    ጉቴሬዝ ንግግራቸው የሐማስን ጥቃት ትክክለኝነት የሚያሳይ ሳይሆን፣ በተቃራኒው የሚገልጽ ሃሳብ መሆኑን ተናግረው፣ በድጋሚም ሐማስ በእስራኤል ላይ “የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት” አውግዘዋል።

    ጨምረውም በፍልስጥኤማውያን በኩል ያለውን ምሬት በተመለከተ የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያኑ ቅሬታ “በሐማስ የተፈጸመውን አስቀያሚ ጥቃት ትክክል አያደርገውም” ብለዋል።

    በማክሰኞው ንግግራቸው ምክንያት የተፈጠረውን ውዥንብር ለማጥራት እና የተናገሩትን ግልጽ ለማድረግ የፈለጉት ለጥቃቱ ሰለባዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ካላቸው አክብሮት የመነጨ መሆኑን ጉቴሬዝ ተናግረዋል።

  11. ባለፉት 24 ሰዓታት ከ700 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

    ጋዛ ውስጥ ከተገደሉ ሰዎች አስከሬን መካከል የሚታይ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጋዛ ውስጥ ከተገደሉ ሰዎች አስከሬን መካከል የሚታይ ሰው

    ባለፉት 24 ሰዓታት ጋዛ ውስጥ ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ባለሥልጣኑ ባወጣው መረጃ መሠረት በ24 ሰዓቱ ውስጥ 344 ሕጻናትን ጨምሮ 756 ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን ገልጿል።

    ሚኒስቴሩ እንዳለው እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ያልተቋረጠ የአየር ጥቃት ምክንያት የተገደሉ ሰዎች አጠቃላይ አሃዝ ከ6,500 በላይ ደርሷል።

    ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ጋዛ ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች ምክንያት ከተገደሉት 6,500 በላይ ሰዎች መካከል 2,704 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።

    በቅርብ ቀናት አስራኤል እያካሄደች ያለው ተከታታይ የአየር ጥቃት በተለይ በደቡባዊው የጋዛ ክልል ላይ በእጅጉ የበረታ መሆኑን የጤና ባለሥልጣኑ ገልጿል።

    እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበትን ይህንን የአየር ጥቃት ጋዛ ላይ መፈጸም የጀመረችው፣ ሐማስ በደቡባዊ ክፍሏ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ከ1400 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ ከተገደሉ በኋላ ነው።

  12. የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ሐማስን ነጻ "አውጪ ቡድን ነው" አሉ

    ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣዪብ ኤርዶዋን

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣዪብ ኤርዶዋን

    የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣዪብ ኤርዶዋን ፍልስጥኤማዊውን ቡድን ሐማስን 'ነጻ አውጪ' ሲሉ ጠሩ።

    ኤርዶዋን ዛሬ በአገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ሐማስ ነፍጥ ያነሳው የፍልስጥኤማውያንን ሕጋዊ መሬት ለማስመለስ እንጂ ሽብርተኛ ሆኖ አይደለም ብለዋል።

    ይህ ንግግራቸው እስራኤልን ክፉኛ እንደሚያስቆጣ ይጠበቃል።

    ሐማስ በአሜሪካ፣ በእስራኤል፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በዩናይትድ ኪንግደም ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ተፈርጇል።

    መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ሐማስ እስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ከጋዛ ድንበር አካባቢ የነበሩ በአብዛኞቹ ሲቪል የሆኑ 1400 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    ይህንንም ተከትሎ አስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ5500 በላይ ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    ኤርዶዋን ቁጭት እና ኃይል በተቀላቀለበት በዚህ ንግግራቸው የእስራኤል ጉብኝታቸውን እንደሰረዙም ገልጸዋል።

    ከዚህ ቀደም የኔታንያሁን እጅ "በበጎ መንፈስ ጨብጫለሁ፤ እሱ ግን የቱርክን መልካምነት ለእኩይ ዓላማ አውሎታል" ሲሉም አገራቸው ከእስራኤል ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ላልተገባ ተግባር ውሏል በማለት ትቸት አቅርበዋል።

    ኔታንያሁ እና ኤርዶዋን ባለፈው መስከረም ወር ኒው ዮርክ ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ተገናኝተው ነበር።

    በወቅቱ ግንኙነታቸው ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

  13. በባሕር ሰርገው ለመግባት የሞከሩ የሐማስ ዋናተኞችን መግደሉን የአስራኤል ጦር ገለጸ

    የሐማስ ጠላቂ ዋናተኞች ማክሰኞ ዕለት ወደ ግዛቷ ሰርገው ለመግባት ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፉን የእስራኤል ጦር በቪዲዮ አስደገፎ አስታወቀ።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እንደገለጸው ቢያንስ ሁለት የሐማስ ተዋጊዎች በሰሜን ጋዛ ሰርጥ በኩል ዚኪም አቅራቢያ በሚገኘው በጋዛ የባሕር ዳርቻ በኩል ወደ እስራኤል ለመግባት ሞክረዋል።

    የሐማስ ታጣቂዎች በጦር ጄቶች እና በእስራኤል የባሕር ኃይል ወታደሮች ጥቃት ደርሶባቸው ሕይወታቸው ማለፉንና “አሸባሪዎቹ ይገለገሉበት የነበረውን” የጦር መሳሪያ ማከማቻ ወደሙንም አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር በባሕር በኩል ሰርጎ የመግባት ሙከራው እንዴት እንደተፈጸመ አልገለጸም። ይፋ ያደረገው ቪዲዮም በባሕር ላይ የፈጸመውን ጥቃት ብቻ የሚያሳይ ነው።

    ጦሩ መረጃውን ይፋ ካደረገ በኋላ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ልዩ የጠላቂ ዋናተኛ አልባሳትን ያደረጉ እና ጠመንጃ ያነገቱ ሁለት ግለሰቦችን ምስል ቴሌግራም ላይ ለጥፏል።

  14. እስራኤል ለተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ ማርቲን ግሪፊትስ ቪዛ ከለከለች

    ማርቲን ግሪፊትስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ማርቲን ግሪፊትስ

    የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ በአስራኤል እና በድርጀቱ መካከል ያለው ውዝግብ እየተባባሰ ባለበት ጊዜ፣ እስራኤል ለተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቪዛ ከለከለች።

    የድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስ ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ቪዛ ተከልክለዋል። በመንግሥታቱ ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ጊላድ ኤርዳን እርምጃው ተመድን ለመቅጣት መሆኑን ተናግረዋል።

    ማክሰኞ ምሽት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና በጋዛ ጦርነት ላይ ለመወያየት በተቀመጠው ስብሰባ ምክንያት ነበር በድርጅቱ እና በቴል አቪቭ መካከል ውዝግብ ተፈጠሯል።

    የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከ1400 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የሐማስ ጥቃት “ዝም ተብሎ የተፈጠረ” አይደለም ሲሉ እስራኤል “ለ56 ዓመታት በፍልስጥኤም ያደረገችውን ወረራ” በማመልከት ተናግረዋል።

    አስተያየቱን ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን “ለእንዲህ ዓይነቱ እልቂት ምንም ምክንያት መቅረብ የለበትም” ሲሉ ቁጣ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።

    አንቶኒዮ ጉተሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, አንቶኒዮ ጉተሬዝ

    "በየትኛው ዓለም ነው የምትኖረው?" ሲሉ ለጉተሬዝ ጥያቄ አቅርበዋል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ እንደሰረዙም አክለው ገልጸዋል።

    በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ጊላድ ኤርዳን “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለመምራት ብቁ አይደሉም” በማለት ጉተሬዝ ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

    ጉተሬዝ ኋላ ላይ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው “የፍልስጥኤማውያን ሕመም ሐማስ ላደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ምክንያት ሊሆን አይችልም፤ እንዲሁም በፍልስጥኤም ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን የጅምላ ቅጣትን ትክክል አያደርገውመ” ብለዋል።

    አሁን ደግሞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ቪዛ እንደምትከለክል እስራኤል አስታውቃለች።

    ለእስራኤሉ ሬዲዮ ሃሳባቸውን የሰጡት ኤርዳን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ማርቲን ግሪፊትስ ቪዛ መከልከላቸውን ተናግረዋል። "እነሱን የምናስተምርበት ጊዜ ደርሷል" ሲሉ ኤርዳን ገልጸዋል።

  15. የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሚገኘው ዃን ዩኒስ ትናትን ምሽት ያደረሰችውን ጥቃት የሚያሳይ ምስል ደርሶናል።

    ቴል አቪቭ በጥቃቱ ዒላማ ያደረገችው የሐማስ መሠረተ ልማቶችን መሆኑን አስታውቃለች።

    የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት
    የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት
    የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት
  16. ሶሪያ 8 ወታደሮቼ በእስራኤል ተገደሉብኝ አለች

    የእስራኤል ተዋጊ ጄት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሶሪያ 8 ወታደሮቿ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታወቀች።

    ዳራ በተባለው የሶሪያ ግዛት በተፈጸመው የአየር ጥቃት ተጨማሪ 7 ወታደሮች መቁሰላቸው ተገልጿል።

    የሶሪያ መንግሥት የዜና ወኪል ሳና እንዳለው ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት ረቡዕ ከእኩለ ለሊት በኋላ ነው።

    የእስራኤል ጦር የአየር ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ፤ በሶሪያ የአየር ጥቃት ዒላማ አድርጌ የነበረው ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ነው ብሏል።

    እስራኤል ጥቃቱን የፈጸመችው ከሶሪያ ሮኬቶች ከተተኮሱባት በኋላ ሮኬት እና ሞርታር ማስወንጨፊያዎችን መምታቷን አስታውቃለች።

  17. በጋዛ በአንድ ሌሊት 80 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው መንግሥት አስታወቀ

    እስራኤል ትላንት ምሽት በጋዛ ሰርጥ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት በትንሹ 80 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው መንግሥት አስታወቀ።

    የመንግሥት የሚዲያ ፅህፈት ቤት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ከ80 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩት መቁሰላቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

    ጥቅምት 7 የሐማስ ታጥቂዎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ የሚገኘው የታጣቂ ቡድን ዒላማ አድርጋ የአየር ድብደባ እየፈጸመች ነው።

    ከዚያ ወዲህ በጋዛ ከ5,800 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  18. የጋዛ ሆስፒታሎች የህክምና ክፍሎቻቸውን መዝጋት ጀመሩ

    ለሆስፒታሎች እርዳታ ቢደርስም እስካሁን ነዳጅ አላገኙም

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ለሆስፒታሎች እርዳታ ቢደርስም እስካሁን ነዳጅ አላገኙም

    በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች የሚያስፈልጋቸውን ነዳጅ ማግኘት ባለመቻላቸው ከድንገተኛ ክፍሎቻቸው በስተቀር ሁሉንም የህክምና ክፍሎቻቸውን ዘጉ።

    "ያላቸውን ነዳጅ ለመቆጠብ በማሰብ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ክፍሎች መዘጋታቸውን" የቢቢሲው ባልደረባ ሩሽዲ አቡአሉፍ ተናግሯል።

    እንደ የኩላሊት እጥበት ያሉ ህክምናዎች ላይ ትኩረት መደረጉን በመግለጽ "የህይወት በማዳን ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆነዋል" ሲል ገልጿል።

    በጣም አስከፊ ሁኔታ መኖሩንም አክሏል።

  19. አውስትራሊያ ወታደሮቿን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ላከች

    አውስትራሊያ ተጨማሪ ወታደራዊ ኃይሏን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያሰማራች ነው።

    የአገሪቱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪቻርድ ማርለስ እንዳሉት ለጥንቃቄ በሚል ሁለት አውሮፕላኖች እና ወታደሮችን ወደ ቀጠናው ልከዋል።

    ማርለስ ምን ያህል ወታደሮች እንደሚላኩ ባይናገሩም "ትልቅ ቁጥር" መሆኑን ግን አረጋግጠዋል።

  20. የዮርዳኖስ ንግሥት ራኒያ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃንን ተቹ

    ንግሥት ራኒያ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃንን ተቹ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ንግሥት ራኒያ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃንን ተቹ

    የዮርዳኖስ ንግሥት ራኒያ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከእስራኤል እና ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ የፍልስጤም እና የአይሁድ ማህበረሰቦችን ጉዳይ በአንድ ዓይን አይዘግቡትም ሲሉ ተችተዋል።

    ማክሰኞ ከአማን በተለቀቀው የሲኤንኤን ቃለ ምልልስ ላይ "ዛሬ ዓለም ላይ የሚታየው በአንድ ዓይን ያለመዘገብ ነገር አሳዛኝ ነው። ጥቅምት 7 የተፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ ጠንከር ያለ ውግዘት ቢታይም አሁን እየሆነ ስላለው ነገር የሚሰማው ውግዘት በጣም ትንሽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

    “አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ጥሪ ለምን አልተደረገም? ዛሬም በሰው ልጆች ላይ አስደንጋጭ ስቃይ ሲደርስ እያየን ነው። ታዲያ ለምንድነው ትርክቱ ሁሌም ወደ እስራኤላውያን የሚያዘነብለው?"

    “ቤተሰብን፣ ሙሉ ቤተሰብን በጠመንጃ መግደል ስህተት እንደሆነ እየተነገረን ነው። ቤተሰቡን በአየር ጥቃት መግደል ግን ምንም አይደለም…. ይህ ለአረቡ ዓለም አስደንጋጭ ነው” ብለዋል።

    “በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የሰው ልጆች መከራ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው። ዓለም ግን የተኩስ አቁም ጥሪ እንኳን አያደርግም። ዝምታው በዝቷል"ሲሉ አክለዋል።