በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኮሮናቫይረስ፡ የዩኬ እዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ትሪሊዮን ተሻገረ

    አጠቃላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እዳ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ትሪሊዮን ፓውንድ መሻገሩ ተዘግበ።

    በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ የእዳው መጠን 2.004 ትሪሊዮን ፓውንድ የነበረ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ227 ቢሊዮን ጭማሪ ማሳየቱን ብሄራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮ ገልጿል።

    ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ሐምሌ ወር ላይ ብቻ 26.7 ቢሊየን ፓውንድ ተበድሯል።

  2. የዓለም ጤና ድርጅት እና ተመድ በአፍሪካ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ጠየቁ

    የዓለም ጤና ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንዲከፈቱ ጠየቁ።

    ድርጅቶቹ ትምህርት ቤቶች ለረዥም ጊዜ ዝግ ሆነው መቆየታቸው በታዳጊዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ በመጥቀስ መንግሥታት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በመውሰድ ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

    ተማሪዎች በቤት በመቆየታቸው ላልተፈለገ እርግዝና እና ለጥቃት ተጋላጭ ሆነዋል ብለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ህጻናት አድን ድርጅት በ39 የአፍሪካ አገራት ባካሄድነው የዳሰሳ ጥናት ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት የተደረጉት በ6 የአፍሪካ አገራት ብቻ ነው ብለዋል።

    አንዳንድ አገራት ደግሞ ትምህርት ቤቶች ክፍት ካደረጉ በኋላ የቫይረሱ ስርጭት በመጨመሩ ትምህርት ቤቶችን መልሰው ለመዝጋት መገደዳቸው ተጠቅሷል።

  3. ሞሮኮ በቱሪስት መዳረሻዎቿ ላይ ገደቦችን ጣለች

    ሞሮኮ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የጎብኚዎች መዳረሻ በሆኑት ካሳብላንካ እና ማራኬሽ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ጣለች።

    የሞሮኮ ባለስልጣናት ከዚህ ውሳኔ የደረሱት የጎብኚ መዳረሻ በሆኑ አከባቢዎች የቫይረሱ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎ ነው።

    በግዛቶቹ የሚገኙ ቡና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት በተወሰነላቸው ሰዓት ብቻ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። መናፈሻ ፓርኮች እና ባህር ዳርቻዎችም ይዘጋሉ።

    በሞሮኮ መዲና ራባት ደግሞ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

    መንግሥት የጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈጸም የአገሪቱ ፖሊስ ኃይል ታጥቆ ቅኝት ሲያደርግ ተስተውሏል።

    ሞሮኮ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ከ46 ሺህ ሰዎች በላይ ሰዎች የመዘገበች ሲሆን ከ740 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

  4. በስፔን እና ፈረንሳይ የኮሮናቫይረስ ስርጭት አገረሸ

    ከአውሮፓ አገራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ተጎድተው ከነበሩት መካከል ስፔን እና ፈረንሳይ ተጠቃሽ ናቸው።

    እነዚህ አገራት ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ቢቻላቸውም፤ አሁን ዳግመኛ ኮሮናቫይረስ በስፋት እየተሰራጨባቸው ይገኛል።

    ፈረንሳይ ባለፉት 24 ሰዓታት ከ4ሺህ 700 በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግኝታለች። ይህም ከግንቦት ወር ወዲህ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎች ሲገኙ የመጀመሪያው ነው።

    በተመሳሳይ በስፔንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

    በሁለቱም አገራት የቫይረሱ ስርጭት ዳግመኛ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆነው ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ተብሎ የተጣሉ ገደቦች እንዲነሱ መደረጋቸው እና ሰዎች ለሥራ እና ለጉብኝት ርቀው መጓዛቸው ነው ተብሏል።

    የዘርፉ ባለሙያዎች ልክ እንደ ስፓኒሽ ፍሉ ኮሮናቫይረስም በሁለተኛ ዙር በርካቶችን ሊያጠቃ እንሚችል እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

  5. እንኳን ወደ ቀጥታ ዘገባ ገጻችን በደህና መጡ

    የቀጥታ ዘገባ ገጻችንን በመጎብኘትዎ እናመሰግናለን።

    በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ከአገር ውስጥ እና ከውጪ የተገኙ ወቅታዊ መረጃዎችን እናቀርባለን።

    መልካም ቀን!