በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እንደምን አረፈዳችሁ

    የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባት ኢትዮጵያ በቀን ውስጥ በቀን ውስጥ በመቶዎች ብቻ በቫይረሱ ተይዘው ይገኝባት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ወደ ሺዎች ተሻግሯል።

    በትናንትናው ዕለት ብቻ 1 ሺህ 329 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 39 ሺህ 33 ደርሷል።

    ከነዚህም ውስጥ 14 ሺህ 480 ሲያገገግሙ አገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 662 መሆኑን የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እለታዊ መግለጫ ያስረዳል።

    ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያከናወነቻቸው የላብራቶሪ ምርመራዎች 736 ሺህ 904 ነው።

    ቢቢሲ አማርኛ ለባለፉት ስድስት ወራት እያደረግን እንዳለው የኮሮናቫይረስን አስመልክቶ የቀጥታ ዘገባችን እዚህ ታገኛላችሁ።

  2. ዴልታ ኤር ላይንስ በቅርቡ ወደ 50 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ በረራ ማድረግ እንደሚችል አስታወቀ።

    የአሜሪካው አየር መንገድ ዴልታ ኤር ላይንስ በቀጣይ ወራት ወደ 50 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ በረራ ማድረግ እንደሚችል አስታወቀ።

    ሬውተርስ እንደዘገበው ዴልታ መብረር ከሚጀምርባቸው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ መካከል ቶኪዮ፣ ሶል፣ ቤጂንግ እና ሻንጋይ ይገኙበታል ተብሏል።

    መጋቢት ወር ላይ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል የመንገደኞች በረራ መቋረጡ ይታወሳል። ዴልታም ወደ ሻንጋይ ሲበር ከሻንጋይ በኋላ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል።

    አየር መንገዱ ጨምሮ እንዳለው በረራው ሲጀመር የአውሮፕላኑ የመሃል መቀመጫዎች ባዶ ይሆናሉ።

    በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች ሲመለሱ ተጓዦች ከፍተኛ ገንዘብ ተጠይቀዋል።

  3. ከ110 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ለቤታቸው የበቁት አዛውንት

    የ65 ዓመቱ አዛውንት በከሮናቫይረስ ተይዘው ከ110 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ለቤታቸው በቅተዋል።

    ሚክ ፒኬሪንግ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ለቤቴ መብቃቴ ትልቅ እረፍት ሆኖኛል ብለዋል።

    ሚያዚያ ወር ላይ በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ የሚያስታውሱት ሚክ ከባድ እና አስጨናቂ ወራት በሆስፒታል ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

    አዛውንቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኩላሊታቸው እና ሳምባቸው ላይ ጉዳት ማጋጠሙን ተናግረው፤ "መልዕክቴም እራሳችሁን ጠብቁ የሚል ነው" ብለዋል።

    ባለቤታቸው ፓትሲ ሃኪሞች "ባለቤቴ ላያገግም እንደሚችል ሲነግሩኝ እጅግ ፈርቼ ነበረ" ብለዋል።

    "ሰዎች የፊት እና አፍንጫ መሸፈኛ በስነ-ስርዓት እና ሁሌም አድርገው መመልከት እፈልጋለሁ" ብለዋል ፓትሲ።

  4. ''ኮሮናቫይረስ ለዘላለም አብሮን ይቆያል'' ተመራማሪ

    ኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም የሁልጊዜም እውነታ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል አንድ እውቅ የእንግሊዝ ተመራማሪ ገልጸዋል።

    ተመራማሪው ፕሮፌሰር ማርክ ዋልፖርት አክለውም ሰዎች ምናልባትም ተከታታይ ክትባት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

    የእንግሊዝ መንግስት ሳይንስ ምክር ቤት አባል የሆኑት ተመራማሪው ''ልክ ፈንጣጣን ማጥፋት እንደተቻለው ሁሉ ኮቪድ-19ንም ማጥፋት የሚቻል አይመስለኝም'' ብለዋል።

    ተመራማሪው አክለውም ''ይሄ ቫይረስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እድሜ ልካችን አብሮን ይቆያል፤ ምናልባትም ተደጋጋሚ ክትባት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል'' ብለዋል።

  5. ሕንድ በቀን 1 ሚሊዮን ሰዎችን መረመረች

    ሕንድ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለ1 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጓን የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር አስታወቀ።

    የአገሪቱ ባለስልጣናት በቀን 1 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመርመር ከፍተኛ ጥረት እና ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ 1 ሚሊዮን ህዝብ የመረመረችው ሕንድ ከ69ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።

    ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ወደ 3 ሚሊዮን አቅርቧል።

    ከሰሞኑ ሒንዱዎች እያከበሩ የሚገኙት ፌስቲቫል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ያደረገ መሆኑ ተነግሯል።

    ሕንድ ከአሜሪካ እና ብራዚል በመቀጠል በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት አገር ነች።

    በሟቾች ረገድ ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አሜሪካ፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

  6. ሌባኖስ ከቤይሩቱ ፍንዳታ በኋላ የእንቅስቃሴ ገደብ ልትጥል ነው

    ሌባኖስ ከቤይሩቱ ፍንዳታ በኋላ የጨመረውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ልትጥል ነው።

    የገበያ ማዕከሎችን ጨምሮ የግብይት ስፍራዎች፣ የአካል ብቃት ማዘወተሪያ ማዕከሎች፣ መዋኛ ገንዳዎች ከትናንት ጀምሮ ዝግ የተደረጉ ሲሆን ሰዓት እላፊም ታውጇል።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቀን ከ450 በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እየተገኙ ነው።

    የሌባኖስ ባላደራ መንግሥት የጤና ሚንስትር የሆኑት ሃማድ ሃሰን በአገሪቱ የሚገኙ የሆስፒታል አልጋዎች በፍጥነት በታማሚዎች እየተያዙ ይገኛሉ ብለዋል።

    የቤይሩቱ ፍንዳታ በመዲናዋ የሚገኙ ሆስፒታሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ይታወሳል።

    ከዚህ በተጫማሪ ለፍንዳታው የመንግሥትን ቸልተኝነት ተጠያቂ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌባኖሳውያን ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል።

  7. ''ኮሮናቫይረስ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሊጠፋ ይችላል'' ደ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

  8. ደቡብ ኮሪያ ከወራት በኋላ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን አገኘች

    ደቡብ ኮሪያ ከወራት በኋላ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን አገኘች።

    ደቡብ ኮሪያ በአንድ ቀን ብቻ 324 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ይህም ከመጋቢት ወር በኋላ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

    ምንም እንኳን አገሪቱ መጀመሪያ አካባቢ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ብትሞካሽም አሁን ላይ ስርጭቱ በድጋሚ እያገረሸ ይገኛል።

    አሁን በዋና ከተማዋ ሶል የቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ናቸው ከተባሉት መካከል አንድ ቤተ-ክርስቲያ እና ሙዚያም እንዲዘጉ ተደርገዋል።

    ከቤተ-ክርስቲያኗ አባላት እና ከአባላቱ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ሙዚየሙን የጎበኙ ሰዎች እራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ተጠይቀዋል።

  9. ኮሮናቫይረስ በአውሮፓ አገራት ዳግም እያገረሸ ይገኛል

    ኮሮናቫይረስ በአውሮፓ አገራት ዳግም እያገረሸ ይገኛል።

    ስፔን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት ቫይረሱ እንደገና እያንሰራራ መሆኑን እየገለጹ ነው።

    በሁለቱም አገራት የቫይረሱ ስርጭት ዳግመኛ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆነው ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ተብሎ የተጣሉ ገደቦች እንዲነሱ መደረጋቸው እና ሰዎች ለሥራ እና ለጉብኝት ርቀው መጓዛቸው ነው ተብሏል።

    የዘርፉ ባለሙያዎች ልክ እንደ ስፓኒሽ ፍሉ ኮሮናቫይረስም በሁለተኛ ዙር በርካቶችን ሊያጠቃ እንሚችል እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

    ፖላንድ እና ስሎቫኪያ አርብ ዕለት ከፍተኛ የተባለ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግበዋል።

    ፖላንድ 903 ሰዎች ስታገኝ ስሎቫኪያ ደግሞ 123 በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።

  10. በሜክሲኮ ለወረርሽኙ ተገቢ ትኩረት አልተሰጠም ተባለ

    የዓለም ጤና ድርጅት በሜክሲኮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በቂ ትኩረት አልተሰጠም አለ።

    የድርጅቱ የድንገተኛ የጤና ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ማይክ ራይን በሜክሲኮ ያለው የወረርሽኙ ስርጭት ''ተገቢውን ትኩረት አላገኘም'' በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ዶ/ር ማይክ ራይን እንዳሉት በሜክሲኮ ከ100 ሺህ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚደረግላቸው ለሶስት ሰዎች ብቻ ነው። ይህ አሃዝ ከሜክሲኮ ጎረቤት አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር 150 ሰዎች ምርመራ ይደረጋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ሜክሲኮ ከዓለም አገራት በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፉባቸው አገራት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ እስካሁን በሜክሲኮ ከ60 ሺህ ሰዎች በላይ ሕይወታቸው አልፏል።

  11. እንዴት አደራችሁ?

    እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    ይህ የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ነው። እንኳን በደህና መጣችሁ!

    በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የአገር ውስጥ እና የውጪ ወቅታዊ መረጃዎችን እናቀርባለን።

    መልካም ቀን!

  12. በዛሬው ዕለት 1 ሺህ 829 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ የ17 ሰዎች ሕይወት አለፈ

    ባለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ ከተደረገላቸው 23 ሺህ 035 ሰዎች መካከል1 ሺህ 829 በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ማምሻውን ባወጡት የኮሮናቫይረስ እለታዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት በኮቪድ-19 ምከንያት የ17 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

    መግለጫው በተጨማሪ 377 ሰዎች ማገገማቸውን የገለፀ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 13 ሺህ 913 ማድረሱ አመልክቷል።

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 37 ሺህ 665 የደረሰ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር 637 መድረሱ ተገልጿል።

  13. ሞዛምቢክ የውጭ አገራት የጉዞ ገደብን አነሳች

    የሞዛምቢክ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ተጥሎ የነበረውን የውጪ አገር ጉዞ ገደብ ማንሳቱን ገለፀ።

    ከአሁን በኋላ ሞዛምቢካውያን ከባህር ማዶ ወደ አገራቸው መምጣት ወደ ተለያዩ አገራትም መጓዝ ይችላሉ ተብሏል። የአገር ውስጥ ሚንስቴር ባለስልጣናት እንዳስታወቁት፣ ሞዛምቢካውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጪ አገር ዜጎችም ከአገር መውጣትም ሆነ መግባት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

    ገደቡ ተጥሎ በነበረበት ወራት ባህር ማዶ ሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከአገር ውስጥ ሚኒስቴር ፈቃድ በመጠየቅ መሄድ ይችሉ ነበር።

    የሞዛምቢክ አየር መንገድም ከሚቀጥለው ማክሰኞ ጀምሮ ወደ ፖርቹጋል ዋና ከተማ ሊዝበን በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል። አየር መንገዱ ከዚህ በፊት የዓለም አቀፍ በረራውን ለመጀመር ሶስት ጊዜ አቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ሲተላለፍ ቆይቷል።

  14. በሕንድ ዴልሂ በኮቪድ-19 ከተጠቁት መካከል የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው

  15. በኬንያ በዓመቱ መጨረሻ የሚወለዱ ህፃናት ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተባለ

    የኬንያ ባለሥልጣናት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በተያዘው የጎርጎሳውያኑ ዓመት መጨረሻ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር እንደሚጨምርና ለዚያም እየተዘጋጁ መሆኑን ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ ጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።

    በአገሪቷ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከመጋቢት ወር ጀምሮ የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ ሴቶች ቁጥር ከባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 10 በመቶ መጨመሩን ጋዜጣው አክሏል።

    ለውልደት መጠኑ መጨመር የተሰጠ ማብራሪያ ባይኖርም፤ ባለሙያዎች ግን የጤና ተቋማት ወረርሽኙ ላይ ትኩረት በማድረጋቸውና የእርግዝና መከላከያ አገልግሎት ላይ ችላ ስላሉ ነው ይላሉ።

    የኬንያ መንግሥት መጋቢት ወር ላይ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ በአገሪቷ የምሽት የሰዓት እላፊ የጣለ ሲሆን ሰራተኞችም ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ አሰሪዎችን ሲያበረታታ ነበር።

    ከዋና መዲናዋ ናይሮቢ እንዲሁም ከሁለት የባህር ዳርቻ ግዛቶች መውጣትም ሆነ መግባት በጊዜያዊነት ተከልክሎ ነበር።

    በባለፈው ዓመት የሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት የኬንያ ሕዝብ ብዛት 47.5 ሚሊየን ነው።

  16. ፖላንድ በአንድ ቀን ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዘገበች

    ፖላንድ ባለፉት 24 ሰዓታት 903 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የመዘገበች ሲሆን የ13 ሰዎች ሕይወትም አልፏል። ይህም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል።

    ምንም እንኳን በቫይረሱ በተጠቁ አካባቢዎች የተለየ ውሳኔ ሊኖር የሚችል ቢሆንም አገሪቷ በመስከረም ወር ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ማቀዷን የጤና ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩም ሰዎች ከእረፍት እና እንደ ሰርግ ካሉ ቤተሰባዊ ክንውኖች እየተመለሱ በመሆኑ ነው ብለዋል ቃለ አቀባዩ።

    ፖላንድ በ19ኙ ወረዳዎቿ ሕዝብ በሚገለገልባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አስገዳጅነትን ጨምሮ እንደገና ገደቦችን ጥላለች።

    እስካሁን በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 60 ሺህ 281 ሲሆን 1 ሺህ 938 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሞተዋል።

    ይህ ቁጥር ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገራት ጋር ሲነፃፀር ግን ዝቅተኛ ነው። በፖላንድ ከ1 ሚሊዮን ነዋሪዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ የሚያንስ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥርም በ12 እጥፍ ዝቅ ይላል።

  17. ሆንግ ኮንግ መላው ሕዝቧን በነፃ ልትመረምር ነው

    ሆንግ ኮንግ ለ7.4 ሚሊየን ነዋሪዎቿ በነፃ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ልታደርግ እንደሆነ አስታወቀች። መሪዋ ካሬ ላም እንዳሉት ምርመራው መስከረም አንድ የሚጀመር ሲሆን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል።

    በሆንግ ኮንግ ምንም እንኳን በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ብለዋል መሪዋ ።

    ይሁን እንጂ ከቻይና በመጡ 60 አባላት ባሉት ቡድን በመታገዝ እየተከናወኑ ባሉ ምርመራዎች ምን ያህል ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ የታወቀ ነገር የለም።

    ቤጂንግ ሰኔ ወር ላይ አዲስ ብሔራዊ የፀጥታ ሕግ በሆንግ ሆንግ ላይ ከጣለች በኋላ በሆንግ ሆንግ በሚገኙ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ቡድኖችና በቻይና መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ነው።

    በርካቶችም ይህ ሕግ ነፃነትን ይሸረሽራል ሲሉ ተችተውታል።

    ይደረጋል የተባለውን ሰፊ ምርመራ ተከትሎም አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ቻይና ምርመራውን ተንተርሳ ለስለላ የዘረ መል ናሙና ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት አንስተዋል።

    መሪዋ ኬሬ ግን አርብ ዕለት "ሀሰተኛ ክስና ስም ማጥፋት ነው" ሲሉ አጣጥለውታል። የተወሰደው ናሙና ከምርመራው በኋላ ይወገዳልም ብለዋል።

    በሆንግ ኮንግ ከጥር ወር ጀምሮ ከ4 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የ75 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

    ባለፈው ወር መሪዋ የሆንግ ኮንግ የምክር ቤት ምርጫ በወረርሽኙ ሳቢያ በአንድ ዓመት ሊራዘም እንደሚችል ተናግረው ነበር።

    ሆኖም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ በመሆኑ የተራዘመው ጊዜው ረዥም ነው በማለት በርካታ ትችቶች ተሰንዝረዋል።

    አርብ ዕለት በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 27 ብቻ ነው።

  18. በኬንያ ከ300 በላይ ዶክተሮች አድማ መምታት ጀመሩ

    በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ የሕዝብ ሆስፒታል የሚሰሩ ከ300 በላይ ዶክተሮች አድማ መምታት መጀመራቸው ተነገረ።

    የጤና ባለሙያዎቹ አድማ መምታት የጀመሩት የተሻለ ክፍያና የቫይረሱ መከላከያ የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦትን ጨምሮ ምቹ የሥራ ቦታ ሁኔታን ለመጠየቅ ነው።

    ዶክተሮቹ የጤና አገልግሎት ጉዳይን በተመለከተ በመዲናዋ ኃላፊነት የተጣለበትን የመንግሥት አካል እስካሁን መታገሳቸውን ገልፀዋል።

    አስተባባሪው ዶ/ር ቱራኒካ ኩዋጊራ የጤና ባለሙያዎች ባላቸው ነገር ሲያገለግሉ መቆየታቸውን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

    ዶክተሮቹ አጠቃላይ የጤና ሽፋን እና ኮቪድ-19 ሕሙማንን የሚያክሙበት ጥራት ያለው የበሽታ መከላከያ የሕክምና ግብዓት ጠይቀዋል።

    በኬንያ ዶክተሮች አድማ ሲመቱ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም ። ከዚህ በፊትም ምቹ የሥራ ሁኔታ እና የተሻለ ክፍያ በመጠየቅ አድማ መትተው ነበር።

    ዶክተሮች፣ ነርሶች እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎቻቸውን የሚመልስላቸው የጤና አገልግሎት ኮሚሽን እንዲቋቋም ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ይህ ግን ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

    በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር የሚገኘው በዋና መዲናዋ ናይሮቢ ነው።

    በኬንያ በቫይረሱ ከተያዙ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች 700 የሚጠጉት የጤና ሰራተኞች ናቸው።

    በርካታ የጤና ሰራተኞችም በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

  19. የአየርላንድ ሚንስትር ክልከላዎችን በመተላለፋቸው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ

    የአየርላንድ ግብርና ሚንስትር ዳራ ካሌረይ የኮሮናቫይረስ ክልከላን በመተላለፍ 80 ሰዎች በታደሙት የእራት ግብዣ ላይ ከተገኙ በኋላ በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው ለቀዋል።

    የአርላንድ ጠቅላይ ሚንሰትርም የግብርና ሚንስትሩን የሥራ ልልቀቅ ጥያቄን ተቀብለዋል። "ውሳኔያቸው ስህተት ነበር" በማለት የግብርና ሚንሰትሩ በእራት ግብዣው ላይ መገኘታቸውን ኮንነዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ የአገራቸው ዜጎች የኮሮናቫይረስ ክልከላን ለማክበር ብዙ መሰዋእትነት ከፍለዋል ያሉ ሲሆን፤ የመንግሥት ባለስልጣናትም ክልከላዎቹን ማክበር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

    በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣን የተነሱት ዳራ በትዊተር ገጻቸው ላይ ስህታቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል።

    አየርላንድ የቫይረሱ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎ ከ6 ሰዎች በላይ በአንድ ቤት ውስጥ መሰባሰብ አይችሉም ስትል ጥብቅ መመሪያ አስተላልፋለች።

  20. በኒው ዚላንድ በለይቶ ማቆያ የሚገኝ ጓደኛውን ያቀፈው በእስራት ተቀጣ

    የ33 ዓመቱ የኒው ዚላንድ ዜጋ የኮሮናቫይረስ ክልከላን በመተላለፉ 6 ሳምንታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተበየነበት።

    እንደ ዘ ኒው ዚላንድ ሄራልድ ዘገባ ከሆነ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጄሲ ዎልሽ የተባለው ግለሰብ ከአውስትራሊያ መልስ ወደ ለይቶ ማቆያ የገባውን ጓደኛውን ሊጎበኝ ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል አምርቷል።

    ጄሲ ዎልሽ ወደ ለይቶ ማቆያ መሄዱ ሳይበቃው እራሱን ለይቶ የሚገኘውን ጓደኛውን በማቀፍ ሰላምታ ሰጥቷል ብለዋል ዳኛው።

    የዎልሽ ጠበቃ ደንበኛቸው በድርጊቱ መጸጸቱን እና "የፈጸመው ተግባር ከእሱ የማይጠበቅ መሆኑን አምኗል" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ዳኛ ተናግረዋል።

    በርካታ አገራት የቫይረሱ ስርጭት ባስጨነቃቸው በዚህ ወቅት ኒው ዚላንድ የበሽታውን ስርጭት በቁጥጥር ሥር በማዋል አድናቆትን አትርፋ ነበር።

    ይሁን እንጂ በዚህ ወር ጀመሪያ ላይ ከ102 ቀናት በኋላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።