በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ተቃረበ

የቀጥታ ሽፋን

  1. "ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል ይችላል" የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት

  2. በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 49 ሺህ 654 ደረሰ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 19 ሺህ 194 የናሙና ምርመራ፤ 1514 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱ ተረጋገጠ።

    የጤና ሚንስትር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ ባወጡት መግለጫ መሠረት አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 49 ሺህ 654 ደርሰዋል።

    በአንድ ቀን 12 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች 770 ደርሰዋል።

    701 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመው፤ አጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 18 ሺህ 116 ሆኗል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን 869 ሺህ 430 የናሙና ምርመራ ተደርጓል።

  3. በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 'ፊልድ' ሆስፒታል ጳጉሜ 5 ይጀምራል ተባለ

    በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የተሰራው የኮቪድ-19 ፊልድ ሆስፒታል ጳጉሜ 5/2012 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የጤና ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ አስታወቀ።

    ሆስፒታሉ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥር በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና በዓለም ምግብ ፕሮግራምና የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ነው የተሰራው።

    በዛሬው እለትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ደመቀ መኮንን ከጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር በመሆን ሆስፒታሉን ጎብኝተዋል።

    ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 200 አልጋዎችን መያዝ እንደሚችልም ተገልጿል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት ከዕለት ተዕለት እየጨመረ ነው።

    በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የሚገቡ እንዲሁም በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በአስጊ ሁኔታ ከፍ ብሏል።

    በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀው የጽኑ ሕሙማን ክፍልም እየሞላ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው ጫኔ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

    የበሽታውን ሥርጭትም ለመግታት በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ተለያዩ ዘመቻዎች እየተደረጉ ነው።

  4. በደቡብ ኮርያ ለህሙማን አልጋ እንዳይጠፋ ተሰግቷል

    ደቡብ ኮርያ ውስጥ በአንድ ቀን 300 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ አገሪቱ ለህሙማን አልጋ እንዳታጣ ተሰግቷል።

    ባለፈው አርብ በመዲናዋ ስዑል ከ22 በመቶ አልጋዎች ያልተያዙት 4.5 በመቶው ብቻ ነበሩ።

    የሕብረተሰብ ጤና ኃላፊው ዮን ታሆ እንዳሉት፤ ለጽኑ ህሙማን ወደ 15 አልጋዎች ብቻ ናቸው የቀሩት።

    በጠና የታመሙ ብዙ ሰዎች ሆስፒታል አልጋ በመያዛቸው ምክንያት ሕክምና መስጫ መጣበባቸውን አክለዋል።

    በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ ክርስቲያኖች፣ የምሽት ክበቦች እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎች ተዘግተዋል።

    ከነገ ጀምሮ ምግብ ቤቶች ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ የመስተንግዶ አገልግሎት ያቆማሉ።

  5. በበርሊን የኮሮናቫይረስ ገደብ ተቃዋሚዎች አደባባይ እየወጡ ነው

    በበርሊን የኮቪድ- 19 ሥርጭትን ለመግታት የተጣሉ ገደቦችን የሚቃወሙ ሰዎች አደባባይ እየወጡ መሆኑ ተገለፀ።

    የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች በሰልፉ ላይ 22 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚገኙ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

    ከበርካታ ሳምንታት በፊት የተካሄደው ተመሳሳይ ተቃውሞም የፀረ ክትባት ዘመቻ አቀንቃኞችን፣ አወዛጋቢ ፅንሰ ሃሳብ አመንጭዎችን እና ነፃ - ሐሳብ አንሸራሻሪዎችን መሳብ ችሎ ነበር።

    ይሁን እንጅ ተቃዋሚዎቹ የጥንቃቄ ሕጎችን ሆነ ብለው በመጣሳቸው ሰልፉ ተበትኗል።

    አሁን የሚካሄደውን ሰልፍ ተከትሎም የበርሊን ባለሥልጣናት ሰልፈኞቹ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አይችሉም በሚል እንዳይካሄድ እገዳ ጥለው ነበር።

    ይሁን እንጅ ፍርድ ቤት ተቃዋሚዎች ሆነ ብለው አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ ሕግን እንደሚጥሱ የሚያመላክት ነገር የለም በማለት የአስተባባሪዎቹን ሐሳብ ተቀብሏል።

    በሥፍራውም 3 ሺህ ፖሊሶች ተሰማርተዋል። ሕግ የሚጣስ ከሆነም ሰልፉን በፍጥነት እንደሚበትኑ ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።

    በጀርመን በሌሎች የአውሮፓ አገራት እንደታየው ወረርሽኙ ባይስፋፋም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ግን ጭማሬ አሳይቷል። ከባለፈው ሚያዚያ ወር ወዲህ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ሆኗል።

  6. በዓለማችን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች 837 ሺህ 559 ደርሰዋል

    በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሐዝ መሠረት፤ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 24 ሚሊዮን 758 ሺህ 970 ደርሷል።

    837 ሺህ 559 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሞተዋል።

    ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ዜናዎችን እንመልከት፦

    ·ጀርመን- ዛሬ በበርሊን የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

    ·ፈረንሳይ- በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

    ·ደቡብ ኮርያ- አንድ ጥናት ልጆች አፍንጫቸው ላይ ቫይረሱን እስከ ሦስት ሳምንት ይዘው እንደሚቆዩ አሳይቷል።

    ·ዩናይትድ ኪንግደም- ሾልኮ የወጣ የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው በቀጣይ ክረምት ነገሮች ከተባባሱ 85,000 ሰዎች እንደሚሞቱ ያሳያል።

  7. ኮቪድ -19፡ ልጆች ኮሮናቫይረስን ያስተላልፋሉ?

    ደቡብ ኮርያ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ልጆች ኮሮናቫይረስን አፍንጫቸው ላይ ይዘው እስከ ሦስት ሳምንታት መቆየት ይችላሉ።

    ከዚህ ቀደም የተሠሩ ጥናቶች፤ በርካታ ልጆች መጠነኛ የበሽታውን ምልክት እንደሚያሳዩ ወይም እስከነጭራሹ ምልክት እንደማይታይባቸው ይጠቁማሉ።

    እነዚህ ግኝቶች ልጆች ምን ያህል በሽታውን ያሰራጫሉ? ለሚለውና እስካሁን ግልጽ ምላሽ ላልተገኘለት ጉዳይ ፍንጭ ይሰጣሉ።

    ለወራት እንቅስቃሴ አቁመው በነበሩ አገሮች ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው። አካላዊ ርቀትና ንጽህናን መጠበቅ መዘንጋት እንደሌለበትም ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

    ኮቪድ-19 እና ልጆችን በተመለከተ ሦስት ዋና ጥያቄዎች እንዳሉ የሚናገሩት የሮያል ኮሌጅ ፕሮፌሰር ራሰል ቪነር ናቸው። የሚከተሉት ጥያቄዎቻቸው ናቸው፦ ተጨማሪ ለማንበብ ኮቪድ -19፡ ልጆች ኮሮናቫይረስን ያስተላልፋሉ?

  8. በፈረንሳይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

    በፈረንሳይ ከመጋቢት ወዲህ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

    ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በአገሪቷ በድጋሜ እንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚችል ተናግረዋል።

    አርብ እለት ብቻ ተጨማሪ 7 ሺህ 379 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን በአጠቃላይ በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 267 ሺህ 077 አድርሶታል።

    አርብ እለት የተመዘገበው ቁጥርም ከመጋቢት ወር ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል።

    በመጀመሪያው ዙር ወረርሽኝ ወቅት የተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር 7 ሺህ 578 ነበር። ኮቪድ -19 ፡ በፈረንሳይ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

  9. የነሐሴ 23/2012 ዓ.ም. የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ

    እንደምን አረፈዳችሁ የተከበራችሁ ወዳጆቻችን?

    ቢቢሲ አማርኛ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ኮቪድ-19ን የተመለከቱ ዜናዎችን ወደ እናንተ ማድረሱን ይቀጥላል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ነው። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርምለሳምንታት በቀነሰባቸው የአውሮፓ አገራትም ቫይረሱ እንደገና እያገረሸ ነው። አንዳንዶች የተለያዩ ገደቦችን በድጋሜ እየጣሉ ነው።

    በአገራችንም በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ሥርጭቱን ለመግታትም በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ዘመቻዎች እየተከናወኑ ነው።

    ጥንቃቄ አይለየን መልዕክታችን ነው።

  10. በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 850 ሺህ 236 ናሙናዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸዋል

    የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማምሻውን ባወጡት የኮሮናቫይረስ ዕለታዊ ሪፖርት 1733 ሰዎች ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን ገለፁ።

    በመግለጫው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ18,766 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መደረጉን ተገለፆ ከእነዚህ መካከል 1,733 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተነግሯል።

    ይህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 48,140 አድርሶታል።

    ባለፈት 24 ሰዓታት ውስጥ 13 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ሲያልፍ እስከ ዛሬ ድረስ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 586 ደርሷል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 586 ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 17,415 መድረሱን እለታዊ ሪፖርቱ ያሳያል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 850 ሺህ 236 ናሙናዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸዋል

  11. የ2013 የትምህርት ዘመንን ለማስጀመር ምን እየተሰራ ነው?

  12. በበርሊን የኮሮናቫይረስ ሕጎችን በመቃወም ሰልፍ ሊካሄድ ነው

    በጀርመን መዲና በርሊን የሚገኝ ፍርድ ቤት የኮሮናቫይረስ ሕጎችን በመቃወም ሊካሄድ የነበረ ሰልፍ ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ አነሳ።

    ፍርድ ቤቱ ሰልፉ አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉ ቅዳሜ መካሄድ ይችላል ብሏል።

    ጀርመን ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየጨመረ ቢሆንም፤ ሰልፉ ላይ ወደ አንድ ሺህ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በሳምንቱ መባቻ ላይ ሰልፉ ላይ ክልከላ እንደሚጣል የከተማ መስተዳድሩ አስታውቆ ነበር።

    ሰልፈኞች ግን ሐሳባችንን በነፃነት የመግለጽ መብታችን ተገደበ ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

    ነሐሴ መግቢያ ላይ በርሊን ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር።

    ቀኝ ዘመም የመብት ተሟጋቾች እና ኮቪድ-19 እውነተኛ ህመም አይደለም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ነበሩ ሰልፉን የተካፈሉት። ኋላ ላይ ፖሊስ ሰልፈኞችን በትኗል።

  13. የኬንያ አየር መንገድ የ133 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ገጠመው

    የኬንያ አየር መንገድ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከታክስ በፊት የ133 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው አስታወቀ።

    ኪሳራው የገጠመው በኮቪድ-19 ሳቢያ ሲሆን፤ ከወረርሽኙ በፊትም እየተንገታገተ ነበር።

    ዘንድሮ ከአምና አንጻር፤ ከጥር እስከ ሰኔ ድረስ የተጓዞች ቁጥር 56 በመቶ መቀነሱን አየር መንገዱ አስታውቋል።

    አየር መንገዱ ለማገገም ዘለግ ያለ ጊዜ እንደሚወስድበትም ለባለ ሀብቶች ገልጸዋል። በረራ እንዲሁም ሠራተኞችም ቀንሷል።

  14. ከኮሮናቫይረስ የዳነው ሰው ዳግም በወረርሽኙ ተያዘ

  15. “ማስክ አማራ- ሕዝብን የማዳን ዘመቻ” ዛሬ ተጀመረ

    “ማስክ አማራ - ሕዝብን የማዳን ዘመቻ” የተሰኘው ኮሮናቫይረስን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ ዛሬ በባህር ዳር ተጀምሯል።

    ከነሐሴ 22 እስከ 30፣ 2012 ዓ. ም. በሚቆየው እና በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሚተገበረው ዘመቻ ሕብረተሰቡ መቶ በመቶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርግ ለማነሳሳት የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ዘመቻው መጀመሩ ተገልጾ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለተግባራዊነቱ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠይቋል።

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያላደረገ ሰው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለማሕብረሰቡም ስጋት በመሆኑ ጭንብል ያለበሰ ሰው መንቀሳቀስ እና በየትኛውም መንገድ ማለፍ ከዛሬ ጀምሮ እንደ ተከለከለ ተገልጿል።

    ዘመቻው በመንግሥትና በግል ተቋማት፣ በሐይማኖት ስፍራዎች፣ በንግድ እና በገበያ ማዕከላትና በትራንስፖርት ቦታዎችም ተግበራዊ ይሆናል።

    ዘመቻው እስከ ነሐሴ መጨረሻ የሚቆይ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን ኮሮናቫይረስን መቆጣጠር እስከሚቻልበት ወቅት ይሆናል ተብሏል።

    የፀጥታ አካላትም ለዘመቻው ስኬታማነት ከዛሬ ጀምሮ ሕግ የማስከበር ተልዕኳቸውን ይወጣሉ ተብሏል።

    ከነሐሴ 1፣ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረ የምርመራ ዘመቻ በአማራ ክልል እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ ናሙናዎች ሲመረመሩ፣ በክልሉ የሚገኙ የምርመራ ላብራቶሪዎች ቁጥርም 10 ደርሷል።

  16. በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ20 በላይ ተለማማጅ ሐኪሞች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

  17. ከእስር የተለቀቀው ኬንያዊው ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ እንደሚቆይ ተገለፀ

    በቅርቡ ከእስር የተለቀቀው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በኢትዮጵያ ከጓደኞቹ ጋር መቆየትን እንደመረጠ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረ ተቃውሞ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጀዋር መሐመድ ቤት ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል።

    በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጣልቃ ገብነት ከእስር የተለቀቀውም በያዝነው ወር ነው።

    ጋዜጠኛው በኮሮናቫይረስ ከተያዘ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኝ ለይቶ ማቆያ ተወስዶ፤ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ካሳለፈ በኋላ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ በመረጋጋጡ ከማዕከሉ መውጣቱን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ገልጿል።

    ጋዜጠኛው ለ'ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ' በታተመው ደብዳቤው ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ኬንያ ያሉ ቤተሰቦቹን እንዳላየ ተናግሮ ነበር።

  18. ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ንግግር አደረጉ

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚደንት እጩነታቸውን በይፋ ከተቀበሉ በኋላ ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች በዋይት ሃውስ ንግግር ማድረጋቸው ተነገረ።

    በፕሮግራሙ ላይ ታዳሚዎቹ ተቀራርበው መቀመጣቸውንና ከተወሰኑት በቀር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረጋቸውን የወጡ ምስሎች ያሳያሉ።

    አሜሪካ ከፍተኛ በኮሮናቫይረስ የሞቱና የተያዙ ሰዎችን ቁጥር የመዘገበች ሲሆን ፤ ለወረርሽኙ በሰጡት ምላሽም ፕሬዚደንቱ ክፉኛ ይተቻሉ።

    ባደረጉት ንግግርም በአገሪቷ በቫይረሱ ሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ180 ሺህ በላይ መሆኑን ባይጠቅሱም፤ ኮቪድ-19ን ‘ረቂቅ ጠላት’ ሲሉ ገልፀውታል።

    አሜሪካ የዚህን በሽታ ክትባት ይህ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት፤ ምናልባትም በቅርቡ ልታመርት እንደምትችል ቃል ገብተዋል።

    ይሁን እንጂ ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነት ንግግር ‘ከፍተኛ ምኞት’ ነው፤ በምርምሮችና በምርመራዎች ላይም ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብለዋል።

    የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን፤ የሪፐብሊካን ብሔራዊ ኮንቬንሽን በዋይት ሃውስ ለተካሄደው ዝግጅት ትክክለኛውን ደንብ ለመከተል ከግል የሕክምና ኩባንያ ጋር መስራቱን ተናግሯል።

  19. የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ለኮቪድ-19 የሚፀለይበት ቀን አወጁ

    የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ዕለተ ቅዳሜ ለኮቪድ-19 የሚፀለይበት ‘ብሔራዊ የፀሎት ቀን’ እንዲሆን አወጁ።

    ፐሬዚደንቱ ይህንን ሃሳብ ያገኙት ‘ፈጣሪ ራዕይ ካሳየው’ አንድ ኡጋንዳዊ መሆኑን ተናግረዋል።

    “ፈጣሪ በሳይንሳዊ መንገድ ብሔራዊ የፀሎት ቀን እንዳዘጋጅ ለባለራዕዩ አሳይቶታል፤ በመሆኑም ፈጣሪ ከዚህ በሽታ እንዲጠብቀን ቅዳሜ [ማለትም በጎርጎሮሳዊያኑ ነሐሴ 29፣ 2020] ብሔራዊ የፀሎት ቀንና የሕዝብ በዓል እንዲሆን አውጃለሁ” ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

    ሙሴቪኒ አክለውም “በቤታችሁ አሊያም በግቢያችሁ ውስጥ ሆናችሁ ፀልዩ” ሲሉ በማህበራዊ ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    በኡጋንዳ እስካሁን 2ሺህ 679 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የ28 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

    መጋቢት ወር ላይ በአገሪቷ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ መንግሥት ጥብቅ ገደቦችን አስተላልፏል።

  20. በዩናይትድ ኪንግደም ከሰኔ አጋማሽ ወዲህ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

    በዩናይትድ ኪንግደም ባለፉት 24 ሰዓታት ተጨማሪ 1 ሺህ 522 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ይህም ከሰኔ ወር አጋማሽ ወዲህ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

    ረቡዕ ዕለት 1 ሺህ 048 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ዛሬ የተመዘገበው የ500 ጭማሪ ያህል አሳይቷል።

    ይሁን እንጂ ለቁጥሩ መጨመር ምክንያት የሚመረመረው ሰው ቁጥር ከፍ በማለቱ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።

    ተጨማሪ 12 ሰዎችም በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር 41 ሺህ 477 አድርሶታል።

    በዩናይትድ ኪንግደም ስታስቲክስ ኤጀንሲዎች የወጣ ሌላ መረጃ ደግሞ የሞት የምስክር ወረቀታቸው በኮቪድ- 19 እንደሞቱ የተገለፀ ሰዎች ቁጥር 57 ሺህ 200 እንደሆነ አመልክቷል።