በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በዛሬው ዕለት ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠውን 610 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው። ። ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ ካለባች ከተሞች ደግሞ ቀዳሚውን የምትይዘው ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ስትሆን፣ እስከ አሁን በዋና መዲናዋ ብቻ 10ሺህ 703 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባም ኮቪድ-19 ይበልጥ እየተሰራጨባቸው የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ቦሌ (1652 ሰዎች)፣ አዲስ ከተማ (1329 ሰዎች) እንዲሁም ጉለሌ (1308 ሰዎች) ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ለወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና እጅን መታጠብ ላይ መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዓለም እንዴት ዋለች? አሜሪካ፣ ስፔን ፣ ሰሜን ኮሪያ . . .

    ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እንደሚያሳው፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ16.2 ሚሊዮን አልፏል። ከ648 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ዘገባዎች የሚከተሉት ናቸው፦

    ·አሜሪካ- በከፍተኛ ደረጃ በወረርሽኙ የተጎዳችው አገር ስትሆን፤ በአጠቃላይ በዓለም በበሽታው ከተያዙ 20 በመቶው አሜሪካ ይገኛሉ።

    ·ሆንክ ኮንግ- በአንድ ቀን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀድሞ ከተመዘገበው በላይ ሆኗል። በሽታው ማኅበረሰቡ ውስጥ የበለጠ እንዳይሰራጭ፤ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተግባራዊ እየተደረጉም ነው።

    ·ቬትናም- ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ውጪ አገር ዜጎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተከትሎ፤ ዳ ኖግ ወደተባለችው ከተማ ጎብኚዎች እንዳይገቡ ተከልክሏል።

    ·ስፔን- አዲስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ተለይተዋል። ጎብኚዎች ደህንነት ተሰምቷቸው ወደ ስፔን መሄድ ይችላሉ ተብሏል። በሌላ በኩል ዩኬ የስፔን ተጓዞች ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ወስናለች።

    ሰሜን ኮሪያ- አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ተጠርጥሯል ተብሏል። ግለሰቡ ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ሸሽቶ የነበረና ድንበር አልፎ የተመለሰ መሆኑን የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ዘግቧል።

  2. የዩናይትድ ኪንግደም ምጣኔ ሀብት ለማገገም አራት ዓመታት ሊወስድበት ይችላል ተባለ

    የልብስ ሱቅ ውስጥ ያለች ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኢንግላንድ ሰኔ ወር ላይ ሱቆች እንደገና ተከፍተዋል

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዩናይትድ ኪንግደም ላይ ያሳደረውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ በተመለከተ የተለያዩ ትንበያዎች ይሰጣሉ።

    አሁን አዲስ የወጣው ጥናት የዩኬ ምጣኔ ሀብት ከወረርሽኙ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሊስተካከል የሚችለው ከአራት ዓመታት በኋላ እንደሆነ አመልክቷል።

    የአገሪቷ የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ኢዋይ አይተም ክለብ፤ የሥራ አጦች ቁጥር 3.9 በመቶ ከነበረው ወደ 9 በመቶ ከፍ እንደሚል ጠቁሟል።

    ከዚህም ባሻገር በዚህ ዓመት ምጣኔ ሀብቱ በ11.5 በመቶ እንደቀነሰ ተጠቅሷል። ይህም ከአንድ ወር በፊት ከገመቱት 8 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ጨምሮ ታይቷል።

  3. ዩኬ የስፔን ተጓዦች ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አስገደደች

    ጎብኝዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ስፔን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከስፔን የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀን በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እገዳ ከጣለች በኋላ ስፔን በወረርሽኙ ሳቢያ የተመታውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመታደግ እየታገለች ነው።

    እገዳው መጣሉን ተከትሎም የስፔን የመንግሥት ባለሥልጣናት ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ በመግለጽ፤ ባሌሪክ ደሴቶችን ጨምሮ የተወሰኑ ቦታዎች በእገዳው እንዳይካተቱ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

    ባለፈው ዓመት ወደ 18 ሚሊየን የሚጠጉ እንግሊዛዊያን ወደ ስፔን ተጉዘዋል። ከእነዚህ መካከል አንድ አራተኛው መዳረሻቸው በአገሪቷ ውስጥ የሆነ ነው።

    ይሁን እንጂ በዩኬ ጤና ሚኒስትር ውስጥ የሚሠሩት ሄለን ኋትልይ አገሪቷ የጣለችው የለይቶ ማቆያ ሕግ ተገቢ ነው ሲሉ ተከላክለዋል።

    ሚኒስትሯ ለቢቢሲ “በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። የወረርሽኙ ሥርጭት እየጨመረ በመሆኑ ወደ ቀደሞው ችግር በመመለስ አደጋውን መጋፈጥ አንችልም” ብለዋል።

    ከቅርብ ቀናት ወዲህ በስፔን የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ ነው።

    ምንም እንኳን በበርካታ የአገሪቷ አካባቢዎች ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ቢውልም፤ በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች በተለይ በካታሎኒያ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ እና በጎረቤቷ አራጎን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሬ አሳይቷል።

    እንደ የአውሮፓ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ፤ በአገሪቷ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ100 ሺህ ሰዎች 39.4ቱ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በዩናይትድ ኪንግደምና ጎረቤት አገሯ ፈረንሳይ ግን በቫይረሱ የተያዙት ከ100 ሺህ ነዋሪዎች 14.6 ያህሉ ናቸው።

  4. “ኮቪድ-19 እጅግ አደገኛው የጤና ቀውስ ነው” ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

    የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፤ “ኮቪድ-19 እጅግ አደገኛው የዓለም የጤና ቀውስ ነው” አሉ።

    ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም አደገኛ ናቸው ካላቸው የጤና እክሎች ኮሮናቫይረስ የባሰው እንደሆነ ተናግረዋል።

    ዶ/ር ቴድሮስ ጄኔቫ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፤ ወደ 16 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና 640 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቃቸውን ገልፀዋል።

    “ወረርሽኙ መባባሱን ቀጥሏል፤ ባለፉት ስድስት ሳምንታት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል” ብለዋል።

    ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም
  5. ሄትሮው ኤርፖርት ተርሚናሎችን ለማጽዳት ሮቦቶች እየተጠቀመ ነው

    ሄትሮው ኤርፖርት

    የፎቶው ባለመብት, PA WIRE

    የለንደኑ ሄትሮው ኤርፖርት ከሌላ ጊዜው ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም ዲሲኢንፌክታንት የሚረጩ ሮቦቶችን እየተጠቀመ ይገኛል።

    ሮቦቶቹ 'አልትራቫዮሌት' የተባለ ጨረር የሚረጩ ሲሆን ጨረሩ ቫይረስና ጀርሞችን በመግደል እንዳይራቡ ያደርጋቸዋል።

    በእያንዳንዱ ተርሚናል አንድ ሮቦት የተዘጋጀ ሲሆን በዋነኛነት እንደ ሽንት ቤትና አሳንሰር የመሳሰሉ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን አካባቢዎች ያጸዳሉ።

    ነገር ግን ሰዎች አካባቢ ስራቸውን መስራት አይችሉም፤ ምክንያቱም ጨረሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ያስከትላል።

    ሮቦቶቹ በጨረሩ አማይይነት የሰዎችን ቆዳ ሊያቃጥሉ ስለሚችሉ ስራቸውን ሲሰሩ አጠገባቸው ሰዎች አይኖሩም ተብሏል።

  6. ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሸሽቶ የሄደው ግለሰብ ኮቪድ-19 አልተያዘም አለች

    ሰሜን ኮሪያ

    የፎቶው ባለመብት, ED JONES / GETTY

    በኮሮናቫይረስ መያዙ የተጠረጠረው የመጀመሪያው ሰሜን ኮሪያዊ ነጻ መሆንኑን በምርመራ ማረጋገጧን ደቡብ ኮሪያ ገለፀች።

    ግለሰቡ ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከሦስት ዓመታት በፊት መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ግን ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ ነበር።

    ግለሰቡ ከደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረው በደቡባዊ ደሴቲ አካባቢ በሚገኝ የቱቦ ማስተላለፊያ ውስጥ በመሹለከለክና በመዋኘት ነበር።

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሰሜን ኮሪያ በኮቪድ-19 የተጠረጠረ ሰው ማግኘቷን አሳውቃ ነበር።

  7. በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ምን ያህል ይታመናል?

    ደብብ አፍሪካ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት ሁሉ የተሻለ የመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ልምድና ተሞክሮ አላት። ግን ቁጥሮችን ማመን ከባድ ነው።

    ቁጥሮችን ብቻ ሳይሆን እንደማሳያ የሚወሰዱ መረጃዎችን ማመኑም አዳጋች ነው።

    አንዳንድ ታዛቢዎች በአገሪቱ በኮቪድ-19 ተይዘው የሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን በማየት ብቻ የአገሪቱን ስኬት ለማንቆለጳጰስ ይሮጣሉ።

    ይህ የሆነው በአገሪቱ ውስጥ የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ ነው? ወይስ አፍሪካውያን የተለየ የመከላከል ብቃት፣ ተፈጥሮ ወይም ሌላ ምስጢር ስላላቸው ነው?

    መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። አይደለም። ደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት እየተጋፈጠች ያለውን ሞት ለመናገር ጊዜው ገና ነው።

    ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ትልልቅ ሆስፒታሎች በኮቪድ-19 ተይዘው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከጣልያን እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር ሲነጻጸር እጅጉን ተቀራራቢ ነው።

  8. የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ በይፋ የሚናገሩት የዛምቢያ የፓርላማ አባል በኮቪድ-19 ተያዙ

    ልዕልት ካሱኔ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር እንደሚኖሩ በይፋ የሚናገሩት የዛምቢያ የህዝብ እንደራሴ አባል ልዕልት ካሱኔ ዙሉ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው አስታውቀዋል።

    የተቃዋሚ ፓርቲው 'ናሽናል ደቨሎፕመንት' አባል የሆኑት የፓርላማ አባል ባሳለፍነው ሐሙስ ነበር የተመረመሩት።

    ከዛምቢያ ህዝብ እንደራሴዎች መካከል 15 አባላት እስካከሁን በኮቪድ-19 ሜኣዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ማንኛውም አይነት የፓርላማ ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጓል።

    ልዕልት ካሱኔ ለቢቢሲ ሲናገሩ በቫይረሱ በመያዛቸው እንዳልተገረሙ ገልጸዋል። '' ፓርላማው ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ እንደሆነ እያወቀ እንኳን ስብሰባዎችን ያደርግ ነበር'' ብለዋል።

    አክለውም ተጓዳኝ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በተቻላቸው መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳlባቸው አሳስበዋል።

  9. በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 ሚሊየን ደረሰ

    ኮሮናቫይረስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይናዋ ሁሃን መነሳቱ ከተሰማ ወዲህ በመላው ዓለም ተሰራጭቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከግማሽ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ሞት ምክንያት ሆኗል።

    እስካሁን በመላው ዓለም የቫይረሱ ስርጭት ምን እንደሚመስል እናስቃኛችሁ፦

    • ባለፉት አራት ቀናት ብቻ አንድ ሚሊየን ሰዎች በመላው ዓለም በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሲሆን አጠቃላይ ቁጥሩን ደግሞ ወደ 16 ሚሊየን ከፍ አድርጎታል።

    • ባለፉት 24 ሰአታት ብቻ ብራዚል ውስጥ 55 ሺ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    • በአሜሪካ 53 ሺ እንዲሁም 48 ሺ ደግሞ በህንድ በተመሳሳይ ባለፉት 24 ሰአታት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መሆናቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል።

    • በቪዬትናም ካለፈው ሚያዝያ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቱሪስቶች በሚያዘወትሯት ዳ ናንግ ከተማ አራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግኝታለች።

    • እስራኤል ደግሞ መጀመሪያ አካባቢ በወሰደቻቸው እርምጃዎች ብትሞካሽም ቫይረሱ በድጋሚ እያንሰራራ እንደሆነ ተገልጿል።

  10. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች!

    BBC

    ቢቢሲ አማርኛ ከአገር ውስጥና ከመላው ዓለም የተወጣጡ ኮሮናቫይረስን የተመለከቱ ዜናዎች ወደናንተ የሚያደርስበት የቀጥታ ዘገባው አሁን ይጀምራል።

    አብራችሁን ቆዩ።

  11. በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛው የሞት ቁጥር ተመዘገበ

    ቢቢሲ አማርኛ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ እስካሁን ከታየው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

    የጤና ሚኒስቴር ዕሁድ አመሻሽ ላይ ባወጣው ዕለታዊ የወረርሽኙ ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው እስካሁን ከተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ሁሉ ከፍተኛ የሆነው የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጿል።

    በዚህም በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች አሃዝ 223 ደርሷል።

    በምርመራ በኩልም በ9 ሺህ 527 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 720 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተገልጾ በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 13 ሺህ 968 ከፍ ብሏል።

    በተጨማሪም ከበሽታው 250 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን እስካሁን በአጠቃላይ 6 ሺህ 216 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

    ከዚህ ቀደም በሽታው እንዳለባቸው ተረጋግጦ የህክምና ድጋፍ ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከልም 65ቱ በጽኑ ታመው እንዳሉ ተገልጿል።

    ከባለፈው ዕሁድ ጀምሮ ባሉት ቀናት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ የተመዘገበ ሲሆን ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች በአንድ ቀን ሲመዘገብ የዛሬው ሦስተኛው ነው።

    በዛሬው ዕለት የተመዘገበው የሞቾች፣ በቫይረሱ የተያዙና ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛው ሲሆን፤ አገሪቱ የምታደርገው የምርመራ ቁጥርም በከፍተኛ መጠን መጨመሩን በየዕለቱ የሚወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

  12. ኢራን በአንድ ቀን ከ2300 በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን አገኘች

    ኢራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኮሮናቫይረስ መልሶ እያገረሸባት ያለችው ኢራን ዛሬ [ዕሁድ] ተጨማሪ 2,333 አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን ይፋ አደረገች።

    ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 216 ሰዎች ኢራን ውስጥ የሞቱ ሲሆን ይህም በአገሪቱ እስካሁን በበሽታው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ወደ 15 ሺህ 700 አድርሶታል።

    ኢራን ከወራት በፊት በበሽታው ክፉኛ በተመታችበት ወቅት ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በቀነሰበት ጊዜ አላልታው ነበር።

    በዚህም መስጂዶች፣ ሱቆችና የመናፈሻ ቦታዎች እንዲከፈቱ ሲደረግ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት የሚደረጉ ጉዞዎችም ተፈቅደዋል።

    ወረርሽኙ መጀመሪያ ላይ በተከሰተበት ወቅት ዋና ከተማዋን ቴህራንንና ቆም የተየተባለችውን ግዛት ነበር ክፉኛ ያጠቃው። የአሁኑ ደግሞ አገሪቱ ከኢራቅ ጋር በምትዋሰንበት የደቡብ ምዕራብ አካባቢ በስፋት እየተዛመተ ነው።

    የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሩሃኒ ዜጎቻቸው በሕዝብ ትራንስፖርትና ሰው በሚበዛባቸው ስፍራዎች ሁሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለም የዋና ከተማዋ ቴህራን ባለስልጣናት በአንዳንድ የንግድና በርካታ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ጥለውት የነበረውን እገዳ መልሰው ተግባራዊ አድርገዋል።

  13. በስፔን ወረርሽኙ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል

  14. አውስትራሊያ ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ሰዎች ሞቱባት

    ሜልቦርን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ ምክንያት እንደሞተባት ይፋ አድርጋለች።

    አገሪቱ ዛሬ [እሁድ] እንዳስታወቀችው በቫይረሱ ምክንያት 10 ሰዎች በአንድ ቀን ሞተውባታል።

    ቫይረሱ እጅግ በተስፋፋባት ቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ 459 ሰዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡ ተመዝግቧል።

    አውስትራሊያ ወረርሽኙ ዓለምን ካጥለቀለቀ ወዲህ በቫይረሱ ምክንያት 155 ሰዎች ሲሞቱባት 14 ሺህ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    ወረርሽኙ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ የአምስት ሚሊዮን ነዋሪዎች መኖሪያ የሆነችው ሜልቦርን ላላፉት ሁለት ሳምንታት የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ቆይታለች።

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ ሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ መንቀሳቀስም ክልክል ነው።

    ፖሊስ፤ ወደ ቪክቶሪያ ግዛት የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን እየተቆጣጠርኩ ነው ብሏል።

  15. የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ 'የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው'

  16. የኮሮናቫይረስ በስፔን በስፋት መልሶ ሊያገረሽ ይችላል ተባለ

    ስፔን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ቀደም ካለው ሰፋ ያለ የኮሮናቫይረስ መልሶ “ሊያገረሽ ይችላል” ብላ ስጋት ውስጥ ያለችው ስፔን አዳዲስ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው።

    በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ውጪ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ የበሽታው መስፋፋት እየታየ ሲሆን የካታሎኒያ ግዛት ደግሞ ለሁለት ሳምንታት የምሽት መዝናኛ ቦታዎችን እንዲዘጉ አድርጋለች።

    ስፔን ጥላው የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካበቃ ከወር በኋላ ዋና ከተማዋን ማድሪድን ጨምሮ ባርሴሎናና ዛራጎዛን በመሳሰሉ ከተሞች በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመታየቱ መንግሥት ወረርሽኙ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያገርሽ እንደሚችል እያስጠነቀቀ ነው።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴርም በሠራዊቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችል ወረርሽኝን ለመለየትና ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሥርዓት ተግባራዊ እያደረገ ነው።

    የጤና ሚኒስቴር ባለፈው አርብ ከ900 በላይ አዲስ ህሙማን መገኘታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፤ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወት አንድ የእግር ኳስ ቡድን 28 አባላቱ በበሽታው ተይዘውበታል።

  17. ሰሜን ኮሪያ 'የመጀመሪያውን' የኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪ ማግኘቷን አስታወቀች

  18. በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 አለፈ

    ሐኪሞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከሁለት መቶ በላይ እንደደረሰ ተገለጸ።

    ከበሽታው ጋር በተያያዘ ህይወታቸው የሚያልፍና በአስከሬን ላይ በሚደረጉ ምርመራዎች የሚገኘው አሃዝ እንደሚያመለክተው እስካሁን በአገሪቱ 209 ሰዎች ሞተዋል።

    አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት የምታደርገው የምርመራ መጠን እየጨመረ መሆኑን በየዕለቱ የሚወጣው የበሽታው ሁኔታ መግለጫ ሪፖርት ያመለክታል።

    ትናንት ቅዳሜ ሐምሌ 18/2012 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ መሰረት ምርመራው ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ማለትም 8 ሺህ 490 ናሙናዎች ላይ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 555 ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በተጨማሪም በዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ድጋፍ ሲያገኑ ከነበሩት መካከል 181 ሰዎች አገግመዋል።

    አስካሁን በተደረገው 372 ሺህ 812 የወረርሽኙ ምርመራ በ13 ሺህ 248 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 5 ሺህ 966 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

    ቀደም ባሉት ሳምንታት በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ማገገማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት የተገኙት ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ በአሁኑ ጊዜ በህመሙ ተይዘው ያሉ ሰዎች ቁጥር ካገገሙት ሰዎች እንዲልቅ ምክንያት ሆኗል።

  19. የዕለተ ዕሁድ ሐምሌ 19/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ?

    ዕሁድ ሐምሌ 19/2012 ዓ.ም

    በሽታውን ለመከላከል ከሚወሰዱ እርምጃዎች ውጪ ክትባትም ሆነ መድኃኒት ባልተገኘለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው።

    ከቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በየደቂቃው የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በተለይ በዚህ ገጽ ላይ በቀጥታ እናቀርባለን።

    ስለወረርሽኙ ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት በአመቻችሁ አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

    በባለሙያዎች የሚመከሩ የበሽታውን የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ እራሳችሁንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንድትጠብቁ እያስታወስን መልካም ዕለት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

    ቢቢሲ አማርኛ
  20. ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ ምርመራ 555 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

    የኮሮናቫይረስ መግለጫ

    ባለፉት 24 ሰዓታት ለ8490 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ 555 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴርና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።

    የ9 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 181 ሰዎች ማገገማቸውም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 13 ሺህ 248 ደርሷል።