የአንድ ክለብ አባል የሆኑ 15 እግር ኳስ ተጫዋቾች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዛምቢያ ፕሪሚየር ሊግ የናፕሳ ሰታርስ ክለብ 15 ተጫዋቾችና አራት ኃላፊዎች በአጠቃላይ 19 የክለቡ አባላት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የክለቡ ቃል አቀባይ አስታወቁ ።
ከሁለት ሳምንት በፊት የፎረስት ሬንጀርስ ክለብ 28 ተጨዋቾችና ባለሥልጣናት በቫይረሱ መያዛቸውን የሚታወስ ሲሆን ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ያጋጠመ ነው ተብሏል።
የናፕሳ ስታር ክለብ አስራ አምስት ተጫዋቾችና አራት ባለሥልጣናት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው በተደረገ መደበኛ ምርመራ እንደሆነ የክለቡ ቃል አቀባይ ግዌን ቺፓሱላ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በቫይረሱ የተያዙት ተጨዋቾችና ባለሥልጣናት በጤና ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።
ቃል አቀባይዋ በተጨማሪ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት፤ ግለሰቦቹ ላይ የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ ክለቡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አክለዋል።
ቀሪው የቡድኑ አባላትም ለሚመጡት ጨዋታዎች ዝግጅታቸውን መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
የክለቡ መሪ ግሬግ ቾላ ሶፉ በበኩላቸው “ ተጫዋቾቻችንን፣ ደጋፊዎቻችንን እንዲሁም አጠቃላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅን እና የእጅ ማፅጃ ፀረ- ተሕዋስ መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እጠይቃለሁ” ሲሉ ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳስበዋል።
በዛምቢያ እስካሁን 4 ሺህ 481 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 139 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
















