በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በዛሬው ዕለት ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠውን 610 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው። ። ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ ካለባች ከተሞች ደግሞ ቀዳሚውን የምትይዘው ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ስትሆን፣ እስከ አሁን በዋና መዲናዋ ብቻ 10ሺህ 703 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባም ኮቪድ-19 ይበልጥ እየተሰራጨባቸው የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ቦሌ (1652 ሰዎች)፣ አዲስ ከተማ (1329 ሰዎች) እንዲሁም ጉለሌ (1308 ሰዎች) ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ለወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና እጅን መታጠብ ላይ መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሺህ አለፈ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተካሄደ 6503 የላብራቶሪ ምርመራ 653 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገጠ።

    የጤና ሚንስትር እና የሕብረተሰብ ጤና ሚንስትር በሰጡት እለታዊ መግለጫ መሠረት፤ ባጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15 ሺህ 200 ደርሷል።

    በበሽታው ሳቢያ 11 ተጨማሪ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 239 ደርሷል።

    170 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ እስካሁን ያገገሙ ሰዎች 6526 ደርሰዋል።

    በአገሪቱ በአጠቃላይ 395 ሺህ 851 የላብራቶሪ ምርመራ ተካሂዷል።

    ኮቪድ-19

    የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

  2. የትራምፕ ልጅ የትዊተር ገጽ ለ12 ሰዓት ታገደ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ የሆነው ትራምፕ ጁኒየር፤ ስለ ኮቪድ-19 የተሳሳተ መረጃ ያለማሰራጨት መርህን ጥሷል በሚል የትዊተር ገጹ ለጊዜው ታገደ።

    የትራምፕ ልጅ አባቱ በተደጋጋሚ ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል በማለት ሲናገሩለት ስለነበረው መድኃኒት ሃይድሮክሲክሎሮክዊን የሚገልጽ ተንቀሳቃሽ ምስል ነበር በትዊር ሰሌዳው ላይ ያጋራው።

    ይህ መድኃኒት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ በተለያዩ አገራት በቫይረሱ ለተያዙ ህሙማን በሰፊው ይሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ በተደረገው ምርምር መድኃኒቱ ፈዋሽ አለመሆኑ ተረጋግጧል።

    ትዊተር፤ የትራምፕ ጁኒየር ትዊት፣ ፖሊሲዬን ጥሷል እንዲሁም ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ ጎጂ ወይም አሳሳች መረጃ አሰራጭቷል በሚል ገጹን ለ12 ሰዓት ያህል እንዳያንቀሳቅስ አግዷል።

    የተለጠፈው ቪዲዮም ከሰሌዳው ላይ እንዲወርድ ተደርጓል።

    ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር፣ ትዊተርን መጠቀም እንዲሁም መልዕክት መላክ ግን ይችላል ተብሏል።

    የትዊተር ገጽ

    የፎቶው ባለመብት, Twitter

  3. በፓኪስታን ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

    በፓኪስታን፣ ፑንጃብ ከተማ ከኢድ በዓል ጋር በተያያዘ ተጥሎ የነበረውን የዘጠኝ ቀን ገደብ በመተላለፍ እየተካሄደ ያለውን ንግድ ተከትሎ ተቃውሞና ግጭት ተቀስቅሷል።

    እገዳው ከተጣለ በኋላ በአንዳንድ ከተሞች የተተገበው በከፊል ነው። አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ግን የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው ተዘግቧል።

    ፈይሰላባድ እና ራውልፒንዲበተባሉ ከተሞች ውጥረቱ የተባባሰ ሲሆን፤ በፈይሰላባድ ፖሊሶች ነጋዴዎችን በዱላ ሲመቱ ታይቷል። የታሰሩ ነጋዴዎችም አሉ።

    በራውልፒንዲ የንግድ ተቋማት ተከፍተው፣ የንግድ ተቋማት መሪዎች ተቃውሞ ሲያሰሙም ነበር። እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ አልወሰደም ነበር።

    የፑንጃብ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ከሆነ መንግሥት በሌሎች ሦስት ግዛቶች ላይ እገዳ አለመጣሉ ኢ-ፍትሐዊ ነው።

    ከኢድ በፊት ያሉት ቀናት ንግድ የሚጧጧፍባቸው እና ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኙበት መሆኑንም ተቃዋሚዎቹ ተናግረዋል።

    ፓኪስታን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  4. የዓለም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ 320 ቢሊዮን ዶላር አጣ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከታህሳስ እስከ ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የዓለም የቱሪዝምን ኢንዱስትሪን 320 ቢሊዮን ዶላር እንዳሳጣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ገለፀ።

    ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደገለፀው ይህ ኪሳራ ዓለም በ2009 ገጥሟት ከነበረው የፋይናንስ ኪሳራ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነው።

    በእነዚህ ወራት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሉ የተነሳ የጎብኚዎች ቁጥር በዓለም ላይ በ300 ሚሊዮን የቀነሰ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ56 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተጠቅሷል።

    “ይህ መረጃ ቱሪዝም በፍጥነት ዳግም መጀመር እንዳለበት በግልጽ ያሳያል” ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የበላይ ኃላፊ ዙራብ ፖሎሊካሽቪሊ ናቸው።

    አክለውም “ የዓለም አቀፉ ቱሪዝም በአስደንጋጭ ሁኔታ በመቀነሱ፣ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ፣ በታዳጊ አገራት የሚገኙትን ጨምሮ፣ ሚሊዮኖች ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።”

    ጎብኚ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  5. በናይጄሪያ በአንድ ቀን በርካታ ህሙማን ከሆስፒታል ወጡ

    በናይጄሪያ በአንድ ቀን 829 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ከሆስፒታል ወጥተዋል። ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን የአገሪቱ የበሽታ ቁጥጥር ተቋም (ኤንሲዲሲ) አስታውቋል።

    በናይጄሪያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 18,203 ደርሰዋል።

    ትላንት የአገሪቱ መንግሥት እንደገለጸው፤ በ24 ሰዓት ውስጥ 648 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 41,180 ደርሷል።

    ናይጄሪያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

  6. አንዳንድ ‘ሳኒታይዘሮች’ ለጤና እክል ያጋልጣሉ ተባለ

    የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ተቋም (ኤፍዲኤ) አንዳንድ እጅ ማጽጃዎች (ሳኒታይዘር) ለጤና እክል እንደሚያጋልጡ አሳሰበ።

    ከአልኮል የተሠሩና በከፍተኛ ደረጃ ሜታኖል የተባለው ኬሚካል ያላቸው ሳኒታይዘሮች ጥቅም ላይ ሲውሉ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት ተቋሙ አስጠንቅቋል።

    እሳት በማስነሳት የሚታወቀው ሜታኖል ቆዳ ላይ ጉዳት ያስከትላል። ሰውነት ውስጥ ከገባ ደግሞ ሕይወት ሊቀጥፍም ይችላል።

    መሰል ጉዳት ያላቸው ሳኒታይዘሮች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማስጠንቂያ ማውጣቱን ተቋሙ ገልጿል። ገበያ ላይ ያሉት ሳኒታይዘሮች ለሸማቾች እንዳይሸጡም እንቅስቃሴ ጀምሯል።

    ተቋሙ ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ በርካታ ሰዎች የልብ ህመም እንደገጠማቸው፣ ማየት እንደተሳናቸው እንዲሁም የሞቱ ሰዎች እንዳሉም ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነው።

    ሳኒታይዘር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  7. ቦሪስ ጆንሰን፡ “በአውሮፓ ቫይረሱ ሊያገረሽ እንደሚችል ምልክቶች አሉ”

    ዩናይትድ ኪንግደም የስፔን ተጓዦችን ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ አስገባለው ማለቷ አነጋጋሪ መሆኑ ይታወሳል።

    ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ ውሳኔው ትክክል መሆኑን አስረግጠው፤ “በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ቫይረሱ ሊያገረሽ እንደሚችል ምልክትቶች አሉ” ብለዋል።

    “በድጋሚ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ አፋጣኝና ጠንካራ እርምጃዎች መውሰድ አለብን” ብለዋል።

    አሁን ባለው አደገኛ ሁኔታ ከአንድ አገር ወደ ሌላው መጓዝ የግለሰቦች ውሳኔ መሆኑን ቦሪስ ጠቅሰዋል።

    የለይቶ ማቆያ ጊዜው ወደ 10 ቀናት ሊቀነስ ይችላል? ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መንግሥታቸው ምን ጊዜም ውሳኔው የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቅረፍ እንደሚሞክር ተናግረዋል።

    አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገቡ ሰዎች መርሁን መከተል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

    ቦሪስ ጆንሰን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ቦሪስ ጆንሰን
  8. ጭምብል ማድረግ ወደሰውነት የሚገባ የቫይረስ መጠንን እንደሚቀንስ ጥናት አሳየ

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፤ ሰዎች ጀርሞችን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ ለማድረግ እንደሚረዳ በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል።

    አሁን ደግሞ አንድ አዲስ ጥናት ጭምብል ማድረግ ሌሎች ሰዎችን ከበሽታ ከመታደጉም በተጨማሪ ጭምብል ለሚያደርገው ሰውም ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁሟል።

    ‘ጄነራል ኢንተርናል ሜድስን’ መጽሔት ላይ ይታተማል ተብሎ የሚጠበቀው ጥናት እንደሚያሳው፤ ጭምብል የሚያደርጉ ሰዎች በበሽታ የመያዝ እድላቸው ይቀንሳል፤ የሚያሳዩት የበሽታ ምልክትም አነስተኛ እንዲሆን ይረዳል።

    እንስሳት ላይ ሙከራ በማካሄድና ወረርሽኙን በአንከሮ በመከታተል የተሠራው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጭምብል ወደሚያደርጉ ሰዎች ሰውነት የሚገቡት ውስን የኮሮናቫይረስ ቅንጣቶች (ፓርቲክልስ) ናቸው።

    ይህም ሰውነት በሽታውን በቀላሉ እንዲከላከል ያግዘዋል።

    በአሜሪካ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ዶ/ር ፅዮን ፍሬው በጥናቱ ባይሳተፉም፤ ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት፤ ጭምብል ማድረግ እና በመጠነኛ ደረጃ ለበሽታ በመጋለጥ መካከል ትስስር ስለመኖሩ ገና አልተረጋገጠም።

    ሆኖም ግን አዲሱ ጥናት “ጭምብል ማድረግ ለሌላው ሰው ብቻ ሳይሆን ለራስም ይጠቅማል” የሚል መልዕክት እንዳለው ዶ/ር ፅዮን ተናግረዋል።

    ጭምብል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  9. ከወራት በላይ በሆስፒታል የቆዩት የ75 ዓመቷ የኮቪድ -19 ታማሚ አገገሙ

    ሳፉራት ኦይኒክ ላዶጀ ከቤተሰቦቿ ጋር

    በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሕክምና ሲደረግላቸው የነበሩ የ75 ዓመት ሴት ከ111 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ለቤታቸው መብቃታቸው ተገለፀ።

    ሳፉራት ኦይኒክ ላዶጀ የተባሉት እኝህ ሴት በበሽታው ተይዘው በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ በሚገኘው ግሬት ሴስተርን ሆስፒታል የገቡት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

    እዚያም ለ6 ሳምንታት ያህል በአጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እየታገዙ በፅኑ ሕሙማን ክፍል ቆይተዋል።

    ሳፉራት በሆስፒታሉ በአጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ ከታገዙ በኋላ አገግመው የወጡ የመጀመሪያዋ በእድሜ ትልቋ ሴት መሆናቸውንም የሆስፒታሉ ኃላፊ ተናግረዋል።

    “ማውራትም ሆነ መነሳት አልችልም ነበር ፤ እስካሁን በሕይወት በመኖሬ ፈጣሪየን እያመሰገንኩ ነው” ብለዋል ሳፉራት።

  10. ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ አገራት አዳዲስ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው

    ማስክ ያደረገ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በርካታ የአውሮፓ አገራት ወረርሽኙ እንደገና ያገረሻል በሚል ስጋት የተነሳ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት አዲስ ውሳኔዎችን እያስተላለፉ ነው። ከእነዚህ መካከል ቤልጂየም ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና ስፔን ይገኙበታል።

    ቤልጂየም፦ ቤልጂየም ሰኞ ዕለት መሰባሰብን በተመለከተ ያሏትን ገደቦች አጥብቃለች። በመሆኑም ከረቡዕ ዕለት ጀምሮነዋሪዎች ከቤተሰባቸው አባላት ውጭ ቢበዛ አምስት ሰዎችን እንዲያገኙ ይፈቀድላቸዋል ተብሏል።በሕዝብ መገልገያ ቦታዎችመሰብሰብ የሚችለው የሰው ቁጥርም በግማሽ የቀነሰ ሲሆን በቤት ውስጥ 100፤ ከቤት ውጭ ደግሞ 200 እንዲሆን ተደርጓል። ቤልጂየም በአውሮፓከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ያሉባት አገር ስትሆን ቁጥሩም እየጨመረ ነው። ባለፈው ሳምንት በቀን በአማካይ 279 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም ቀድሞ በነበረው ሳምንት ከተመዘገበው 163 ጭማሬ አሳይቷል።

    ጀርመን ፦ የጤና ሚኒስትርጀንስ ስፓህን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከፍተኛ የቫይረሱ ሥርጭት ካለባቸው አገራት ወደ አገሪቷ ለሚገቡ መንገደኞች ግዴታ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ፈረንሳይ፦ ፈረንሳይም ባለፈው ሳምንት በብሪታኒይ ሪዞርት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በኪቤሮን ባህር ዳርቻዎች የምሽት ሰዓት እላፊ ጥላለች።

    ስፔን፦ ስፔን በወረርሽኙ ሳቢያ የተዳከመውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋን ለመታደግ ጥረት እያደረገች ቢሆንም በካታሎኒያና አራጎን አካባቢዎች ወረርሽኙ እየተስፋፋ ነው። የአገሪቷ ባለሥልጣናት ግን ቫይረሱ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እየገለፁ ነው።

  11. አይኤምኤፍ ለደቡብ አፍሪካ የ4.2 ቢሊየን ዶላር ብድር አፀደቀ

    ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል

    ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካደረሰባት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም የሚያስችል የ4.3 ቢሊየን ዶላር ብድር ማፅደቁን አስታወቀ።

    በአፍሪካ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ እስካሁን 450 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    አገሪቷ ከአይኤምኤፍ ብድር ስትቀበልም ይህ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

    የአገሪቷ የገንዘብ ሚኒስትር ቲቶ ምቦወኒ፤ “ገንዘቡ የአገሪቷን የተዳከመ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት በመደገፍ እና ግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎችን በመርዳት ወረርሽኙን ለመቆጣጠርበተጨማሪም ያጋጠመውን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግም ለማስቻል ይውላል” ብለዋል።.

    አገሪቷየወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት በቅርቡ ከኒው ዲቨሎፕመንት እና ከአፍሪካ ዲቨሎፕመንት ባንኮች በአጠቃላይ ወደ 1.3 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ብድር ወስዳለች።

  12. "የዩናይትድ ኪንግደም የለይቶ ማቆያ ሕግ ፍትሓዊ አይደለም" የስፔን ጠቅላይ ሚኒስተር

    የባህር ዳርቻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከስፔን የሚገቡ ተጓዦች ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የጣለው ገደብ ፍትሃዊ አለመሆኑን የስፔን ጠቅላይ ሚኒስተር ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስተር ፔድሮ ሳንቼዝ በአብዛኛው የስፔን አካባቢዎች ያሉ ጎብኝዎች ከዩኬ በተሻለ ከኮሮናቫይረስ የተጠበቁ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት አገሪቷ ውሳኔዋን መልሳ እንደምታስብበት ተስፋ አድርገው እንደነበር ገልፀዋል።

    ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ውሳኔውን የመለወጥ እቅድ እንደሌለው አስታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን ቃል አቀባይ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ‘ማንኛውም ጉዞ ከአደጋ ነፃ አይደለም’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ሰኞ ዕለት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፤ ሰዎች አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር ወደ ካናሪይ እና ባሌሪክ ደሴቶች፤ እንዲሁም ወደ ስፔን ጉዞ እንዳያደርጉ መክረዋል።

    ከስፔን ቴሌሲንኮ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስተር ፔድሮ፤ የዩኬ መንግሥት ስፔን የለይቶ ማቆያ ሕጉ ከሚመለከታቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ ያወጧታል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር እና አሁንም ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል።

    64.5 በመቶ የሆነው አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡት በሁለት ግዛቶች ብቻ መሆኑን በመግለፅም ዩኬ የወረርሽኙን ሥርጭት የጨመረው በመላ አገሪቷ እንደሆነ በማሰብ ‘ስህተት’ ሰርታለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    እንደ የአውሮፓ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል በስፔን የቫይረሱ ሥርጭት ከ100 ሺህ ሰዎች 35.1 ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም ግን ይህ አሃዝ 14.7 ነው።

    ሆኖም ወረርሽኙ በአብዛኛው የስፔን አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በሰሜን ምስራቋ ካታሎኒያ እና ጎረቤቷ አራጎን ግን የወረርሽኙ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

  13. የሐምሌ 21/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ

    ቢቢሲ አማርኛ ግራፊክስ

    እንደምን አደራችሁ የተከበራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች?

    ቢቢሲ አማርኛ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በዓለማችን አስጊ ስለሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከአገር ቤትና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያገኘናቸውን መረጃዎች ወደ እናንተ ያደርሳል።

    አስተያየትና ጥቆማ ካላችሁ በፌስቡክ ገፃችን ብታደርሱን በአክብሮት እንቀበላለን።

    መልካም ቀን እንዲሆንላችሁ ተመኘን!

  14. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በመሰብሰቧ እንድትቀጣ ተጠየቀ

    ቤተ ክርስቲያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በስፔን በሰሜን ምሥራቅ የምትገኘው ካታሎኒያ ባለሥልጣኖች፤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኮሮናቫይረስን ለመግታት የወጣውን ሕግ ተላልፋ በርካታ አማኞችን በመሰብሰቧ እንድትቀጣ ጠየቁ።

    እሁድ እለት ባርሴሎና በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን፤ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ተካሂዶ ነበር።

    ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሰዎች አካላዊ ርቀት ጠብቀው የነበረ ቢሆንም፤ ከአሥር ሰው በላይ እንዳይሰበሰብ የተጣለው እገዳ ግን ተጥሷል።

    የካታሎኒያ ፕሬዘዳንት ኩዊም ቶራ፤ በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁሉም አካል መተባበር አለበት ብለዋል።

    ባለፉት ጥቂት ቀናት በስፔን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ወረርሽኙን መቆጣጠር ቢቻልም፤ እንደ ካታሎኒያ ባሉ ግዛቶች በሽታው እየተስፋፋ ነው።

    የካታሎኒያ አራት ሚሊዮን ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ትዕዛዝ ተላልፏል።

  15. ኬንያ የወረርሽኙን ሥርጭት ተከትሎ የመጠጥ ሽያጭ አገደች

    የአልኮል መጠጦች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት መጨመሩን ተከትሎ ተጥሎ የነበረው የምሽት የሰዓት እላፊ ለተጨማሪ አንድ ወር እንደሚራዘም አስታወቁ።

    መጠጥ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆነው የሚቆዩ ሲሆን፤ ሬስቶራንቶችም መጠጥ እንዳይሸጡ መታገዳቸውን ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።

    ፕሬዚደንቱ ይህንን ያስታወቁት አገሪቷ ለኮሮናቫይረስ የሰጠችውን ምላሽ ለመገምገም ከክልል ገዥዎች ጋር ዛሬ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።

    በተለይ በቫይረሱ የሚያዙ ወጣቶች ቁጥር መጨመሩ እንዳሳሰባቸው የገለፁት ፕሬዚደንቱ፤ በግድየለሽነት የሚፈፅሙት ድርጊትም መላ አገሪቷን ለአደጋ አጋልጧል ብለዋል።

    በኬንያ እስካሁን ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 280 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

  16. የወርቅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ናረ

    ወርቅ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምጣኔ ሀብት መናጋትና የቫይረሱ ስርጭት ያስከተለውን ስጋት ተከትሎ ባለ ሀብቶች ገንዘባቸውን ምን ላይ እንደሚያውሉ ግራ ገብቷቸዋል። ይህን ተከትሎም የወርቅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መናሩ ተሰምቷል።

    ከዚህ ቀደም ከፍተኛው የወርቅ ዋጋ የተመዘገበው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2011 ላይ ሲሆን አንድ ወቄት1,921 ዶላር ሲገባ ነበር። ከዛ በማስከተል ከፍተኛው ዋጋው 1,944 ዶላር ገብቷል።

    ብዙ ባለ ሀብቶች ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ከሚታቀቡበት ምክንያት አንዱ ወለድ አለመክፈላቸው ነው። ሆኖም ግን ወርቅ ላይ ሀብት ማፍሰስ ትርፋማ እንደሚያደርግ ይታመናል።

    በተለይም በፖለቲካዊ ሁኔታ ሳቢያ ስለወደፊቱ እርግጠኛ መሆን በማይቻልባቸው ወቅቶች የወርቅ ዋጋ ይጨምራል።

    ዘንድሮ የወርቅ ዋጋ የጨመረው 25 በመቶ ነው።

    ለዋጋው መናር አንድ ምክንያት የተባለው ደግሞ የዶላር ዋጋ መላሸቁ ነው።

  17. የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ወረርሽኙን 'ተቆጣጥረነዋል' አሉ

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስተር ኢምራን ካን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስተር ኢምራን ካሀን መንግሥታቸው የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን መቆጣጠር መቻሉን አስታወቁ።

    በመሆኑም የአገሪቷ ሕዝቦች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው በመጭው የአረፋ በዓል ወቅት የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ የተመዘገበውን ውጤት ፍሬያማ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ፓኪስታን የአረፋ በዓልንና በሺያ ሙስሊሞች የሚከበረውን ባሕላዊ ክብረ በዓል 'ሙሃራም' ያለ ምንም ችግር ከተሻገረች "ሕይወታችንን ወደ ቀደመው ሁኔታ መመለስ እንችላለን" ብለዋል።

    በበዓላቱ ወቅት እንደ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግንና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ችላ ከተባለ የወረርሽኙ ሥርጭት ሊጨምር እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።

    አውስትራሊያ እና ኢራን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ የጣሏቸውን ገደቦች በማላላታቸው ወረርሽኙ እንደገና ማገርሸቱንም በምሳሌነት አቅርበዋል።

    ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በፓኪስታን ለወረርሽኙ ሥርጭት መቀነስ፤ ሌሎች ሀብታም አገራት ማድረግ ከሚችሉት ሙሉ የሰዓት እላፊ ይልቅ መንግሥት የጣለው “ስልታዊ የእንቅስቃሴ ገደብ" ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

  18. በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ተጨማሪ 579 ሰዎች ተገኙ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 7009 የላብራቶሪ ምርመራ 579 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው መረጋገጡ ተገለጸ።

    የጤና ሚንስትር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም በሰጡት እለታዊ መግለጫ መሠረት፤ አምስት ተጨማሪ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። 170 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል 422 ከአዲስ አበባ፣ 37 ከጋምቤላ፣ 35 ከድሬዳዋ፣ 23 ከትግራይ፣ 18 ከኦሮሚያ፣ 18 ከሲዳማ፣ 11 ከደቡብ፣ 7 ከሶማሊ፣ 5 ከሐረሪ፣ 2 ከአማራ እንዲሁም አንድ ግለሰብ ከአፋር ክልሎች ናቸው።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 14 ሺህ 547 ደርሷል።

    እስካሁን 389 ሺህ 348 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገዋል። በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 6386 ሲደርሱ፤ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች 228 ናቸው።

    አሃዝ

    የፎቶው ባለመብት, ቢቢሲ

  19. የትራምፕ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ኮቪድ -19 ተገኘባቸው

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሮበርት ኦብራያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሮበርት ኦብራያን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

    ዋይት ሃውስ በመግለጫው፤ አማካሪው ሮበርት መለስተኛ የበሽታው ምልክቶች እንደነበራቸው ገልፆ ራሳቸውን ማግለላቸውንና ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ሆነው ሥራቸውን ማከናወናቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጿል።

    መግለጫው አክሎም “ፕሬዚደንቱም ሆነ ምክትል ፕሬዚደንቱ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድል የላቸውም፤ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱም ሥራው አልተቋረጠም” ብሏል።

    የ54 ዓመቱ ሮበርት፤ በትራምፕ አስተዳዳር በኮቪድ -19 የተያዙ ከፍተኛው ባለሥልጣን ናቸው ተብሏል።

    ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በዋይት ሃውስ አልባሽ የሆኑት የጦር አባል፣ የምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ ፕረስ ሴክሬታሪያት ካቴ ሚለር እና የባህር ኃይል ሄሊኮፕተር ቡድንን ጨምሮ ሌሎች የአስተዳዳር ሠራተኞች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    የደህንነት አማካሪው ሮበርት በዚህ ወር ላይ ከአውሮፓ አቻቸው ጋር ስለ ውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ለመወያየት ወደ ፓሪስ ተጉዘው እንደነበር ተገልጿል።

  20. በዩናይትድ ኪንግደም በድመት ላይ ኮሮናቫይረስ ተገኘ

    የፊት መሸፈኛ ያደረገች ድመት

    የፎቶው ባለመብት, PA

    በዩናይትድ ኪንግደም ድመት ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱን የአገሪቷ የእንስሳት ጤና ባለሙያ አስታወቁ።

    በአገሪቷ ቫይረሱ በእንስሳት ላይ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

    ውጤቱ ይህንን ቢያሳይም መንግሥት ግን እንስሳዋ በሽታውን ለአሳዳሪዋ ወይም ለሌሎች የቤት እንስሳት ለማስተላለፏ እንዲሁም ቫይረሱን ወደ ሰው ማስተላለፍ እንደምትችል የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ አለመኖሩን ተናግሯል።

    የምርመራ ውጤቱ የተረጋገጠው ረቡዕ ዕለት ሲሆን፤ የተካሄደውም በዌይብሪጅ ቤተ ሙከራ ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ የኢንግላንድ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ሰዎች ከእንስሳት ጋር ከመነካካታቸው በፊት እና በኋላ እጃቸውን እንዲታጠቡ መክሯል።

    የእንስሳት ጤና ባለሙያዋ ክርስቲን ሚድልሚስ “ይህ ያልተለመደ ክስተት ነው፤ እስከዛሬ ድረስ በቫይረሱ የተያዙ እንስሳት መለስተኛ ምልክት ካሳዩ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ያገግማሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ “የቤት እንስሳት ቫይረሱን በቀጥታ እንደሚያስተላልፉ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም፤ ጉዳዩን በቅርበት ሆነን መከታተላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል ክርስቲን።