በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በዛሬው ዕለት ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠውን 610 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው። ። ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ ካለባች ከተሞች ደግሞ ቀዳሚውን የምትይዘው ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ስትሆን፣ እስከ አሁን በዋና መዲናዋ ብቻ 10ሺህ 703 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባም ኮቪድ-19 ይበልጥ እየተሰራጨባቸው የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ቦሌ (1652 ሰዎች)፣ አዲስ ከተማ (1329 ሰዎች) እንዲሁም ጉለሌ (1308 ሰዎች) ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ለወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና እጅን መታጠብ ላይ መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኦክስፎርዱ ክትባት ውጤታማ መሆኑ የሚታወቀው በጥቅምት መሆኑ ተገለጸ

    በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየተሠራ ያለው የኮቪድ-19 ክትባት ውጤታማ መሆኑ የሚታወቀው በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ላይ ነው ተባለ።

    አስትራዜንካ የተባለው የመድኃኒት ድርጅት በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ሁለት ቢሊዮን ክትባት የማምረት እቅድ ይዟል።

    በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ፣ በብራዚል እና በደቡብ አፍሪካ የተጀመሩ ሙከራዎች ውጤታማ መሆናቸው የሚታወቀውም በቀጣዩ ዓመት ነው።

    ድርጅቱ ለቢቢሲ እንዳለው፤ ቢያንስ ለ12 ወራት የሚቆይ በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያዳብር ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለ24 ወራት ወይም ከዚያ በላይ በሽታ መከላከል ያስችላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

    ጥናቱ አሁን ባለበት ደረጃ፤ ክትባቱ በሽታ የመከላከል አቅምን እንደሚያለምድ ቢታወቅም፤ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ መሆኑ ገና አልተረጋገጠም።

    ከአንድ ጠብታ ይልቅ ሁለት ጠብታ የተሻለ ውጤታማ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።

    ሆኖም ግን ክትባቱ ለምን ያህል ጊዜ በሽታ እንደሚከላከል አልታወቀም። በተጨማሪም ለበሽታው በዋነኛነት ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን ላይ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን አልታወቀም።

    ክትባት

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

  2. የቀድሞው የአሜሪካ እጩ ፕሬዘዳንት በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    ኸርመን ኬይን

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የምስሉ መግለጫ, ኸርመን ኬይን

    በ2012ቱ የአሜሪካ ምርጫ የሪፐብሊካን ተወዳዳሪ የነበሩት ኸርመን ኬይን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ።

    የ74 ዓመቱ ኸርመን በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡት በወሩ መባቻ ላይ ነበር።

    በድረ ገጻቸው ላይ “አለቃችን፣ ጓደኛችንና ለብዙዎቻችን እንደ አባት የነበሩት ኸርመን ኬይን አርፈዋል” የሚል መልዕክት ተለጥፏል።

    የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፤ አሜሪካ ውስጥ በቫይረሱ ከሞቱ እውቅ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው።

    ሆስፒታል ሳሉ ስለሚገኙበት ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ መረጃ ሲሰጥ ነበር።

    ሐምሌ 7 የኦክስጅን መጠናቸው ትክክለኛ መሆኑን ሀኪሞች እየመረመሩ መሆኑ ተገልጾ፤ “ከባድ ቫይረስ ነው። መጸለያችሁን አታቋርጡ” የሚል መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ተላልፎ ነበር።

    የተወለዱት በቴንሲ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸው የጽዳት ሠራተኞች ነበሩ። በሒሳብ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኮምፒውቲንግ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል።

    የቤተ ክርስቲያን አጥማቂ፣ የሬድዮ መርሀ ግብር አዘጋጅና ነጋዴም ነበሩ።

  3. አውሮፓ እና ኮሮናቫይረስ

    ኮቪድ-19 በአውሮፓ አገራት በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል። ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተውጣጡ ዜናዎች ተከታዮቹ ናቸው።

    ·ፖላንድ እና ሮማንያ- በአንድ ቀን ቫይረሱ የተገኘባቸው በርካታ ሰዎችን ካስመዘገቡ አገሮች መካከል ናቸው። ሮማንያ እንቅስቃሴ እንዲገታ ወስናለች።

    ·አይስላንድ- ለሦስት ወራት ቀስ በቀስ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲላላ ነበር። ነገር ግን የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ በድጋሚ እርምጃ ሊወሰድ ነው።

    ·ስፔን- በመዲናዋ ማድሪድ አዲስ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች አካላዊ ርቀት መጠበቅ ቢቻልም ባይቻልም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው።

    ·ፈረንሳይ-የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዣን ካስቴክስ ለሁለተኛ ጊዜ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ እንዳይጣል አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት ብለዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም- በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአውሮፓ ቀዳሚዋ ኢንግላንድ ናት። ከዚህ ቀደም ስፔን ሁለተኛ፣ ስኮትላንድ ደግሞ ሦስተኛ ነበሩ።

    ጭምብል

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

  4. ከዚምባብዌ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

    በዚህ ዓመት መጨረሻ ከዚምባብዌ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ።

    የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም በዚምባብዌ ሊከሰት የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

    የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዳለው በዓመቲ መጨረሻ ላይ ከአገሪቱ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ።

    በአገሪቱ ይጠበቅ የነበረው የእህል ምርት አልደረሰም። የኑሮ ውድነት እና የኮሮናቫይረስ ስርጭትም ፈተና ሆነዋል።

    ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የሥራ አጦችን ቁጥር ጨምሮታል። በከተማ ረሀብ ከመስፋፋቱም በላይ ለተሻለ ሕይወት ወደ ከተማ የተጓዙ የገጠር ሰዎች ወደ ትውልድ ቀያቸው እየተመለሱ ነው። ገጠር ውስጥ ደግሞ የምግብ እጥረት አለ።

  5. በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 805 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ተገኙ

    አሃዝ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 9786 ናሙናዎች ላይ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 805 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ። ይህም ወረርሽኙ ያለባቸው ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተገኙ ከተገለጸ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

    እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 16 ሺህ 615 ሆኗል።

    የጤና ሚንስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ እንደተመለከተው፤ 10 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም የሟቾችን ቁጥር 263 አድርሶታል።

    78 ተጨማሪ ሰዎች ከህመሙ ያገገሙ ሲሆን፤ ይህም እስካሁን ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 6763 አድርሶታል።

    በአሁን ወቅት በአገሪቱ 134 በጽኑ የታመሙ ሰዎች አሉ።

    ኢትዮጵያ እስከ አሁን 413 ሺህ 397 የላብራቶሪ ምርመራ አካሂዳለች።

  6. በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ምርመራ አነስተኛ ነው

    እስካሁን ድረስ ከአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝቧን የመረመረችው ደቡብ አፍሪካ ነች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የየአገራቱ ጤና ሚኒስትሮች ከሚገልጹት ሊልቅ እንደሚችል በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የተሰማራው አይ አር ሲ ገለፀ።

    አይ አር ሲ በቂ ምርመራ ማድረግ አለመቻልና ተገቢውን መረጃ አለማግኘት "በሽታውን በጨለማ እንደመዋጋት" ነው ሲል አስቀምጦታል።

    ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው 20 የአፍሪካ አገራት " የምርመራው መጠን ከዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ እጅጉን የወረደ" ሲል ገልጾታል።

    በመላው አፍሪካ በሐምሌ ወር በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን በመጥቀስም እናም ይህ "የችግሩ ጫፍ ሊሆን ይችላል" ሲል ስጋቱን ገልጿል።

    በአፍሪካ በአሁኑ ሰዓት 890,000 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

    የዓለም ጤና ድርጅትም በአፍሪካ የሚካሄደው ምርመራ አነስተኛ በመሆኑ አንዳንድ በቫይረሱ የሚያዙ እና በዚሁ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ሳይመዘገቡ ይቀራል ሲል ገልጿል።

    ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞይቲ በዝምታ ሕዝቡን እየገደለ ያለ ወረርሽኝ አለ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

    እንደ አፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጣር ከሆነ ደግሞ አህጉሪቱ ካላት 1.3 ቢሊየን የሕዝብ ብዛት ውስጥ 8.3 ሚሊየኑ ተመርምረዋል።

  7. በሙምባይ የድሃ ሰፈሮች ከግማሽ በላይ ነዋሪዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

  8. ኮሮናቫይረስ፡ የህሙማን ቁጥር ከሆስፒታሎች አቅም እንዳያልፍ የሰጋችው ከተማ

  9. ኬንያ በሊባኖስ በደል ስለሚፈጸምባቸው ዜጎቿ ምርመራ ልታደርግ ነው

  10. በቻይና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል

    አሃዝ

    የፎቶው ባለመብት, CCTV

    በቻይና ላለፉት ሰባት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል። የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያዎች፤ ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉና በአንድ ቦታ እንዳይሰበሰቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው 105 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በቻይና የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩና የማያሳዩ ሰዎች በተለያየ መዝገብ ስለሚያዙ፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይፋ ከተደረገውም በላይ ሊሆን ይችላል።

    አብዛኞቹ ቫይረሱ የተገኘባቸው ኡሩምኪ የተባለች ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። በከተማው ሐምሌ 15፣ የ20 ዓመት ወጣት ቫይረሱ ከተገኘባት በኋላ የጅምላ ምርመራ እየተደረገ ነው። ባለፉት 24 ሰዓታት 96 የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች፤ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    ዴሊያን ሌላው በቫይረሱ በስፋት የተጠቃ ከተማ ቢሆንም፤ ዋነኛ ስጋት የሆነው የሆንክ ኮንግ ጉዳይ ነው።

    እስካሁን ከ3,000 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። የመተንፈሻ አካል ተመራማሪው ዦንግ ናንሻን ሆንክ ኮንግ ውስጥ የጅምላ ምርመራ ያስፈልጋል ብለዋል።

    ራስ ገዟ ሆንክ ኮንግ የቻይናን ጥብቅ እንቅስቃሴ የማቆም ውሳኔ አልተገበረችም።

  11. የኬንያ ትምህርት ቤቶች እስከ ዓመቱ መጨረሻ አይከፈቱም ተባለ

    የኬንያ ትምህርት ሚንስትር ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች እስከ መጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ድረስ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ አስታወቀ።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ ተቋማቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ ባለመቻላቸው ነው።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ጆርጅ ማጎሄ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ተቋማቱ የድረ ገጽ ኮርሶችን፣ ፈተናዎችንና የምረቃ መርሃ ግብሮችን መስጠታቸውን ይቀጥላሉ።

    መሥሪያ ቤታቸው ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ለመጪው ዓመት እንዲከፈቱ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወሰዷቸውን እርምጃዎች መቆጣጠሩን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

    በኬንያ ትምህርት የተቋረጠው አገሪቱ የመጀመሪያውን በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ካገኘችበት መጋቢት ወር ጀምሮ ነው። መንግሥት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም ሙሉ በሙሉ መዝጋቱ ይታወሳል።

  12. አውሮፓ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሰጋታል?

  13. በፓራጓይ በድጋሚ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ተቃውሞ አስነሳ

    በፓራጓይ የተነሳው ተቃውሞ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፓራጓይ መንግሥት በአንዳንድ አገሪቱ ክፍሎች የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀመጡን ተከትሎ ከባድ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰምቷል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲዩዳድ ዴል ኤስቴ በተባለችው ከተማ በሚገኙ ጎዳናዎች በመውጣት ቁጣቸውን ገልጸዋል።

    በርካታ ሱቆች ስለመዘረፋቸውና አንዳንዶቹም ስለመቃጠላቸው ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።

    ጥቂት የማይባሉ የፖሊስ አባላትም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

    ፓራጓይ በመላው አገሪቱ ያለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺ እንዳይበልጥ በሰራችው ስራ ከፍተኛ ምስጋና ተችሯት ነበር።

    ነገር ግን ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት አንዳንድ የጤና አገልግሎት መስጫዎች ከአቅማቸው በላይ እየሞሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

  14. በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትርፉ መጨመሩን ሳምሰንግ አስታወቀ

  15. ጭምብል የማይለብሱ የአሜሪካ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አባላት ይባረራሉ ተባለ

  16. ኮሮናቫይረስ ለምን ጥቁሮች ላይ እንደሚበረታ ሊጠና ነው

  17. "በኮሮናቫይረስ አጎቴን አጥቻለሁ፤ አሁን ደግሞ እኔ ተይዣለሁ"

  18. ፍሎሪዳ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላትን ልትዘጋ ነው

    ፍሎሪዳ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ በእጅጉ በኮሮናቫይረስ ከተጠቁ ግዛቶች አንዷ የሆነቸው ፍሎሪዳ ወደ ግዛቲቱ እየመጣ ባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ምክንያት የኮቪድ-19 የምርመራ ማዕከላትን ልትዘጋ እንደሆነ አስታውቃለች።

    ''ሁሉም ማዕከላት ወደውስጥ ያልተቀበሩ መደገፊያዎችና ድንኳኖች የሚበዙባቸው በመሆናቸው የሚመጣውን አደጋ መቋቋም አይችሉም፤ በዚህ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ'' ብለዋል የግዛቲቱ ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያ ቢሮ ኃላፈዎች።

    መመርመሪያ ማዕከላቱ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግተው እንደሚቆዩም ተገልጿል።

    የአሜሪካ ኃላፊዎች እንዳስጠነቀቁት አውሎ ነፋሱ በሰአት 80 ኪሎሜትር የሚጓዝ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ፍሎሪዳ ሊደርስ ይችላል።

    21 ሚሊዮን ነዋሪ የሚገኝባት ፍሎሪዳ እስካሁን 450 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን 6300 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ከነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ አንድ አራተኛን ቁጥር የሚእዙት ሰዎች ማያሚ ውስጥ ነው የሚገኙት።

  19. የጋምቢያው ፕሬዝዳንት ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደገቡ ገለፁ

    የጋምቢያው ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጋምቢያው ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው ራሳቸውን ለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብተዋል። ይህም የሆነው ምክትል ፕሬዚዳንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ነው።

    ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ሳምንት ያህል ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋርጣሉ፤ በመንግሥታዊ ተግባርም አይሳተፉም ተብሏል።

    ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሳቱ ቱራይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ነው።

    ኢሳቱ ቱራይ "ጤንነታቸው በደህና ሁኔታ ላይ እንደሆነና ለይቶ ማቆያ እገባለሁ" ብለዋል።

    በጋምቢያ እስካሁን ድረስ 326 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    መንግሥትም ዜጎች ጭምብል እንዲያጠልቁና አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት እንዲገቱት ጥሪ እያደረገ ነው።

  20. እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች!

    አበቦች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    ኮሮረናቫይረስን በተመለከተ ወደናንተ የተለያዩ መረጃዎችን የምናቀርብበት ዕለታዊ የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ተጀምሯል።

    በዓለማችን ላይ በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 17 ሚሊየን እየተጠጋ ሲሆን ከ600 ሺ በላይ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    እናንተም እራሳችሁን እና ወዳጆቻችሁን ከቫይረሱ ለመከላከል በመንግስት የተቀመጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንድትከሉ ለማሳሰብ እንወዳለን።

    አብራችሁን ቆዩ!