በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡ ተገለፀ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተዛምቶ የሁሉም ዋነኛ የህልውና ስጋት ሆኗል። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት ቀላል የመከላከያ መንገዶችን በመከተል በሽታውን መከላከል ይቻላል። እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና በተቻለ መጠን በርካታ ሰው ከሚሰበሰብበት ቦታ እራስን ማራቅ በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ እርምጃ ናቸው። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የተለያዩ ዜናና መረጃን ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በቀጥታ ዘገባ እዚህ ገጽ ላይ ያቀርባል። አብራችሁን በጤና ቆዩ!

የቀጥታ ሽፋን

  1. “ፈረንሳዊያኑ ‘የቫይረሱ ክትባት በአፍሪካ መሞከር አለበት’ ማለታቸው ያበሳጫል”- የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ፈረንሳዊው ዶክተር የኮሮናቫይረስ ክትባት በአፍሪካ ይሞከር ማለታቸውን አወገዙ።

    ፈረንሳዊው ዶክተር፤ "ይህንን ሙከራ ማድረግ ያለብን አፍሪካ አይደለምን? የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) በሌለበት፣ ህክምና በላደገበትና፣ መተንፈስ ቢያዳግት እንኳን ትንፋሽ መመለስ የሚያስችል መሳሪያ በሌለበት መሆን አይገባውም?" ብለዋል።

    ጨምረውም "ልክ በአፍሪካውያን የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎች ላይ የኤድስ ጥናት እንደተሞከረባቸው። ምክንያቱም ራሳቸውን መጠበቅ እንደማይችሉምና፤ በጣም ተጋላጭ እንደሆኑ እናውቃለን” ሲሉ ነበር ዶ/ር ጂን ፖል ሚራ በቴሌቪዥን በተካሄደ ውይይት ላይ የተናገሩት።

    በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩትና የኢንሰርም የጥናት ቡድንን ወክለው የተገኙት ካሚሌ ሎችትም በዶክተሩ ሃሳብ ተስማምተዋል።

    ታዲያ ይህ ዘረኛ የተባለው ንግግራቸው በርካቶችን አስቆጥቷል።

    በዶክተሩ ንግግር ከተበሳጩት መካከል ታዋቂዎቹ አፍሪካዊያን እግር ኳስ ተጨዋቾች ዲዲየር ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶም ይገኙበታል።

    “ንግግሩ ዘረኝነት የተሞላበት እና አፍሪካውያንን እንደ የቤተ ሙከራ አይጦች የቆጠረ ነው” ሲሉ ነቅፈውታል።

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳሬክተር ዶ/ር ማሺዲሶ ሞቲም በትዊተር ገጻቸው ላይ ንግግሩን በጥብቅ አውግዘዋል።

    ዶ/ር ጂን ትናንት መስሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ላይ በንግግራቸው ክፉኛ የተጎዱትን በሙሉ “ይቅር በሉኝ!” ብለዋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  2. ሰበር, በኢትዮጵያ የ85 ዓመቷ አዛውንት ከኮሮናቫይረስ መዳናቸው ተነገረ

    የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

    የፎቶው ባለመብት, ፋና

    በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው ከተነገሩ ሰዎች መካከል አንዷ የነበሩት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ መዳናቸው ተነገረ።

    የጤና ጥበቃ ባወጣው መረጃ መሰረት ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በህክምና ላይ የነበሩት የ85 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት አዛውንት "አገግመዋል" ብሏል።

    አክሎም የ85 ዓመቷን አዛውንት ጨምሮ እስካሁን በሽታው እንደተገኘባቸው ከተነገረው 38 ሰዎች መካከል አራት ሰዎች ከቫይረሱ መዳናቸው ተነግሯል።

    በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ዛሬ በሦስት ጨምሮ 38 መድረሱን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 89 ሰዎች መካከል 86ቱ ከቫይረሱ ነጻ ሲሆኑ ሦስት ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ይህም ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ምርመራ ተደርጎላቸው በሽታው የተገኘባቸውን ሰዎች ቁጥርን 38 አድርሶታል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸው ሦስቱም ግለሰቦች የውጭ አገሮች ጉዞ ታሪክ ያላቸውና ሁሉም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።

    ከመካከላቸው አንደኛው ግለሰብ የ29 ዓመት ወንድ ሲሆን መጋቢት 10 ቀን ከዱባይ የመጣና በበሽታ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው መሆኑ የተነገረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የ34 ዓመት እድሜ ያለው ወንድ መጋቢት 23 ከዱባይ የመጣና በማቆያ የነበረና ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው መሆኑ ታውቋል።

    ሦስተኛዋ የ35 ዓመት እድሜ ያለት ሴት መጋቢት 25 ከሲዊዲን ወደ አዲስ አበባ የመጣችና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለች መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

  3. በስፔን በ24 ሰዓታት ውስጥ 800 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ተነገረ

    በስፔን የቫይረሱ ስርጭት መረጋጋት ያሳያል የሚል ተስፋ ተጥሏል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ለሳምንታት በእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ባለችው ስፔን፤ ባለፉት 24 ሰዓታት 809 ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

    ይህም የሟቾቹን ቁጥር 11 ሺህ 744 አድርሶታል።

    እስካሁን 124 ሺህ 736 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህ ቁጥር በቫይረሱ ክፉኛ እየተጎዳች ካለችው ጣሊያንም የበለጠ ነው ተብሏል።

    ስፔን ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየታገለች ሲሆን ባለፉት ሦስት ቀናት በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ900 በታች ወርዷል።

  4. ቀነኒሳ ሕዝቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጠበቀ ስላልሆነ አሳስቦኛል አለ

    ቀነኒሳ በቀለ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኦሎምፒክ አሸናፊውና የአምስት ሺህና የአስር ሺህ ክብረወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ማኅበረሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች በሥራ ላይ እያዋለ አይደለም ሲል ስጋቱን ለቢቢሲ ተናገረ።

    የዓለም ሕዝብ እንደ ቅጠል እየረገፈ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሱን ከወረርሽኙ መጠበቅ ቢኖርበትም ይህ እየተተገበረ አለመሆኑ እንዳሳሰበው አትሌት ቀነኒሳ ገልጿል።

    ጨምሮም "ሕዝቡ በባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ ራሱን የማይጠብቅ ከሆነ አገሪቱ ትልቅ ፈተና ሊገጥማት ይችላል" በማለት አሳስቧል።

  5. ደቡብ ኮሪያ አካላዊ ርቀትን መጠበቅን በሁለት ሳምንት አራዘመች

    ደቡብ ኮሪያውያን በባቡር እየሄዱ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ደቡብ ኮሪያ በአገሯ ያለው የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ባለመቆሙ የተነሳ አካላዊ እርቀትን መጠበቅን ለተጨማሪ ሁለት ሳምንት አራዘመች።

    የጤና ሚኒስትር የሆኑት ፓርክ ኒዩንግ ሁ እንዳሉት፣ በአገሪቱ በቫይረሱ በቀን ውስጥ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 50 ወይንም ከዚያ በታች እስካልሆነ ድረስ የተቀመጡት ገደቦች አይነሱም ብለዋል።

    ዛሬ እንደተገለፀው 94 ሰዎች መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥርን ወደ 10,156 ከፍ ሲያደርገው እስካሁን ድረስ ደግሞ 177 ሞቶች ተመዝግበዋል።

    ደቡብ ኮሪያውያን አንዳቸው ከአንዳቸው የሚኖራቸው እርቀት ቢያንስ ሁለት ሜትር እንዲሆን የተደነገገው ቫይረሱ መከሰቱ እንደታወቀ ሲሆን በተጨማሪም ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይደረጉ ተከልክሏል።

    በርካታ አገራት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ቤት ውስጥ መቀመጥን ቢደነግጉም በደቡብ ኮሪያ ግን አሁንም ምግብ ቤቶችና የገበያ ስፍራዎች ክፍት ናቸው።

    ደቡብ ኮሪያ የቫይረሱን ወረርሽኝ በፍጥነት በመቆጣጠር ረገድ በሰፊው ብትወደስም የጤና ሚኒስትሩ ግን "ገደቦቹን ለማንሳት ጊዜው ገና ነው" ብለዋል።

  6. ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ከተባበርን የኮቪድ-19 ስርጭትን ማስቆም እንችላለን እያለች ነው

    የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር እያንዳንዱ ሰው በየደቂቃው የሚወስዳቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ወሳኝ እንደሆኑ የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

    በሽታውን ለመከላከል ቀላልና ማንም ሊፈጽማቸው የሚችላቸውን የጥንቃቄ መንገዶች ያለመዘናጋት ተግባራዊ ማድረግ እራሳችንንና በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን እንጠብቅ።

    የእጃችንን በተደጋጋሚ በአግባቡ መታጠብ፣ አፍ፣ አፍንጫ፣ ዓይናችንና ፊትን አለመነካካት እንዲሁም የሚቻል ከሆነ ከቤት አለመውጣት ካልሆነ ደግሞ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ላይ አለመገኘት፤ በሽታውን ለመከላከል መፍትሄዎች ናቸው።

    ታዋቂዋ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደም እነዚህን ነገሮች በመፈጸም እራሳችንን እንድንጠበቅ ተደጋጋሚ መልዕክቶችን እያስተላለፈች ነው።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  7. አዲስ አበባ ውስጥ የእንቅስቃሴ እገዳ አይኖርም ተባለ

    ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

    የፎቶው ባለመብት, AA PRESS SECRETARY

    የምስሉ መግለጫ, ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲቆም እንደማይደረግ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።

    በዚህም በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችና የትራንስፖርት አገልግሎቶች በሽታውን ከመከላከል አንጻር የሚያስፈልጉ ማስተካከያዎች እየተደረጉባቸው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

    ምክትል ከንቲባው ይህንን ያስታወቁት የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር መደረግ ያለባቸውን የጥንቃቄ ሥራዎች የከተማው መስተዳደር እየሰራ መሆኑን በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት ጊዜ ነው።

    ኢንጂነር ታከለ በተለይ ለበሽታው መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥሩ ይችላል ተብሎ በሚታሰበው የትራንስፖርት አገልገሎት በኩል ታክሲዎች ትርፍ ሰው እንዳያሳፍሩ ከመቆጣጠር በተጨማሪ የከተማ አውቶብሶች ባላቸው መቀመጫ ልክ ብቻ እንዲሁም ቀላል ባቡሮች ደግሞ በግማሽ አቅማቸው ብቻ ተሳፋሪዎችን እንዲይዙ መደረጉን አመልክተዋል።

    ኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ባሕር ዳርና አንዳንድ ከተሞች ለተወሰኑ ቀናት የእንቅስቃሴ ዕገዳ የጣሉ መሆናቸው ተነግሯል።

  8. “ኒው ዮርክ አደጋ ላይ ናት፤ ኒው ዮርክን እንታደግ”

    የጤና ባለሙያ በአሜሪካ ጎደና ላእ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በአንድ ቀን ውስጥ ከተመዘገበው የሞት ቁጥር ከፍተኛውን መዘገበች።

    አሁን ከአሜሪካ እየተሰማ ያለው መረጃ አሳዛኝ ሆኗል፤ አሜሪካ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 1,100 ሰዎችን በቫይረሱ አጥታለች።

    ይህም እስካሁን በሌሎች አገራት በአንድ ቀን ውስጥ ከተመዘገበው የሞት ቁጥር ከፍተኛው ነው።

    የኒው ዮርክ ግዛት ደግሞ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁት ቀዳሚዋ ናት።

    በግዛቷ ትናንት የነበረው 2,373 የሟቾች ቁጥር ወደ 2,935 ከፍ ብሏል።

    ይህንንም ተከትሎ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አንድሪው ኮሞ፤ “ኒው ዮርክ አደጋ ላይ ናት፤ ኒው ዮርክን እንታደግ” ሲሉ የሌሎች ግዛቶችን እርዳታ ጠይቀዋል።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፤ በአሜሪካ እስካሁን 278,458 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 7,000 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  9. አሜሪካ የጀርመንን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ‘በመውሰድ’ ተከሰሰች

    የጀርመን ወታደሮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያዘውን እሽግ ሲከፍቱ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ለጀርመን የተዘጋጀ 200 ሺህ የፊት ጭምብል (ማስክ) ወደ ራሷ በማዞር ተከሰሰች፤ ድርጊቱ "ዘመናዊ ወንበዴነት" በሚልም ተወግዟል።

    በአሜሪካ የተሰሩት የፊት ጭምብሎች በታይላንድ ባንኮግ መያዛቸውን የበርሊን መንግሥት አስታውቋል።

    ኤፍኤፍፒ2 የተሰኙት እነዚህ ጭምብሎች የተዘጋጁት በበርሊን የፖሊስ ኃይል ትዕዛዝ የነበረ ቢሆንም በእጃቸው ሳይገባ ቀርቷል።

    የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪያስ ጌሴል፤ ጭምብሎቹ ወደ አሜሪካ ሳይመለሱ እንዳልቀሩ ተናግረዋል። ተጨማሪ ለማንበብ፡ አሜሪካ የጀርመንን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ‘በመውሰድ’ ተከሰሰች

  10. በዩናይትድ ኪንግደም ምን አዲስ ነገር ተሰማ?

    የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣን

    በዩናይትድ ኪንግደም ተጨማሪ 684 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ይህም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር 3 ሺህ 605 አድርሶታል። እስካሁን 38 ሺህ 168 ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    • የአየር ንብረቱ ፀሐያማ ይሆናል ተብሎ ስለሚጠበቅ ሰዎች ቅዳሜና እሁድን በቤታቸው እንዲያሳልፉ መንግሥት አሳስቧል።
    • ሁለት ነርሶች በቫይረሱ መሞታቸውን ተከትሎ፤ የእንግሊዝ የነርሶች ኃላፊ “እባካችሁ ለእነርሱ ስትሉ ከቤታችሁ አትውጡ!” ሲሉ ሕዝቡን ተማጽነዋል።
    • የጤና ሚኒስተሩ ማት ሃንኮክ፤ ቀድሞ የነበሩ መድኃኒቶች ቫይረሱን ለማከም እንዴት እንደሚረዱ ለመመልከት ጭምር በሦስት ዋና የጤና ተቋማት ለሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች ጥሪ አቅርበዋል።
    • ንግሥቲቱ እሁድ ምሽት ለሕዝቡ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
  11. የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ከጤና ቀውስ በላይ ነው አለ

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ኮቪድ-19 ከጤና ቀውስ በላይ ነው አሉ።

    ዶ/ር ቴድሮስ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደጠቀሱት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊየን በላይ መሆኑን እንዲሁም በቫይረሱ ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ50ሺህ ማለፉን በመጥቀስ ኮቪድ-19 ከጤና ቀውስ በላይ መሆኑን እንረዳለን ብለዋል።

    አክለውም የወረርሽኙን ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ እናውቃለን ካሉ በኋላ፤ በርካታ አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ያስቀመጡት ከቤት ያለመውጣት ገደብ የበርካቶችን ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል ብለዋል።

    ይህ የማኅበረሰብና የአገራትን ምጣኔ ሃብት ላይም ተጽዕኖ እንዳለው አስታውቀዋል።

    ሕይወትንና ኑሮን ለመታደግ በጋራ ትግል ላይ ነን ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አገራት የጣሉትን የመንቀሳቀስ ገደብ አላልተው የተቸገሩ ሕዝቦች የሚበሉት ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ሊያሟሉላቸው ይገባል ብለዋል።

  12. ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የበኩላቸውን ያደረጉ አፍሪካዊ ጀግኖች

    በደቡብ አፍሪካ የአበባ መሸጫ ሠራተኞች የአዛውንቶችን መቆያ በአበባ አስውበዋል

    የፎቶው ባለመብት, Adene's Farm Flowers

    በዚህ በኮሮና ዘመን ልብን የሚያሞቅ፣ መተሳሰብን የሚያደረጅ ታሪክ ከአፍሪካውያን መንደር ሰምተናል። አፍሪካዊያን ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተጨነቀችበትን ይህን ጊዜ በማሰብ፤ ሌሎችን ለመርዳት አስገራሚ በጎ ተግባራት እያከናወኑ ነው። ከእነዚህ ጀግኖች መካከል የተወሰኑትን ታሪክ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የበኩላቸውን ያደረጉ አፍሪካዊ ጀግኖች

  13. ባለስልጣኑ ወደ ለይቶ ማቆያ አልገባም በማለታቸው ታሰሩ

    የኪሊፊ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ጌዲዮን ሳቡሪ

    የፎቶው ባለመብት, GIDEON SABURI

    አንድ የኬንያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ከውጭ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ማንኛው ሰው መፈጸም ያለበትን ወደ ለይቶ ማቆያ የመግባት ግዴታን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታሰሩ።

    የባሕር ዳርቻ የኬንያ ግዛት ኪሊፊ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ጌዲዮን ሳቡሪ በግድ ወደ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት ከገቡ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።

    ባለስልጣኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከተገኙባት ጀርመን ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ወደ ኬንያ የተመለሱት።

    ምክትል አስተዳዳሪው በአሁኑ ወቅት ከበሽታው ሙሉ በሙሉ በመዳናቸው የኬንያ መንግሥት ያወጣውን ደንብ ተላልፈዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት። ተጨማሪ ለማንበብ ኮሮናቫይረስ፡ ባለስልጣኑ ወደ ለይቶ ማቆያ አልገባም በማለታቸው ታሰሩ

  14. 'ወሲብ ብፈጽም ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል?'

    ስዕል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    'ወሲብ ብፈጽም ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል?' በእርግጠኝነት ይህ ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ቢያቃጭልም ለመጠየቅ ግን እንሸማቀቃለን።

    ሃቅንና ብዥታን ለመለየት ጥያቄዎን ለጤና ሙያዎች በማቅረብ ቢቢሲ ተገቢውን ምለሽ አግኝቷል።

    የቀድሞው የላቭ አይላንድ አወዳዳሪ ዶ/ር አሌክስ ጆርጅ እና የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ አሊክስ ፎክስ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል። በጥያቄዎቹ ዙሪያ ሁለቱም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    ምላሹን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ ወሲብና ኮቪድ-19ን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች

  15. ቻይና በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎችን በሕሊና ፀሎት አሰበች

    ቻይናዊያን ለሦስት ደቂቃ በወረርሽኙ የሞቱ ወገኖቻቸውን አሰቡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ቻይናዊያን ለሦስት ደቂቃ በወረርሽኙ የሞቱ ወገኖቻቸውን አሰቡ

    ቻይና በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎችን በደቂቃዎች የሕሊና ፀሎት አሰበች። ይህም በመላው አገሪቱ ተፈፃሚ የሆነ ሲሆን ሁሉም በያለበት ለሦስት ደቂቃ ያህል ቆሞ የሞቱ ወገኖቹን አስቧል።

    በቻይና ከ3ሺህ 300 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሲሆን እነዚህን ዜጎች አስቦ ለመዋል እንዲቻል አንድ ቀን ተሰይሞላቸዋል።

    በዚህም መኪኖች፣ ባቡሮችና መርከቦች ጥሩምባቸውን ያሰሙ ሲሆን የአገሪቱ ሰንደቅ አላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል።

    በቻይና ዉሃን የትራፊክ መብራት ቀይ ሆኖ የቆየ ሲሆን ለሦስት ደቂቃ ያህልም የትራፊክ እንቅስቃሴ ተገትቶ ነበር።

    በቻይና የመጀመሪያው በኮቪድ-19 የተያዘው ሰው የተገኘው በሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ ነበር።

    ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙ ላለፉት ሦስት ወራት በመላው ዓለም በመሰራጨት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 60 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    እስካሁን ድረስ 181 የዓለማችን አገራት ቫይረሱ ያለበትን ሰው ማግኘታቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

    የቻይና መንግሥት ይህ “ሰማዕታቶችን” ለማሰብ እድል ይሰጠናል፤ ያለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ብሎ ወረርሽኙን ለመግታት የሕክምና እርዳታ በመስጠት ሳሉ የሞቱ 14 የጤና ባለሙያዎችን "ሰማዕታት" በሚል ስማቸውን ማስፈሩ ይታወሳል።

  16. የምር ግን ኮሮናቫይረስ ያልገባበት አገር ይኖር ይሆን?

    ደሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር በቻይና ተገኘ ተባለ። አንድም ሰው ከቻይና ውጭ አልተያዘም ነበር ያኔ። ከጥር ወር አጋማሽ በኋላም ወረርሽኙ ከቻይና ውጭም እንዳለ ተነገረ።

    መጀመርያ በታይላንድ፣ ከዚያም በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በአሜሪካ ተገኘ ተባለ። አሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓለም ዙርያ በወረርሽኙ ተይዘዋል።

    ከኔፓል እስከ ኒካራጓ፣ ከኢኳዶር እስከ ኢትዮጵያ በሽታው ያልገባበት የለም ማለት ይቻላል፡። የሆስፒታል አልጋዎች ሞልተዋል፤ አገሮች ለደቂቃ አስበውት የማያውቁት የፊት ጭምብል እንኳ አንሷቸዋል።

    የምር ግን ኮሮናቫይረስ ያልገባበት አገር ይኖር ይሆን? በሚገርም ሁኔታ መልሱ "አዎ" ነው።

  17. የአርብ ዕለት የቀጥታ ዘገባችንን ለመመልከት ወደ ታች ይውረዱ

    እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች። የቅዳሜ ዕለቱን የቀጥታ ዘገባችንን ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን። የትናንት አርብ ዘገባዎቻችንን ለመመልከት ወደታች በመውረድ መመልከት ትችላላችሁ።

  18. የዛሬን በዚህ ቋጨን

    ቢቢሲ አማርኛ

    የዛሬን በዚህ ቋጭተናል

    ነገ ጠዋት በቀጥታ ዘገባችን እንመለሳለን።

    አብራችሁን ስለቆያችሁ እናመሰግናለን።

  19. አንጌላ መርክል ወደ ሥራቸው ተመለሱ

    Angel Merkel

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጀርመኗ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወደ ሥራ ገበታቸው ተመለሱ።

    አንጌላ ሜርክል የተለይቶ መቆያ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መመለሳቸው ተገልጿል።

    የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ለ12 ቀናት ራሳቸውን አግልለው ከቆዩ በኋላ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰዋል።

    ከ14 ቀናት በፊት የሳንባ ምች ክትባት ከወሰዱ በኋላ ክትባቱን የሰጣቸው ዶክተር በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋግጦ ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ አንጌላ መርክል ራሳቸውን ለይተው ከቤታቸው ስራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

    በጀርመን እስካሁን 1,107 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

  20. የዉሃን ነዋሪዎች ወደ ጎዳናዎች እየወጡ ነው

    የኮሮናቫይረስ የተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ነዋሪዎች ወደ ጎዳናዎች እየወጡ ነው።

    በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ነዋሪዎች ለሁለት ወራት ከቤት ሳይወጡ ቆይተው ነበር።

    ትናንት እና ዛሬ በዉሃን ግዛት የነበረው ገጽታ ይህን ይመስላል።

    ዛሬ በዉሃን ከተማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዛሬ በዉሃን ከተማ
    Wuhan China

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    Wuhan China

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images