በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡ ተገለፀ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተዛምቶ የሁሉም ዋነኛ የህልውና ስጋት ሆኗል። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት ቀላል የመከላከያ መንገዶችን በመከተል በሽታውን መከላከል ይቻላል። እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና በተቻለ መጠን በርካታ ሰው ከሚሰበሰብበት ቦታ እራስን ማራቅ በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ እርምጃ ናቸው። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የተለያዩ ዜናና መረጃን ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በቀጥታ ዘገባ እዚህ ገጽ ላይ ያቀርባል። አብራችሁን በጤና ቆዩ!

የቀጥታ ሽፋን

  1. ደቡብ አፍሪካ ከ47 ሺህ በላይ ሰዎችን ብትመረምርም የወረርሽኙን ሙሉ ምስል ለማወቅ የበለጠ ምርመራ ያስፈልጋል አለች

    የደቡብ አፍሪካ የጤና ባለሙያዎች አየመረመሩ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአገሪቱ ውስጥ እየተዛመተ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልግ የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር አስታወቁ።

    ሚኒስትሩ ዝዌሊ ምክሂዜ እንደገለፁት ደቡብ አፍሪካ 47ሺ541 በኮሮና የተጠረጠሩ ሰዎችን የመረመረች ቢሆንም የወረርሽኙ መዛመት አለመዛመት ሙሉ ምስሉን ለማግኘት የበለጠ መሰራት አለበት ብለዋል።

    "በፍጥነት ሥራዎችን ካላከናወንን ሊያጥለቀልቀን ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።

    እስካሁን ባለው መረጃም በአገሪቷ ውስጥ 1ሺ462 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ሃገሪቷም ለ21 ቀናት እንቅስቃሴ በማገድ ሁሉን የመዝጋት ውሳኔ አስተላልፋለች።

    በተለይም በሰኔ ወር የሚከሰተውን የጉንፋን (ኢንፍሉዌንዛ) በሽታንም ተከትሎ በርካታ ህመምተኞች ወደ ጤና ማዕከላት ሊጎርፉ እንደሚችሉ ጠቁመው ይሀም ሁኔታ የኮሮና መዛመትን እንደሚጨምረውም ፍራቻቸውን ሚኒስትሩ አጋርተዋል።

    "ከጊዜ ጋር ሩጫ ነው የተያያዝነው" ያሉት ሚኒስትሩ "አገሪቱ መረጋጋት ላይ ብትሆንም ከፍተኛ ማዕበል ሊያጋጥም ይችላል" በማለት አስረድተዋል።

    እስካሁን እየመረመሩ ያሉት ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ቢሆንም በቀጣይነት ወደ ተጨናነቁ መንደሮች በመሄድ ምርመራ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

    ደቡብ አፍሪካ ካሏት ቋሚ መመርመሪያዎች በተጨማሪ 67 ተንቀሳቃሽ መመርመሪያ ተሽከርካሪዎችንም መድባለች።

    ግለሰቦች ምልክቱ ታይቶባቸው ወይም ታመው ወደ ሆስፒታሎች ከመምጣታቸው በፊትም በየአካባቢያቸው ቢመረመሩ ወረርሽኙ የደረሰበትን ደረጃ መረዳት ያስችላል ብለዋል።

  2. በፓኪስታን በአንድ ቀብር ላይ የተገኙ ሃዘንተኞች በፖሊስ ተያዙ

    ቀብራቸው የተፈጸመው እናት

    የፎቶው ባለመብት, FAMILY

    የምስሉ መግለጫ, ቀብራቸው የተፈጸመው እናት

    ፓኪስታን ያወጀችውን ከቤት ያለመውጣት አስገዳጅ ሕግን ተላልፈው ቤተሰባቸውን ሲቀብሩ የተገኙ ሃዘንተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

    ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የዶክተር አንጁም ማህሙድ ቤተሰቦች ናቸው።

    ዶክተሩ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱትን እናቱን ሊቀብሩ በሄዱበት ወቅት ቀብር ላይ መላ ቤተሰቡ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    አንዳንድ ዘመዶቹም ከቤት ውጭ በር ተቆልፎባቸው በፖሊስ እየተጠበቁ እንደሚገኙ ዶክተሩ ለቢቢሲ አስረድቷል።

    የአካባቢው ባለስልጣናት ሃያ የሚሆኑ የቤተሰቡ አባላት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

    ቤተሰቦቹም ሆነ እሱ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ ሲሆን ወደ ፓኪስታን ያቀኑትም ለሠርጉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመሸመት በሚል ነበር።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባይከሰት የሠርጉ ቀን የተቆረጠው መጋቢት ወር ላይ ነበር።

    በፓኪስታንም ቆይታቸው እናቱ በቫይረሱ ሞቱ፤ በነገታው ለቀብር በወጡበት ጊዜ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ተጨማሪ ለማንበብ በፓኪስታን በአንድ ቀብር ላይ የተገኙ ሃዘንተኞች በፖሊስ ተያዙ

  3. የትኛው አገር ቢሄዱ ከኮሮናቫይረስ ያመልጣሉ?

    በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ያለችው የቱቫሉ ደሴት አንድ ክፍል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር በቻይና ተገኘ ተባለ። አንድም ሰው ከቻይና ውጭ አልተያዘም ነበር ያኔ።

    ከጃንዋሪ 13 ወዲህ ከቻይና ውጭም አለ ተባለ። መጀመርያ በታይላንድ፣ ከዚያም በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በአሜሪካ ተገኘ ተባለ።

    አሁን አንድ ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ዙርያ በወረርሽኙ ተይዘዋል።

    ከኔፓል እስከ ኒካራጓ፣ ከኢኳዶር እስከ ኢትዮጵያ በሽታው ያልገባበት የለም ማለት ይቻላል፡። የሆስፒታል አልጋዎች ሞልተዋል፤ አገሮች ለደቂቃ አስበውት የማያውቁት የፊት ጭምብል እንኳ አንሷቸዋል።

    የምር ግን ኮሮናቫይረስ ያልገባበት አገር ይኖር ይሆን?

    በሚገርም ሁኔታ መልሱ "አዎ" ነው።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት 193 ናቸው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ 19 አገራት ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር በአገራችን አይተንም ሰምተንም አናውቅም ይላሉ።

    እነዚህን አገራት መዘርዘር ይቻላል። ብዙዎቹ ስማቸው ለጆሮም ለአይንም እንግዳ ነው።

    ኮሞሮስ፣ ኪሪባቲ፣ ሌሶቶ፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሮኒሺያ፣ ናዉሩ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓላዉ፣ ሳሞዋ፣ ሳዎ ቶሜና ፕሪንሲፔ፣ ሶሎሞን ደሴቶች፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታጃኪስታን፣ ቶንጋ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ቱቫሉ፣ ቫኑዋቱና የመን ናቸው። ዝርዝሩ እዚህ ይገኛል የትኛው አገር ቢሄዱ ከኮሮናቫይረስ ያመልጣሉ?

  4. የዓለም ባንከ ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መዛመትን ለመግታት የሚያግዛትን የ82.6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

    የጥበቃ ሰራተኛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መዛመት ለመግታት ለምታደርገው ጥረት የ82.6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የዓለም ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻለ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት የቻለች ቢሆንም፤ ለብዙ አገራት ፈታኝ የሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ያለውን የኅብረተሰብ ጤናም ሆነ አገሪቷ ያላትን የጤና ሽፋን የሚፈትንና ኢኮኖሚዋን አጣብቂኝ ውስጥ ሊከተው ስለሚችል ልገሳው ይህንን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።

    'የአስቸኳይ ጊዜ መከላከልና ዝግጁነት' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት አገሪቷ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም ለወረርሽኙ ያላትን ዝግጁነትም የሚያጠናክር እንደሆነም መግለጫው አትቷል።

    ገንዘቡም ለኮሮናቫይረስ መከላከያነት የሚውሉ የህክምና እቃ ግዢዎች፣ ለበሽታው ምርመራና ማሰልጠና፣ አገሪቷ ውስጥ የሚገቡ መንገደኞችን የሚመረምሩ መሳሪያዎች፣ ለይቶ ማቆያዎችንና የህክምና ማዕከላትን ለመገንባት ይውላል ተብሏል።

    ከዚህም ውስጥ 41.3 ሚሊዮን ዶላሩ በልገሳ የተሰጣት ሲሆን፣ ሌላኛው ግማሽ 41.3 ሚሊዮን ዶላር በብድር እንደሆነ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ገንዘቡ የተገኘው ከዓለም አቀፉ ልማት ማኅበር ነው።

  5. በናይጄሪያ 11 የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች በመዳናቸው ከሆስፒታል ወጡ

    በናይጄሪያ 11 ታማሚዎች አገገሙ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በናይጄሪያ 11 ታማሚዎች አገገሙ

    በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ቀድሞ ሪፐርት ከተደረገባቸው አገራት መካከል ናይጄሪያ አንዷ ናት።

    በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸው ተረጋግጦ በሆስፒታል እርዳታ ሲደረግላቸው የነበሩ 11 ታማሚዎችን ናይጄሪያ ከሆስፒታል አስወጥታለች። ታማሚዎቹ ከሆስፒታል እንዲወጡ የተደረገው ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ መዳናቸው ተረጋግጦ ነው።

    የአገሪቱ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ዛሬ 11 ታማሚዎችን ከሆስፒታል ያስወጣ እንጂ በሌላ በኩል ደግሞ 10 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘቱን አስታውቋል። ይህም አጠቃላይ በናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ቁጥር ወደ 180 ከፍ አድርጎታል።

    የናይጄሪያ ባለስልጣናት እንዳሉት በቀን የሚደረገውን የመመርመር አቅም ማሳደጋቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ እስከ 1 ሺህ 500 ሰዎችን መመርመር እንደሚቻል ተናግረዋል።

    የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ኦሳጌ ኢሃኒር ቫይረሱ በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ቀናት ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል።

    በዚህም ምክንያት ቫይረሱ ከነበረነባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል የተባሉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ተጠናክሯል።

  6. ኤርትራ የኮሮናቫይረስን መዛመትን ለመቀነስ የፖለቲካ እስረኞችን እንድትፈታ ተጠየቀ

    ኤርትራውያን እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ሰልፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኤርትራ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ለመከላከል የፖለቲካ እስረኞችንና ቀለል ያለ ወንጀል ያለባቸውን ቅድሚያ በመስጠት የተጨናነቁ እስር ቤቶቿን ከስጋት ነፃ ማድረግ እንዳለባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ባለሙያ ተናገሩ።

    ከዚህም በተጨማሪ ህመም ያለባቸው እንዲሁም በእድሜ ገፋ ያሉትንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትፈታ ጠይቀዋል።

    በኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ የሆኑት ዳንኤላ ክራቬትዝ በምሳሌነትም የቀድሞ የማስታወቂያ ሚኒስትር ልጅ አሜሪካዊ-ኤርትራዊቷ ታዳጊ እስር ቤት የገባችው ገና በ15 ዓመቷ መሆኑን ጠቅሰው ለሰባት ዓመታትም ያህል ያለምንም ፍትህ በእስር ቆይታለች ብለዋል።

    ሲሃም አሊ አብዱ አባቷ በሌላ አገር ጥገኝነት መጠየቃቸውን ተከትሎ ወደ ሱዳን ልታመልጥ ስትል ነው በቁጥጥር ስር የዋለችው። እስካሁንም ድረስ ቤተሰቦቿ ስለሁኔታዋ ምንም መረጃ የላቸውም።

    በተደጋጋሚ እንዲፈቷት ባለስልጣናቱ ቢጠየቁም አሻፈረኝ ማለታቸውን ዳንኤላ ገልፀዋል።

    "ለኤርትራ ባለስልጣናት የማስተላልፈው መልዕክት ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው እንዲሁም የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ነው። በዚህም ሁኔታ በእስር ቤት ሊከሰት የሚችለውን የወረርሽኝ መዛመትንም ለመቀነስ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል" ብለዋል።

    በኤርትራ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በእስር ላይ ከዋሉ ሁለት አስር ዓመታት ያለፋቸው ሲሆን፤ በዓመታትም ውስጥ በምግብ እንዲሁም በህከምና እጥረት ብዙዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል።

    በባለፈው ዓመትም ከሁለት መቶ በላይ ግለሰቦች በሃይማኖት አመለካከታቸው ምክንያት እስር ቤት ገብተዋል።

    በኤርትራ ውስጥ 22 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ አገሪቷም ለሦስት ሳምንታት ያህል ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ ውሳኔ አስተላልፋለች።

  7. እስካሁን ኮሮናቫይረስ ያልተገኘባት ማላዊ የመጀመሪያዎቹን ህሙማንን አገኘች

    በማላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በማላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

    ለረጅም ጊዜ ቫይረሱ ካልደረሰባቸው አገራት ተርታ ተሰልፋ የነበረቸው ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ ዛሬ ቢያንስ ሦስት የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ማግኘቷን አስታውቃለች።

    የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ እንዳስታወቁት ሦስቱም የቫይረሱ ታማሚዎች የተገኙት በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ መሆኑን ገልጸዋል።

    የመጀመሪያዋ ታማሚ የ61 ዓመት ሴት ሲሆኑ በቅርቡ ቤተሰብ ጥየቃ ወደ ህንድ አምርተው የነበሩ ናቸው። ከእርሳቸው በተጨማሪም ከእርሳቸው ጋር ንክኪ የነበራቸው ሠራተኛቸውና ሌላ አንድ ዘመዳቸው በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ማላዊ በቫይረሱ መጠቃቷን ተከትሎ እስካሁን በኮሮናቫይረስ ያልተጎበኙት የአፍሪካ አገራት ቁጥር ወደ አራት ዝቅ ብሏል። እነዚህም አገራት ሌሶቶ፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፕ፤ ኮሞሮስ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው።

  8. በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆነ

    የህክምና ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

    ወረርሽኙን ለመግታት ለሚደረገው ትንቅንቅም ጨለም ያለ ዜና ነው ተብሏል።

    እስካሁን ባለው መረጃ 53ሺ ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ 210 ሺ ሰዎች ደግሞ እንዳገገሙ የዩኒቨርስቲው መረጃ ጠቁሟል።

    በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ በሆነችው አሜሪካ በትናንትናው እለት መጋቢት 24፣ 2012 ዓ.ም አንድ ሺ 169 ሰዎች ሞተዋል።

    ለሰው ልጅ ጠንቅ የሆነው ኮቪድ- 19 የተከሰተው ከሶስት ወራት በፊት በቻይና፣ ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ ነው። ተጨማሪ እዚህ ያንብቡ፡ በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆነ

  9. በኮሮናቫይረስ የተያዘው ሰው ቁጥር ከ5 እስከ 10 ሚሊዮን ይሆናል፡ የአውስትራሊያ ዋና ሐኪም

    አውስትራሊያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማግስት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኮሮናቫይረስ ታማሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ መኖሩ በምርመራ ተረጋግጧል።

    የአውስትራሊያው ዋና የህክምና ኦፊሰር እንደሚሉት ግን በቫይረሱ የተያዙት የዓለማችን ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

    “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ተጠቂ መኖሩን አረጋግጠናል። ነገር ግን ትክክለኛው የታማሚዎች ቁጥር በአምስት ወይም አስር እጥፍ ከፍ ያለ ይሆናል” ብለዋል ዶ/ር ብሬንዳን መርፊ።

    ይሁንና ዶክተሩ በአውስትራሊያ በምርመራ ተረጋግጧል የተባለውን የተጠቂዎች ትክክል መሆኑን ይናገራሉ። “አውስትራሊያ ከሌሎች የዓለም አገራት በተሻለ ሁኔታ ሰፊ ቁጥር ያለው ተጠርጣሪ እየመረመረች ነው” በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

    ሌሎች አገራት ግን በሚገባ የመመርመር ብቃታቸው ያነሰ ነው፤ የተወሰኑት ደግሞ ከነጭራሹ “ሁሉንም ተጠርጣሪዎቻቸውን አይመረምሩም” ብለዋል።

    አውስትራሊያ የተረጋገጠ 5 ሺህ 2 መቶ የኮሮናቫይረስ ታማሚ አላት።

  10. በቻይና በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ

    ቻይና

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ቻይና በአገሯ ያለውን የኮሮናቫይረስ ሁኔታ የሚያመለክት አዲስ መረጃ ይፋ አድርጋለች።

    በዚህም መሰረት ከውጪ የሚመጡ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን እያገኘች መሆኑን አመልክታል።

    ትላንት ሐሙስ ብቻ በግዛቷ ውስጥ ከውጪ የመጡ 29 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፤ ረቡዕ እለት ደግሞ በተመሳሳይ 35 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ በሽታው እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    ተጨማሪ ሁለት ህሙማን ደግሞ በአገር ውስጥ ተገኝተዋል።

    ሐሙስ ዕለት 4 ሰዎች በበሽታው መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ ሁሉም ሞቶች ያጋጠሙት የወረርሽኙ መነሻ እንደሆነች ሲነገርላት በነበረችው ዉሃን ውስጥ ነው።

    ቻይና ውስጥ እስካሁን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች አሃዝ 81,620ሲሆን የሞቱ ሰዎች ደግሞ 3,322ነው።

    ከበሽታው የዳኑት ቁጥር ደግሞ 76,500 መሆኑ ተገልጿል።

  11. አሜሪካ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለውን ሞት አስመዘገበች

    አሜሪካ በቀን ከፍተኛ የተባለውን የሞት መጠን አስመዘገበች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በቀን ከፍተኛ የተባለውን የሞት መጠን አስመዘገበች

    አሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱት ዜጎቿ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክትው በትናንትናው ዕለት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 169 አሜሪካዊያን በኮሮናቫይረስ ሞተዋል።

    ይህም ወረርሽኙ በቻይና ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በአገር ደረጃ በአንድ ቀን ብቻ የተመዘገበ ከፍተኛው የሞት ቁጥር ሆኗል።

    በአሜሪካ ከ244 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 6 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    1 ሺህ 5 መቶ የሞት ቁጥር በማስመዝገብ ኒው ዮርክ በሽታው ክፉኛ ጉዳት ያደረሰባት ግዛት ነች።

  12. በዓለም ዙሪያ ከ210 ሺህ በላይ ሰዎች ከኮቪድ-19 ድነዋል

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, GALLO IMAGES

    የምስሉ መግለጫ, የኮሮናቫይረስ ምርመራ

    በዓለም ላይ በስፋት ከተቀሰቀሰ ወደ አራት ወራት እየተጠጋ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተይዘው ከነበሩ ሰዎች መካከል ከ210 ሺህ ሰዎች በላይ መዳናቸውን ስለበሽታው የተሰባሰበ መረጃ አመለከተ።

    የኮቪድ-19 አጠቃላይ መረጃን በማሰባሰብ የሚያሰራጨው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የመረጃ ቋት እንደሚያመለክተው ከ211 ሺህ 400 ሰዎች በላይ በበሽታው ከተያዙ በኋላ ድነዋል።

    በርካታ የዳኑ ሰዎች ካሉባቸው አገራት መካከል መጀመሪያ ቫይረሱ ክፉኛ ያጠቃት ቻይና ቀዳሚ ስትሆን በመከተል ስፔን፣ ጣሊያን፣ ኢራንና ፈረንሳይ ይገኙበታል።

    በኢትዮጵያም እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው ተረጋግጦ ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል ባገኙት የህክምና ድጋፍ ሦስት ሰዎች መዳናቸውን የጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

    ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭት በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ሲሆን አሃዙ አሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል። የሞቱ ሰዎች አሃዝም ከ50 ሺህ በላይ እንደሆነ የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያመለክታል።

  13. የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    ዕለተ አርብ መጋቢት 25/2012 ዓ.ም

    ዛሬም እንደ ተለመደው ቢቢሲ አማርኛ የተለያዩ ዜናና መረጃዎችን ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በድረገጽ፣ በፌስቡክና በሬዲዮ ያቀርብላችኋል።

    ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ እንድትከታተሉን እንጋብዛለን፤ እናንተም ቢቢሲ አማርኛ ሽፋን ቢሰጠው ብላችሁ የምታስቧቸው ነገሮች ካሉ ጠቁሙን።

    መልካም ዕለት እንዲሆንላችሁ እየተመኘን፤ ከቻላችሁ ቤታችሁ ሆናችሁ ቀኑን አሳልፉ።

    የግድ ከቤታችሁ መውጣት ካለባችሁ ደግሞ እራሳችሁን ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች አርቁ።

    ስለኮቪድ-19 ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ የሚወጡ አሁናዊ መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን እዚህ ገጽ ላይ እናቀርባለን፤ ተከታተሉ።

    መልካም ቀን!

    ቢቢሲ አማርኛ