በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡ ተገለፀ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተዛምቶ የሁሉም ዋነኛ የህልውና ስጋት ሆኗል። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት ቀላል የመከላከያ መንገዶችን በመከተል በሽታውን መከላከል ይቻላል። እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና በተቻለ መጠን በርካታ ሰው ከሚሰበሰብበት ቦታ እራስን ማራቅ በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ እርምጃ ናቸው። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የተለያዩ ዜናና መረጃን ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በቀጥታ ዘገባ እዚህ ገጽ ላይ ያቀርባል። አብራችሁን በጤና ቆዩ!

የቀጥታ ሽፋን

  1. ለሰላምታ እጃቸውን ከዘረጉ 10 ዓመታት ያስቆጠሩት መምህር

    መምህር ብርሃኔ አቻሜ
    የምስሉ መግለጫ, መምህር ብርሃኔ አቻሜ

    መምህር ብርሃኔ አቻሜ ለሰላምታ እጃቸውን ከዘረጉ 10 ዓመታትን አስቆጥረዋል።

    መምህር ብርሃኔ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፉት 10 ዓመታት "በእጀ ተጨባብጨ አላውቅም" ይላሉ።

    በዘመኑ ቋንቋ፤ “እጅ ይነሳሉ እንጅ፤ እጅ አይሰጡም።” በዚህም ልማዳቸውም ወዳጅ ዘመዶቻቸው አኩርፈዋቸው ያውቃሉ።

    በእርግጥ መምህሩ ይህን ልማድ የጀመሩት ሰው በመጥላት አሊያም በመናቅ አይደለም። ለጋራ ጤንነት ሲሉ እንጂ።

    መምህር ብርሃኔ የዚህን ልማዳቸውን መነሻ ሲያስረዱ፤ ከአስር ዓመታት በፊት በየዓመቱ የዓለም የቆሻሻ ነገር ውድድር እንደነበር ያስታውሳሉ።

    ታዲያ በዚያን ወቅት በነበረው ውድድር ላይ በቆሻሻነቱ አንደኛ ሆኖ የተገኘው የኮምፒዩተር ኪቦርድ ነበር ይላሉ። እንደ እርሳቸው መረጃ ከሆነ፤ በኮምፒዩተር ኪቦርድ ላይ በአንድ ስኩየር ኢንች 44 ሺህ ጀርሞች ይገኛሉ።

    በዚህም ምክንያት “የእኔን ቆሻሻ ለሰው አላሳልፍም፤ የሌላም አልቀበልም” ብዬ በእጅ ሰላምታ መለዋወጡን እርግፍ አድርጌ ተውኩ ሲሉ ያስረዳሉ።

    በዚህ ልማዳቸውም በርካታ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ስላኮረፏቸው፤ “ለሰላምታ እጀን አለመዘርጋቴ እናንተ ቆሻሻ ናችሁ ማለት ብቻ ሳይሆን፤ እኔም ቆሻሻ ነኝ ማለቴ ነው” ሲሉ አበክረው አስረድተዋል።

    ይሁን እንጂ በርካቶች በውል እየተረዷቸው የመጡት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አለምን እያስጨነቀ ከመጣ ወዲህ መሆኑን መምህሩ ይናገራሉ።

    አሁን የኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ መንገድ አንዱ እጅ በመሆኑ የእጃችንን ንጽህና መጠበቅ አለብን ሲሉም ይመክራሉ።

    በግል ንጽህና ላይ የግል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል የሚሉት መምህር ብርሃኔ፤ ስለ ጤናችን መንግስት ይህን አድርጉ፤ አታድርጉ ሳይለን ራሳችን ተገቢውን ማድረግ እንችላለን ይላሉ።

    መምህሩ "በእጅ በመጨባበጥ የሚደረግ ሰላምታ ይቅር፤ የቃል ሰላምታዎችን መለዋወጡ በቂ ነው፤ እኔም ስከተለው የኖርኩት ይህንኑ ነው" ሲሉም ይመክራሉ።

  2. ሰበር, ኒው ዮርክ ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር አስመዘገበች

    New York

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተመታችው የአሜሪካዋ ግዛት ኒው ዮርክ ባለፉት 24 ሰዓታት ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር መዝግባለች።

    የኒው ዮርክ ገዢ አንድሩው ኩሞ እንዳሉት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በግዛታቸው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2,900 በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    የግዛቷ አስተዳዳሪ ጨምረው እንደተናገሩት አሁንም በግዛቷ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መጠን እንደጨመረ ነው።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የኒው ዮርክ ግዛት አሃዞች የሚከተሉት ናቸው

    • በኒው ዮርክ ከሐሙስ ወዲህ ተጨማሪ 10,000 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
    • 102,000፡ አጠቃላይ በኒው ዮርክ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ነው
    • 14,000 በሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን 3,700 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ታመዋል
    • 8,800 አገግመው ከሆነስፒታል ወጥተዋል
  3. የኡጋንዳ ፖሊስ መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች የሚጥሱትን እያሰረ ነው

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    የኡጋንዳ ፖሊስ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚጥሱ ዜጎችን እያሰረ ይገኛል።

    ፕሬዝደንት ሙሴቪኒ የሰዓት እላፊ ከማወጃቸውም በተጨማሪ በከፊል የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ወስነዋል።

    የአገሪቱ ፖሊስም የፕሬዝደንቱን ትዕዛዝ የሚተላለፉትን በቁጥጥር ሥር ማዋል ጀምሯል።

    ታዲያ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ሰዎች የያዘበት ሁኔታ ክፉኛ እያስተቸው ይገኛል።

    የኡጋንዳ መገናኛ ብዙሃን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሰዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው እና ተጠጋግተው ተቀምጠው የሚያሳይ ምስል አሰራጭቷል።

    ፖሊስ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሰዎች መራራቅ ይኖርባቸዋል የሚለውን ምክረ-ሃሳብ አልጠበቀም፤ የሰዎች ህይወትንም አደጋ ላይ ጥሏል የሚሉ ትችቶች በስፋት ተሰምተዋል።

    በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ ምላሽ የሰጡት የፖሊስ ቃል አቀባይ ግን የእስረኞቹ ሙቀት ቀድሞ መለካቱን እና በተደጋጋሚ እጃቸውን እንዲታጠቡ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

  4. የቀድሞ የማራቶን ሻምፒዮን ሰዓት እላፊን ተላልፎ በፖሊስ ተያዘ

    ኬንያዊው አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊው አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ፤

    የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት የነበረው ኬንያዊው አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ፤ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ያስተላለፈውን ሰዓት እላፊ ተላልፎ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በዋስ ተለቀቀ።

    ኪፕሳንግ እአአ 2013 ላይ በበርሊን ማራቶን አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሎ ነበር።

    ትናንት በቁጥጥር ሥር የዋለው ኪፕሳንግ አንድ ምሽት በእስር ቤት ካሳለፈ በኋላ በ5ሺህ የኬንያ ሽልንግ በዋስ ተለቋል።

    አትሌቱ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ጋር ፑል እየተጫወተ እና እየጠጣ መሆኑን ፖሊስ ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

    "ይህ ሕግን መተላለፍ ነው። እኚህ ሰዎች በማህብረሰቡ ዘንድ የሚከበሩ እንደመሆናቸው አርዓያ መሆን ይገባቸዋል እንጂ ሕግ መጣስ አይኖርባቸውም" ብለዋል- የኬንያዋ ኢቴና ግዛት ፖሊስ መኮንን ጆን ሙዋዚ።

    ኬንያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከምሽቱ 1፡00 እስከ ንጋት 11፡00 ሰዓት ድረስ ስዓት እላፊ ጥላለች።

  5. በአሜሪካ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎች መበራከታቸው ተገለጸ

    US

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት የኮቪድ-19 ምርመራ እናደርጋለን እያሉ ሰዎችን ገንዘብ የሚያስከፍሉ አጭበርባሪዎች መበራከታቸው ተገለጸ።

    ግለሰቦቹ ለምርመራ የሚመጡት ሰዎችን 240 ዶላር እንደሚያስከፍሉ ተነገሯል።

    የአካባቢው ባለስልጣናት የግለሰቦቹን ተግባር "ማጭበርበር ነው" ሲሉ ኮንነዋል።

    ነዋሪዎች ከሚጭበረበሩት ገንዘብ በተጨማሪ የግል መረጃቸውን አሳልፈው እየሰጡ መሆኑን በማስታወስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተላልፏል።

    በተመሳሳይ አንድ የኮቪድ-19 ክትባት አቀርባለሁ በማለት ያስተወወቀ ድረ-ገጽ እንዲዘጋ ተደርጓል።

    በቨርጂኒያ ግዛትም የመንግሥት የጤና ባለሙያ በመምሰል ለማጭበርበር የሚሞክሩ በርካቶች መሆናቸው ተጠቁሟል።

  6. ቱኒዚያ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ሮቦት በዋና መዲናዋ አሰማራች

    Tunisia

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የቱኒዚያ ፖሊስ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ሮቦት በመዲናዋ ቱኒዝ አሰማራ።

    ሮቦቱ ልክ እንደ ፖሊስ ሰዎች እንቅስቀሴያቸውን መገደብ አለመገደባቸውን ይቆጣጠራል።

    ሮቦቱ ጭር ባሉት ጎዳናዎች ላይ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ከተመለከተ ወደ ግለሰቦቹ በመቅረብ ለምን ከቤት እንደወጡ ይጠይቃል።

    ሰዎቹም መታወቂያቸውን እና ሌሎች የፈቃድ ወረቀቶችን ወደ ሮቦቱ ካሜራ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

    በዚህም ፖሊሶች ካሉበት ሆነው መቆጣጠር ያስችላቸዋል ማለት ነው።

    ባለ አራት እግሩ ሮቦት መብራት በመጠቀም እንደ ራዳር መቆጣጠሪያ ይሰራል። አንዳንዶች ሮቦት መጠቀምን ያደነቁ ሲሆን፤ ሮቦቱ በዝግታ እንደሚንቀሳቀስ በመጥቀስ ውጤታማ ላይሆን ይችላል ሲሉ የተቹትም አሉ፡፡

    ሮቦቱ ሰዎችን በማስቆም ሲጠይቅ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተሰራጭቷል።

    በቪዲዮ አንድ ሰው “እንቅስቃሴ ተገድቧል ግን ሲጋራ መግዛት ፈልጌ ነው” ሲል ለሮቦቱ የመለሰ ሲሆን፤ “እሽ! ሲጋራህን ግዛና በፍጥነት ወደ ቤትህ ተመለስ!” በማለት ሮቦቱ ሲያስጠነቅቅ ያሳያል።

    ቱኒዚያ እስካሁን 14 ሰዎች የገደለባትን ወረርሽኝ ለመግታት እንቅስቃሴን ከገደበች ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች፡፡

    የህክምና አሊያም አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ነዋሪ ከቤት መውጣት አይችልም።

    በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አገራት 436 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ በሚመጣው ኮቪድ -19 በሽታ ተይዘው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

  7. ሰበር, በዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨመረ

    UK Health worker

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 684 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 605 ደርሷል።

    በአገሪቷ እስካሁን 173 ሺህ 784 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል 38 ሺህ 168 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  8. በቤት ውስጥ የመቀመጥ ውሳኔን ለማስፈጸም የተሰማሩ ወታደሮች በአስገድዶ መድፈር ተወነጀሉ

    Rwand

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሩዋንዳ መንግሥት ያስተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም የተሰማሩ 5 የአገሪቱ ወታደሮች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰሱ።

    አምስቱ የሩዋንዳ ወታደሮች የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ያቀረቡትን ጥቆማ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።

    ወታደሮቹ ይህን ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ከዋና ከተማዋ ኪጋሊ ወጣ ብሎ በሚገኝ አቅመ ደካማ ሩዋንዳዊያን በሚኖሩበት መንደር ውስጥ ነው።

    ከዚህ ክስ በተጨማሪ ወታደሮቹ ዘረፋ ፈጽመዋል የሚል ክስም ተመስርቶባቸዋል።

    ባሳለፍነው ሳምንት የእንቅስቃሴ ገደቡን በመጣስ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው መንገድ ላይ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በጥይት ተመተው መገደላቸው በሩዋንዳ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር። በሩዋንዳ እስካሁን 84 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  9. በዩናይትድ ኪንግደም በ9 ቀናት የተገነባው ሆስፒታል ተከፈተ

    ጦሩ የሆስፒታሉ ግንባታ ላይ የበኩሉን አበርክቷል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጦሩ የሆስፒታሉ ግንባታ ላይ የበኩሉን አበርክቷል

    በዩናይትድ ኪንግደም ለኮቪድ-19 ታካሚዎች የሚሆን በ9 ቀናት የተገነባ ሆስፒታል ተከፈተ።

    በዩኬ ትልቁ የሆነው ናይቲንጌል ሆስፒታል፤ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከፍተኛ ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

    ለዚህ ሆስፒታል ይሆን ዘንድም በምስራቅ ለንደን የሚገኘው ኤክሴል ኤግዚቢሽን ማዕከል ወደ ጊዜዊ ሆስፒታልነት የተቀየረ ሲሆን 4 ሺህ አልጋዎችን እንደሚይዝ ተነግሯል።

    በ87 ሺህ 328 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ሆስፒታሉ እያንዳንዳቸው 42 አልጋዎች የሚይዙ 80 ተኝቶ መታከሚያ ክፍሎች አሉት።

    በቫይረሱ የተያዙት የዌልሱ ልዑል ቻርልስ ሆስፒታሉን በቪዲዮ መርቀው ከፍተውታል።

    ልዑሉ፤ ሆስፒታሉን በዚህ አጭር ቀናት ውስጥ እውን ያደረጉ አካላትን ያመሰገኑ ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ሙያዊ ትግል እያደረጉ ላሉት የህክምና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

  10. ወረርሽኙን ለመቆጠጣር የምንወስዳቸው እርምጃዎች ለወንጀሎች እያጋለጡን ነው ተባለ

    Paris

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ሲባል መንግሥታት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ዜጎችን ለተወሰኑ አይነት ወንጀሎች ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው ተባለ።

    የአውሮፓ ፖሊስ ኤጀንሲ ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ መወሰኑን ተከትሎ ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የወሲብ ጥቃቶች ቁጥር እንዲጨምር እንዳደረገ አመላክቷል።

    ከዚህ በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩ ተጠቁሟል።

    ከዚህ በተጨማሪ የበይነ-መረብ ጥቃቶች አይነት እና ብዛትም መጨመሩ ተጠቁሟል።

  11. በኬንያ የ6 ዓመት ልጅ በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወቱ አለፈ

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    የኬንያ ጤና ሚንስቴር በኮቪድ-19 ምክንያት የ6 ዓመት ወንድ ልጅ ህይወት ማለፉን አስታወቀ።

    ታዳጊው ከዚህ ቀደም የጤና እክል እንደነበረበት ተነግሯል።

    ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት 24 ሰዓት በተደረጉ ምርመራዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 12 ሰዎች መገኘታቸው ተነግሯል።

    የጤና ሚንስትር እየሰጠ ባለው መግለጫ በኬንያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 122 መድረሱን አስታውቋል።

    ጨምሮም የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለሚያክሙ ባለሙያዎች የሚሆን መከላከያ ልብስ እና ጓንት እያመረትን ነው ብለዋል።

    ከዚህ ተጨማሪም በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4 እንዲሁም አገግምው ከጤና ተቋም የወጡ ሰዎች ቁጥርም በተመሳሳይ 4 መሆኑ ተጠቁሟል።

  12. በማሌዥያ የአገሬው ተወላጆች ኮሮናቫረስን ፍራቻ ወደ ጫካ እየሸሹ ነው

    ማሌዢየ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በማሌዥያ ከብዙ ዓመታት በፊት መኖር የጀመሩት የማህብረሰብ አባላት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመሸሽ በአገሪቷ ወዳሉ ጫካዎች እየተሰደዱ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ይህ የሆነው ኦራንግ አስሊ የተባለው የመጀመሪያው የማህበረሰቡ አባል ባለፈው ሳምንት ቫይረሱ እንደተገኘበት ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

    የአካባቢው ነዋሪና አክቲቪስት በዱል ቸማይ እንደሚለው፤ “ራሳችንን ለመነጠል እና ምግብ ለመፈለግ ወደ ጫካዎቹ እየተመለስን ነው። ከጫካ ውስጥ ምግብ እንዴት ማግኘት እንደምንችል እናውቃለን። እዚያ ልንተክላቸው የምንችላቸው እጽዋቶችም አሉ” ብሏል።

    እኚህ ጥንታቂ የማህብረሰብ አባላት ድህነት ለበሽታ ተጋላጭ አድርጓቸዋል።

    በማሌዥያ 3 ሺህ 333 በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 53 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ይህም በደቡብ ምስራቅ እስያ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡

  13. ሕይወት እንቅስቃሴ በተገደበባቸው አራቱ ከተሞች ምን ትመስላለች?

    ባህር ዳር ከተማ

    የፎቶው ባለመብት, Facebook

    ከመጋቢት 23 ጀምሮ በአዲስ ቅዳም፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና በባህር ዳር ከተሞች ለ14 ቀናት ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካሪም ሆነ የህዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ መወሰኑ ይታወሳል።

    እንቅስቃሴ በተገደበባቸው አራቱ ከተሞች ሕይወት ምን ትመስላለች?

    አሽከርካሪ እና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው አበባው ሃሙስ "የባህር ዳር ከተማ ፀጥ ረጭ ብላለች" ሲል ያለውን ሁኔታ አጋርቶናል።

    የከተሞቹ ነዋሪዎች ያጋሩንን እዚህ መመልከት ይችላሉ።

  14. ከወደ አውሮፓ ምን አዲስ ነገር ተሰማ?

    የአውሮፓ ሕብረት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፈረንሳይ፡ የፈረንሳይ መንግስት ዜጎች ለመጭው ፋሲካ በዓል የሚያድርጉትን ጉዞ ለማስቆም በባቡር ጣቢያዎች፣ በአየር ማረፊያዎች እና በሌሎች ዋና ዋና መንገዶች ላይ ፍተሻ በማካሄድ እርምጃ እየወሰደ ነው።

    ጀርመን፡ በጀርመን በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ በልጧል። እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በልጧል።

    ስፔን፡ ስፔን ዛሬ በቫይረሱ 950 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ይህም እስካሁን በአንድ ቀን ውስጥ ከተመዘገበው ሞት ከፍተኛ ነው ተብሏል። በስፔን በኮሮናቫይረስ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እያለፈ ሲሆን፤ ከጣሊያን ቀጥሎ ከፍተኛ ሞት ተመዝግቦባታል።

    የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን፡ የኮሚሽኑ ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተዘጋውን የህብረቱን ድንበር ከፋሲካ በኋላም ለማራዘም ውይይት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

    ግሪክ፡ በግሪክ የስደተኞች ካምፕና መንገደኞችን ጭኖ ከፒራውስ ወደብ የተነሳው የዕቃና ሰው ማጓጓዣ መርከብ የኮሮናቫይረስ መነሻ መሆኑ ታውቋል። በመርከቧ ተሳፍረው ከነበሩ 380 መንገደኞች 119 የሚሆኑት በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  15. ሰሜን ኮሪያ ኮሮና የለብኝም ትላለች፤ እንዴት እንመናት?

    ሰሜን ኮሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድም ሰው በኮሮና አልተያዘብኝም ትላለች ሰሜን ኮሪያ። ጥብቅ እርምጃ ስለምወስድና ድንበሮቼን ከርችሜ ነው ይህን ውጤት ያመጣሁት ስትል ታብራራለች።

    ይህንን ለመቀበል እቸገራለሁ ይላሉ በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ ጦር ኮማንደር።

    ሌላ ሰሜን ኮሪያዊ ኤክስፐርት በበኩላቸው የተያዘ ሰው አይኖርም ባይባልም በብዙ ቁጥር ላይሆን ይችላል ሲሉ ይገምታሉ።

    በዚህ ወቅት በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን አልፏል።

    ከ53ሺ በላይ ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። ሰሜን ኮሪያ ግን በዚህ ቁጥር ውስጥ የኔ ዜጋ አንድም የለበትም ትላለች።

    ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

    ተጨመሪ ለማንበብ፡

  16. ሰበር, ስፔን ከጣሊያን በመቀጠል ከፍተኛውን የሞት ቁጥር መዘገበች

    በስፔን በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እንደጨመረ ነው።

    የባለስልጣናት መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 932 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።

    ይህም የሟቾቹን ቁጥር 10 ሺህ 935 አድርሶታል።

    ስፔን ከጣሊያን በመቀጠል ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆናለች።

  17. የኮሮና ክትባት መጀመሪያ በአፍሪካ ሊሞከር ይገባል ያሉትን ፈረንሳያዊ ዶክተሮች ድሮግባና ኤቶ አወገዙ

    ዲዲየር ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለት የፈረንሳይ ዶክተሮች በቴሌቪዥን ላይ በነበረ ውይይት የኮሮናቫይረስ የሙከራ ክትባት መጀመሪያ በአፍሪካ ሊሞከር ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውግዘትን እያስተናገዱ ሲሆን፤ ታዋቂዎቹ አፍሪካውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ዲዲየር ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶም የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

    "አፍሪካ መሞከሪያ ላብራቶሪ አይደለችም፤ አፍሪካውያንም የላብራቶሪ አይጦች አይደለንም" በማለት ድሮግባ በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

    የቀድሞው የካሜሮን እግር ኳስ ተጫዋች ሳሙኤል ኤቶ በበኩሉ ዶክተሮቹን "ነፍሰ ገዳይ" ብሏቸዋል።

    የዶክተሮቹ አስተያየት ዘረኝነትን በሚቃወሙ ቡድኖች እንዲሁም በብዙዎች ውርጅብኝን አስተናግዷል።

    ከቀናት በፊት በፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡት ዶክተር ጂን ፖል ሚራና ዶክተር ካሚል ሎችት ውይይትንም ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው አጋርተውታል።

    ዶክተሮቹ እንዳሉት ኤድስ ጥናቱ የተደረገው በአብዛኛው አፍሪካ ውስጥ ከመሆኑ አንፃር የኮቪድ-19 ክትባትም ሙከራ በአህጉሪቱ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

    "ይህንን ሙከራ ማድረግ ያለብን አፍሪካ አይደለምን? የፊት ጭምብሎች በሌለበት፣ ህክምና በላደገበትና፣ መተንፈስ ቢያዳግት እንኳን ትንፋሽ መመለስ የሚያስችል መሳሪያ በሌለበት መሆን አይገባውም? ልክ እንደ ኤድስ በአፍሪካውያን የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎች ጥናት እንደተሞከረባቸው።

    "እነዚህን ሙከራዎች የምናደርገው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ በመሆናቸውና ራሳቸውን መከላከል እንደማይችሉ ስለምናውቅ ነው" በማለት ዶክተሩ በተናገሩበት ወቅት ከፈረንሳይ የጤና ኢንስቲትዩትና የህከምና ማዕከል ተወክለው የመጡት ዶክተር ካሚልም ልክ ነው ተመሳሳይ ጥናቶች አፍሪካ ውስጥ ሊደረጉ ይገባል ብለዋል።

    ጉዳዩ አወዛጋቢ መሆኑንም ተከትሎ የጤና ኢንስቲትዩቱ የአተረጓጓም ስህተት ነው ብሏል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  18. "ኮሮና ቢራ" በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርት አቁሚያለሁ አለ

    ኮሮና ቢራ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ኮሮና ቢራ

    የሜክሲኮ ትልቁ ቢራ አምራች ኩባንያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተወዳጁን “ኮሮና ቢራ” ማምረት ማቆሙን አስታወቀ።

    የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ከኮቪድ-19 በሽታ ጋር ስሙ በመግጠሙ የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ፤ የቀልድ ምንጭና ባለዝና መሆን የቻለው ኮሮና ቢራ ስሙ በማህበራዊ ሚዲያ ሲያነጋግር ቆይቷል።

    ታዲያ ብዙዎች እንደገመቱት ስሙ ከቫይረሱ ጋር በመግጠሙ የገበያ ድርቅ መትቶት አይደለም ምርት እያቆመ ያለው።

    አንዳንድ አሉባልተኞች ቢራው በስሙ ምክንያት በአሜሪካ የነበረው ገበያ አፈር ድሜ በልቷል ሲሉ ነበር፤ ኩባንያው ግን ምንም አይነት የገበያ እጦት አልገጠመኝም ሲል ሐሜቱን አስተባብሏል።

    እንዲያው አሁን ምርት የምናቆምበት ምክንያት ከስማችን ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል የኩባንያው ኃላፊ።

    የቢራው አምራች ግሩፖ ሞዴሮ ኩባንያው በኮሮና ምክንያት አገራት “እጅግ መሠረታዊ ንግድ ብቻ” በሥራ ላይ እንዲቆይ ሌላው ግን ሥራ እንዲያቆም በማዘዛቸው ምክንያት ኮሮና ቢራን ማምረት ለማቆም እንደተገደዱ ይፋ አድርጓል።

    ኮሮና ዝነኛ ቢራ ሲሆን ምርቱ 180 በሚደርሱ አገራት ውስጥ ይሰራጭነበር።

    ሲኤንኤን ቴሌቪዥን ሰራሁት ባለው ቅኝት 38 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ቢራው ቫይረሱን እንዳያሲዘን በሚል መጠጣት እንዳቆሙ ዘግቦ ነበር።

    ጉግል በበኩሉ ባለፈው ሳምንት ‹‹ኮሮና ቢራ›› የሚለውን ስም የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ሰማይ እንደነካ አስታውቆ ነበር።

    ለዚህ ዝነኛ ቢራ ‹‹ኮሮና›› የሚል ስም የወጣለት የፀሐይን የውጭኛው ከባቢ አየር ኮሮና ስለሚባል ይህንኑ ተንተርሶ ነው።ኮሮና ቢራ በአሜሪካ ገበያ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እውቅ ቢራ ነው።

  19. ሰበር, በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ያለባቸው ስድስት ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

    ሰበር ዜና

    በኢትዮጵያ ውስጥ ስድስት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡ ተገለጸ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው 74 ሰዎች መካከል 6ቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ያሉትን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ወደ 35 ከፍ አድጎታል።

    በሽታው እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት ስድስት ሰዎች መካከል አምስቱ ከአዲስ አበባ እንዲሁም አንዷ ደግሞ ከድሬዳዋ መሆናቸው ተገልጿል።

    በአዲስ አበባ ከተያዙት ውስጥ ሁለቱ የውጪ ጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው ተብሏል።

    የመጀመሪያው የ35 ዓመት ወንድ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ የመጣ ሲሆን ሁለተኛው የ30 ዓመት ወንድ በተመሳሳይ ከዱባይ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም የመጣ መሆኑ ተገልጿል።

    ሚኒስቴሩ እንዳለው ሁለቱም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ግዴታ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ነው።

    ቀሪዎቹ ሦስተኛው የ28 ዓመት ወንድ፣ አራተኛውም የ56 ዓመት ወንድ፣ አምስተኛው የ30 ዓመት ወንድ ሲሆኑ፤ ሁሉም ቀደም ያለ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው ተብሏል።

    በተጨማሪም ሰዎቹ ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እየተጣራ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    ከዚህ ባሻገርም ስድስተኛዋ ሰው የ33 ዓመት ሴት ስትሆን በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ከዚህ በፊት በኮሮናቫይረስ መያዙ ከተገለጸው ሰው ጋር ግንኙነት የነበራት መሆኑ ተገልጿል።

    በኢትዮጵያ ውስጥ በወረርሽኙ መያዛቸው ከተረጋገጠ 35 ሰዎች መካከል ሦስቱ ሙሉ ለሙሉ መዳናቸው የተገለጸ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በጽኑ የህክምና ክትትል ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    በአገር ውስጥ ያሉት ቀሪዎቹም አስፈላጊው የህክምናና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

  20. ህንድ ውስጥ የተወለዱት መንትዮች ኮሮናና ኮቪድ የሚል ስም ተሰጣቸው

    ጨቅላ ህጻን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኮሮናና ኮቪድ እንኳን ወደዚህች ዓለም በሰላም መጣችሁ!

    በህንዷ ራይፑር ከተማ የተወለዱት ሁለቱ መንትዮች ኮሮናና ኮቪድ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

    ጨቅላዎቹ የተወለዱት ህንድ አስገዳጅ የሆነውንና ለሦስት ሳምንታት ያህል የሚቆየውን የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔ ባሳለፈችበት ወቅት ነው።

    ወላጆቻቸው ይህንን ስያሜ የሰጧቸው የዓለምን ማህበረሰብ እያስጨነቀና እየፈተነ የሚገኘው ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማስታወስ ነው ብለዋል።

    እናትየው ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃል ልጆቹ በሚያስጨንቅ ምጥ ነው የተወለዱት።

    "ምንም እንኳን እኔም ሆነ ባለቤቴ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ እያለፍን ቢሆንም ይህንን ጊዜ ማስታወስ እንፈልጋለን" በማለት ተናግራለች።

    ልጆቹ የተወለዱትም ከሳምንት በፊት ነው።

    ቫይረሱ አደገኛ ቢሆንም ይህ ወረርሽኝ ለህይወት መሰረታዊ የሆኑ የጤና ሁኔታዎችን የሚታሰብበት ጊዜ እንደሰጠም እናትየው አስረድተው "እነዚህንም ስያሜዎች ስንሰጥ እነዚህም ጉዳዮች ከግምት ውስጥ እንዲገቡ ነው" ብለዋል።

    መንትዮቹ እንደተወለዱም የሆስፒታሉ ሠራተኞች ኮሮናና ኮቪድ እያሉ መጥራታቸውም ለቤተሰቦቻቸው ውሳኔውን ቀለል አድርጎላቸዋል።