ትራምፕ ከማክሰኞ በፊት ሆርሙዝ የማይከፈት ከሆነ ኢራን "ሲኦል" እንደምትሆን አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም ዛቱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ከማክሰኞ በፊት የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ አገሪቱን “ሲኦል” እንደሚያደርጉ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም አስጠነቀቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ወደ ቻይና በሚጓዝ የኩዌት ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ተፈጸመ

    የኩዌት ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ አል ሳልሚ የተባለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኩዌት ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ አል ሳልሚ የተባለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    ሌሊቱን የኩዌት ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ አል ሳልሚ የተባለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ “ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ” በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ የባሕር ዳርቻ ዱባይ ላይ በቆመበት ጥቃት እንደደረሰበት ቫንጋርድ የተሰኘው የባሕር ትራንስፖርት ደኅንነት ኩባንያ አስታውቋል።

    ኩባንያው ጥቃቱን ተከትሎ በመርከቧ ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱ እና እሳት ተቀስቅሶ እንደነበር ጠቅሶ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል።

    የመርከቧ 24 ሠራተኞችም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳላጋጠማቸው እንዲሁም ጥቃቱን ተከትሎ የፈሰሰ ነዳጅ አለመኖሩን ይፋ አድርጓል።

    የዱባይ ባለሥልጣናት ስለ ጥቃቱ መፈጸም አረጋግጠው ስለመርከቧ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የኩዌት ነዳጅ ኮርፖሬሽን ግን ጥቃቱን “የኢራናውያን ጨካኝ የአየር ጥቃት” ሲል ገልጾታል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ስለ ጥቃቱ ቢዘግቡም ማን እንደፈጸመው ግን አልገለጹም።

    አል ሳልሚ በአውሮፓውያኑ 2011 የተሠራች ሲሆን፣ በባለቤትነት የተያዘችው እና የምትንቀሳቀሰው በኩዌት የነዳጅ ዘይት ጫኝ ኩባንያ ስር ነው።

    ቢቢሲ አደጋውን በተመለከተ ከኩባንያው አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

    ታንከርታንከርስ የተባለ ሌላ የማሪታይም ደኅንነት ኩባንያ መርከቧ 1.2 ሚሊዮን በርሜል የሳዑዲን እንዲሁም 800,000 በርሜል የኩዌት ድፍድፍ ነዳጅ መጫኗን ገልጿል።

    የነዳጅ ጭነቱ የተጠናቀቀው ባለፈው ወር መሆኑን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።

    ስለ መርከቧ የጉዞ መስመር ይፋ የሆኑ መረጃዎች መዳረሻዋ ኪንጋዶ ቻይና መሆኑን ያሳያሉ።

    በመርከቧ ጎን የደረሰን ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረ ቀዳዳ

    የፎቶው ባለመብት, Nader Itayim

    የምስሉ መግለጫ, በመርከቧ የጎን ክፍል የደረሰን ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረ ቀዳዳን
  2. ኢራን ‘የሽብር’ ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ ሁለት ዜጎቿን በሞት ቀጣች

    በሞት የተቀጡት ሁለቱ ኢራናውያን

    የፎቶው ባለመብት, mojahedin.org

    የምስሉ መግለጫ, በሞት የተቀጡት ሁለቱ ኢራናውያን

    ኢራን ከተቃዋሚው የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ እና “በበርካታ የሽብር ድርጊቶች” ውስጥ ተሳትፈዋል ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች በሞት ቀጣች።

    የኢራን የፍትህ ተቋማት የዜና ምንጭ የሆነው ‘ሚዛን’ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያጸደቀው የሞት ቅጣት ተግባራዊ የሆነው ሰኞ ጠዋት ነው።

    ሁለቱ ሰዎች ላይ ለሞት ያበቃቸው ክስ ተብሎ የቀረበው “በወሳኝ ቦታዎች እና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች” ላይ በላውንቸር ጥቃት ለመፈጸም ሲሉ በመገኘታቸው እንደሆነ አመልክቷል።

    የኢራን መንግሥት እንዳለው ሁለቱ ሰዎች ፒፕልስ ሞጃሂዲን ኦርጋናይዜሽን ከተባለው ድርጅት ጋር ባላቸው ግንኙነት እና ተሳትፎ በዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ ጥቃቶችን ሊፈጽሙ እንደነበር አመልክቷል።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች በኋላ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙት የሞት ቅጣቶች ቁጥር መጨመራቸውን የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች ይናገራሉ።

  3. በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ማወቅ ያለብዎት ሦስት ነገሮች

    በቴህራን ሰኞ ዕለት የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ ከወደመው መኖሪያ ቤቱ እቃዎችን ሰብስቦ የሚወጣ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን ሰኞ ዕለት የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ ከወደመው መኖሪያ ቤቱ እቃዎችን ሰብስቦ የሚወጣ ሰው

    አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ የከፈቱት ጥቃት አምስተኛ ሳምንቱ ላይ ይገኛል። አሁንም በአሜሪካ እና ቴህራን መካከል እየተደረገ ነው የተባለው ንግግር ምንም ዓይነት ተጨባጭ ውጤት አላስገኘም።

    ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ኢራን ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ላይ ድብደባዎችን እየፈጸመች መሆኑ ሲገለጽ፣ እስራኤል ደግሞ በሊባኖስ የሄዝቦላህ ይዞታዎች ናቸው ባለቻቸው ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው።

    ጦርነቱ መቼ ያበቃል?

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው ከኢራን ጋር የጀመረችው ጦርነት “በእርግጠንነት ከግማሽ በላይ መሄዱን" ለአንድ የአሜሪካ ቴሌቪዥን የተናገሩ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ደግሞ ይህ ከዘመቻ እንጂ ከጊዜ አንጻር አለመሆኑን አብራርተዋል።

    ኔታንያሁ ጦርነቱ “በሺህዎች የሚቆጠሩ” የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላትን መግደሉን እንዲሁም አሜሪካ እና እስራኤል የጦሩን ኢንዱሰትሪ የኒውክሌር ተቋማትን ጨምሮ ድምጥማጡን አጥፍተው “ለመጨረስ መቃረባቸውን” ተናግረዋል።

    በቀጣናው የሚፈጸሙ ጥቃቶች

    የእስራኤል ጦር ከኢራን የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች መለየቱን ከገለጸ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በቴህራን ላይ አዲስ የጥቃት ማዕበል መክፈቱን ተናግሯል።

    የኢራን ድሮኖች ዱባይን ጨምሮ በባሕረ ሰላጤው አገራት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተዘግቧል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የኢራን የፓርላማ ኮሚቴ በወሽመጡ ላይ የሚያልፉ መርከቦችን ቀረጥ ለማስከፈል ያዘጋጀው ሕግን አጽድቋል። እንደ ፋርስ የዜና ወኪል ዘገባ በዕቅዱ መሠረት የአሜሪካ እና እስራኤል መርከቦች እንዲሁም በኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የተሳተፉ አገራት በወሽመጡ እንዳያልፉ ይከለከላሉ።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ትራምፕ ለረዳቶቻቸው የሆርሙዝ ወሽመጥ በሰፊው ለእንቅስቃሴ ዝግ ሆኖ ቢቆይም ጦርነቱን ለማቆም ያላቸውን ፍላጎት መናገራቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው የሆርሙዝ ወሽመጥ “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ዳግም መከፈቱ አይቀርም” ሲሉ ተነግረዋል።

    ዋይት ሐውስ በፕሬዚዳንቱ አስተያየት ላይ ምላሽ ሲጠየቅ ይህንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር ጠቅሷል።

  4. ኢራናውያን ባለሥልጣናት ስላሉበት ሁኔታ ምን እናውቃለን?

    የኢራናውያን ባለሥልጣናትን እንቅስቃሴ ለማወቅ እንደዚህ ጊዜ ከባድ ሆኖ አያውቅም።

    ነገር ግን ባለሥልጣናቱ በብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ያላቸውን ተሳትፎ ማየት ይቻላል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን ከተኩበት ከየካቲት 29 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአደባባይም ሆነ በቴሌቪዥን ታይተው አያውቁም።

    እስራኤል ሞጅታባ ከመመረጣቸው በፊትም ሆነ በኋላ ዒላማ መሆናቸውን ስትገልጽ ቆይታለች።

    ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን መጋቢት 17 2018 ዓ.ም. ቴህራን ውስጥ አንድ የገበያ ማዕከል ሲጎበኙ ታይተዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱን ታሳቢ በማድረግ ፍትሃዊ የሆነ ስርጭት እና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰፍን በአጽንዖት መናገራቸውን ዘግበዋል።

    ከዚያ በኋላ በትናንትናው ዕለት የመንግሥት ስብሰባ ሲመሩ የሚያሳይ ምስል በኢራን የመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ተጋርቷል።

    የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ መጋቢት 8 2018 ዓ.ም. ቀድሞ የተቀረጸ መግለጫቸው በቴሌቪዝን ሲተላለፍ ታይተዋል።

    ምንም እንኳን ለመደበኛው የኢራን ሕዝብ ኢንተርኔት ቢታገድም የእርሳቸው የኤክስ ገጽ ግን አሁንም በሥራ ላይ ነው።

    ጋሊባፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በፋርስ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ መልዕክቶችን የሚለጥፉ ሲሆን፣ በክስተቶች ላይ የሚሳለቁ የተቀናበሩ ምስሎችንም ያጋራሉ።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ትናንት ሲቀባበሉት የነበረው መረጃ ደግሞ የእስላማዊ አብዮት ዘብ የቁድስ ኃይል የድንበር ተሻጋሪ አዛዥ የሆኑት እስማኤል ጋኒ መልዕክቶችን መለጠፍ እንደጀመሩ የኤክስ ገጻቸው ታግዷል።

    አንደኛው ልጥፋቸው ኢራን በቀጣናው ካሏት ኃይሎች ጋር ያላትን ትብብር ያንቆለጳጵሳል። እነዚህ ኃይሎች [ሄዝቦላህ እና ሁቲ] በእስራኤል ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ስትራቴጂ አዛብተዋል ብለዋል።

    የኢራን የመንግሥት ሚዲያ የጋኒ ኤክስ ገጽ መታገዱን ተከትሎ የኤክስ መሪዎች የባለሥልጣኑ በሕይወት መኖር “ያስደነግጣቸዋል” ሲሉ ዘግበዋል።

  5. በደቡብ ሊባኖስ አራት የእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ

    እስራኤል በሊባኖስ ሃኑዪህ መንደር ባደረሰችው የአየር ድብደባ የደረሰ ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በሊባኖስ ሃኑዪህ መንደር ባደረሰችው የአየር ድብደባ የደረሰ ጉዳት

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳስታወቀው ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት አራት የእስራኤል ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ሁለት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በመግለጫው መሰረት የተገደሉት የእስራኤል ወታደሮች ናኦም ማድሞኒ፣ ቤን ኮሄን፣ ማክሲዝም ኤንቲስ የሚባሉ ናቸው።

    ሁለት ሌሎች ወታደሮች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። አንደኛው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ሁለተኛው መካከለኛ ጉዳት ማስተናገዱ ተገልጿል።

    የመከላከያ ኃይሉ በመግለጫው አራተኛው ወታደር በተመሳሳይ ቦታ የተገደለ ሲሆን እስካሁን ማንነቱ አለመለየቱን ገልጿል።

  6. ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶም ቢሆን ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኛ መሆናቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሰፊው ለእንቅስቃሴ ዝግ ሆኖም ቢሆን ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኛ መሆናቸውን ለረዳቶቻቸው መናገራቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ጆርናሉ የአስተዳደሩን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ፕሬዚዳንቱ እና ረዳቶቻቸው ወሽመጡን ለማስከፈት የሚደረግ ወታደራዊ ዘመቻ ጦርነቱን ከተያዘት የጊዜ ገደብ፣ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት፣ ሊገፋው ይችላል ብለው መገምገማቸውን ዘግቧል።

    ትራምፕ የኢራንን ባሕር ኃይል እና የሚሳዔል ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ ካወደሙ በኋላ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በማቆም ወሽመጡን እንድትከፍት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማድረግ እያሰቡ መሆኑ ተገልጿል።

    ቢቢሲ ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

  7. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ያረቀቀችው ሕግ ጸደቀ

    አነሰተኛ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢራን የሚገኝ የፓርላማ ኮሚቴ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ቀረጥ ለመጣል ያረቀቀውን ሕግ አጽድቋል ሲል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አጋር) የሆነው የፋርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የብሔራዊ ደህንነት ኮሚሽን አባል የሆነ ሰው ዕቅዱ መፅደቁን አረጋግጠዋል፤ ይህም የአሜሪካ እና የእስራኤል መርከቦች በባሕረ ሰላጤው ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግድ ነው።

    በእቅዱ መሠረት በኢራን ላይ በተጣሉ ማዕቀቦች የተሳተፉ ሌሎች አገሮችም እንዲሁ በወሽመጡ በኩል እንዳያልፉ ይከለከላሉ ሲል አክሏል።

    የኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው አዲሱ የክፍያ ስርዓት ኢራን ከኦማን ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደምታደርግ የመንግሥት ቴሌቪዥኖች ዘግበዋል

    ከዓለም የነዳጅ ዘይት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የሚተላለፈው አብዛኛውን ጊዜ በኢራን እና በኦማን መካከል በሚገኘው በዚህ ጠባብ መተላለፊያ በኩል ነው።

    ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ በኩል የሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች 95 በመቶ መቀነሳቸውን የባሕር ላይ ደህንነትን የሚከታተለው ኬፕለር አስታውቋል።

  8. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያካሄደች አለመሆኑን በድጋሚ ገለጸች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እየተካሄደ አይደለም ሲሉ በድጋሚ አስተባበሉ።

    ኢስማዔል ባቃአይ ጦርነቱ የተካሄደባቸውን ጊዜያት በመጥቀስ፣ "ኢራን በእነዚህ 31 ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር አላደረገችም" ሲሉ አስተባብለዋል።

    "የተከሰተው ከአሜሪካ በተሰጡ የምክረ ሃሳቦች ታጅቦ የድርድር ጥያቄ ማቅረብ ነው፤ ፓኪስታንን ጨምሮ በተወሰኑ አሸማጋዮች በኩል ደርሶናል" ሲል በድረ ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    "አቋማችን በጣም ግልፅ ነው። የአሜሪካ ወታደራዊ ጥቃት እና ወረራ በተጠናከረበት በዚህ ወቅት፣ ጥረታችን እና አቅማችን የኢራንን ማንነት ማስጠበቅ ለይ ያተኮረ ነው።

    “ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዲፕሎማሲ ላይ ከአንዴም ሁለቴ የደረሰውን ክህደት አንረሳም” ብለዋል።

  9. ኔታንያሁ ከኢራን ጋር እያካሄዱት ያለው ጦርነት መቼ እንደሚያበቃ መናገር እንደማይችሉ ገለፁ

    ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኒውስ ማክስ ለተባለ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ከኢራን ጋር እያደረጉ ያለው ጦርነት የሚያበቃበትን ጊዜ በሚመለከት “የጊዜ ሠሌዳ” ማስቀመጥ እንደማይችሉ ተናገሩ።

    ኔታንያሁ ጦርነቱ “በእርግጠኝነት ከግማሽ በላይ ተከናውኗል” ያሉት ኔታንያሁ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ “ከውስጥ መውደቁ" አይቀርም ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  10. ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ በእስራኤል ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ሆስፒታል ገብተዋል

    ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለተኛ ወሩን በጀመረው እስራኤል ከኢራን ጋር ከምታካሂደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች ለሕክምና ወደ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    እስካሁን ሆስፒታል ከገቡት መካከል 121 ሰዎች አሁንም ድረስ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። ከመካከላቸውም አንዱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን 16 ደግሞ ከባድ የሚባል ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ 232 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመላው አገሪቱ ወደ ሆስፒታሎች መሄዳቸውን የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር ጨምሮ አሳውቋል።

    እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በማበር በኢራን ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃቶችን እየፈጸመች ትገኛለች።

    በሚሳዔሎች እና በድሮኖች የሚፈጸሙት ጥቃቶች በተለያዩ የእስራኤል አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው።

  11. ትራምፕ የኢራንን ኻርግ ደሴት ለምን ይፈልጉታል?

    የኻርግ ደሴት ካርታ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በቅርብ ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የኻርግ ደሴትን ጨምሮ ሌሎችም ዒላማዎችን እንደሚመቱ አስጠንቅቀዋል።

    ለመሆኑ ኻርግ ደሴት ምንድን ነው?

    ኻርግ ደሴት ከኢራን ባሕር ዳርቻ 28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በኢራን የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ቁልፍ ቦታ የሚሰጠው ነው።

    ከኢራን ድፍድፍ ነዳጅ 90 በመቶው የሚተላለፍበት ሥፍራም ነው።

    ለኢራን ቁልፍ የሆነው በእዚህ ደሴት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የምጣኔ ሃብት መስመርን ክፉኛ ያናጋል።

    ይህም ጦርነቱን የመቀጠል አቅምን እንደሚያሳጣው የደኅንነት ተንታኝ ሚኬይ ኬይ ይናገራሉ።

    በዚህ ደሴት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የኢራንን የነዳጅ ሽያጭ የሚያቃውስ ከመሆኑም ባሻገር አሜሪካ የእግረኛ ጦር እርምጃ ለመውሰድ እንዲቀልላት ያስችላል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ለማስገደድም አሜሪካ ልትጠቀምበት እንደምትችል ተንታኞች ይናገራሉ።

    ሆኖም ግን የአሜሪካ ዘመቻ ቀላል አይሆንም። እግረኛ ጦር ወደ ደሴቱ እንዲደርስ በባሕር ወይም በአውሮፕላን ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅበታል።

    ኢራን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ለኻርግ ደሴት የምታደርገውን ጥበቃ አጠናክራለች። በርካታ ወታደሮች እና የአየር መከላከያዎች እንደተሰማሩ የሲኤንኤን ምንጮች ገልጸዋል።

    ኻርግ ደሴት ያለውን ቁልፍ ሚና ለመረዳት ይህንን ዘገባ ያንብቡ- አሜሪካ በኢራኗ ኻርግ ደሴት ላይ የፈጸመችው ጥቃት በጦርነቱ ሂደት ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

  12. ስፔን በኢራን ጦርነት በሚሳተፉ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ የአየር ክልሏን ዘጋች

    የስፔን የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ

    ስፔን በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ የአሜሪካ አውሮፕላኖች በግዛቷ እንዳያልፉ የአየር ክልሏን መዝጋቷን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮቤልስ አስታወቁ።

    ሚኒስትሯ ጨምረውም አሜሪካ በስፔን ግዛት ውስጥ የሚገኙ የጦር ሰፈሮቿን ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ እንዳታውል ማዘዛቸውን እና “ይህንንም ከመጀመሪያው ለአሜሪካ መንግሥት አስታውቀናል” ብለዋል።

    በስፔን ውሳኔ ላይ አሜሪካ እስካሁን አስተያየት ያልሰጠች ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስፔን በኢራን ጦርነት ላይ ተቃውሞዋን በማሰማቷ ሙሉ የንግድ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።

    በኢራን ላይ ከተከፈተውን ጦርነት ከመጀመሪያው አንስቶ በመቃወም ዋነኛው የሆኑት ስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ አሜሪካንን እና እስራኤልን “ግድየለሽ” እና “ሕገወጥ” በማለት ገልጸዋቸዋል።

    በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፔን አንዳሉሺያ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን ከአሜሪካ ጋር በጋራ የሚያስተዳድሯቸውን ሮታ እና ሞሮን የተባሉ የጦር ሰፈሮችን አሜሪካ እንዳትጠቀም ከልክለዋል።

    የአሁን የአየር ክልል እገዳ ይፋ ከመሆኑ ከቀናት በፊት ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሁሉም የአሜሪካ የበረራ ዕቅዶችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድቅ አድርገዋል።

    አሜሪካ በሌሎች የአገራት ከሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች የሚነሱ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በስፔን የአየር ክልል ላይ ማቋረጥ ወይም ለአስቸኳይ ጊዜ ለማረፍ ወሳኝ ነው።

    የስፔን ውሳኔ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ተጨማሪ ርቀትን እንዲጓዙ ሊገደዱ ይችላሉ።

  13. ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ያራዘሙባቸው ቀናት

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአፋጣኝ የማይከፈት ከሆነ የኢራንን የነዳጅ እና ኤሌክትሪክ ይዞታዎች “እንደሚያጋዩ” እንዲሁም “ሙሉ በሙሉ እንደሚያወድሙ” አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው መሰል ዛቻ ሲያሰሙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ሲያራዝሙ ቆይተዋል።

    ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት አስቀምጠዋቸው የነበሩ ቀነ ገደቦችን ያራዘሙባቸው ቀናት ዝርዝር የሚከተው ነው፦

    መጋቢት 12/2018 ዓ.ም.፡ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ እንድትከፍት ጊዜ የሰጡት ትራምፕ ይህ ካልሆነ ግን “የኢራንን የተለያዩ የኃይል ተቋማት መትተን እናወድማለን። የምንጀምረውም ከትልቁ ነው” ብለዋል።

    መጋቢት 12/2018 ዓ.ም፡ ሁለቱ አገራት “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ” ንግግር ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት ላይ “የሚፈጸም ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ ጥቃት” ለአምስት ቀናት ማራዘማቸውን ገልጸዋል።

    መጋቢት 17/2018 ዓ.ም፡ ትራምፕ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ በ10 ቀናት እንደሚያራዝሙ አስታውቀዋል። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የኢራን መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትለው መሆኑን ገልጸዋል። ቀነ ገደቡን ወደ መጋቢት 28 አሸጋግረውም ነበር።

    ዛሬ፡ ትራምፕ ከኢራን አዲስ አመራሮች ጋር “ቆፍጠን ያለ ውይይት” ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ውይይቱ “በኢራን እየፈጸምን ያለውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሊያስቆም ይችላል” ብለዋል። ሆኖም ግን “በአጭር ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ አሜሪካ ተወዳጅ ‘ቆይታዋን’ ታገባድዳለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  14. የእስራኤል ነዳጅ ማጣሪያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የእሳት አደጋ ተከሰተ

    በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደላይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደላይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    ከኢራን የተተኮሰ ሚሳዔል በእስራኤል የአየር መከላከያ ከከሸፈ በኋላ የተፈጠረው ስብርባሪ በነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ላይ ማረፉን ተከትሎ የእሳት አደጋ መነሳቱ ተገለጸ።

    ‘ባዛን ኦይል’ የተባለው የእስራኤል ነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ውስጥ ዛሬ የነዳጅ ታንከር እና የኢንዱስትሪ ሕንጻ ላይ በሚሳዔል ስብርባሪ ጉዳት ደርሷል።

    በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    የአገሪቱ የእሳት እና አደጋ መከላከያ ባወጣው መግለጫ መሠረት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ እያደረጉ ነው።

    በተቋሙ ውስጥ በተለያየ ቦታ ሆነው በእሳት አደጋው ምክንያት መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ለማትረፍም ርብርብ እየተደረገ ነው ተብሏል።

    ሚሳዔሉ ከየት እንደተተኮሰ ግልጽ አይደለም። ሆኖም ግን ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ኢራን እና ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል።

  15. ኢራን በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ሕግ ልታጸድቅ ነው

    የኢራኑ የፓርላማ አባል (መጅሊስ) አላዲን ቦሩጄርዲ

    የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራኑ የፓርላማ (መጅሊስ) አባል አላዲን ቦሩጄርዲ

    የኢራኑ የፓርላማ (መጅሊስ) አባል አላዲን ቦሩጄርዲ ወሳኙን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን በተመለከተ የተዘጋጀውን አዲስ ሕግ "በተቻለ ፍጥነት ይጸድቃል" አሉ።

    በታቀደው “አዲስ አሠራር” መሠረት “ያለ ኢራን ፈቃድ” ምንም ዓይነት ጭነት በሆርሙዝ በኩል እንዲያልፍ እንደማይፈቀድ ቦሩጄርዲ ተናግረዋል።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው ላይ አዲስ የጉዞ ክፍያ ለመጀመር እንደምትፈልግም ተናግረዋል።

    "ደኅንነትን መጠበቅ እና ለሚያልፉ መርከቦች አገልግሎት መስጠት ወጪዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በወሽመጡ በኩል የትራንስፖርት ክፍያ ለመሰብሰብ የሚያስችል ማዕቀፍ መዘርጋት አለበት" ብለዋል።

    ኢራን ከኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ከፈረመችው ስምምነት የምትወጣበት “ጊዜው ደርሷል” ሲሉም ተናግረዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር መሳሪያዎች ላይ የፈጸሙት ጥቃትን ተከትሎ በስምምነቱ ውስጥ መቆየት “ተገቢነቱ” እንዳልታያት አስረድተዋል።

  16. የኢራቅ አየር ኃይል በሚሳዔል ተመታ

    ጉዳት የደረሰበት የኢራቅ ጦር አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Iraqi Ministry of Defence

    የምስሉ መግለጫ, ጉዳት የደረሰበት የኢራቅ ጦር አውሮፕላን

    የኢራቅ መከላከያ ሚኒስቴር ሞሐመድ አላ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር የሚሳዔሎች ጥቃት እንደተፈጸመበት እና የአገሪቱ አየር ኃይል አውሮፕላን ጉዳት አንደደረሰበት ገለጸ።

    ጥቃቱ ዛሬ ማለዳ በባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን አጠገብ በሚገኘው የጦር ሰፈር ላይ መፈጸሙን የገለጸው ሚኒስቴሩ የተጎዳ ወይንም የሞተ ሰው የለም ብሏል።

    የኢራቅ መከላከያ ሚኒስቴር በድረገፁ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዞ “ወታደራዊ ተቋም እና የመከላከያ አቅም ላይ ያነጣጠረ የፈሪ እና የወንጀል ድርጊት” ሲል ኮንኖታል።

    ዛሬ ማለዳ የሶሪያ ጦር ከኢራቅ ጋር በሚወሰንበት ድንበር አቅራቢያ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  17. ስድስት የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ ጉዳት ደረሰባቸው

    የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የእስራኤል ጦር ስድስት ወታደሮቹ በተለያየ ጊዜ በሊባኖስ ውስጥ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታወቀ።

    በደቡባዊ ሊባኖስ በትናንትናው ዕለት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ጸረ ታንክ ከተተኮሰባቸው በኋላ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጦሩ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

    የእስራኤል መከለከያ አክሎም የተተኮሰ ድሮን በአቅራቢያቸው የወደቀ ሦስት የጦሩ አባላት በተጨማሪ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና አንዱ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን ገልጿል።

    በተጨማሪም አንድ ወታደር “በዘመቻ ላይ በተፈጠረ አደጋ” ጉዳት የደረሰበት መሆኑን አስታውቆ ሁሉም ወታደሮች ወደ ሕክምና ተቋም ተወስደዋል ብሏል።

    እስራኤል በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ ዳግም የጀመረችው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራአል ማስወንጨፉን ተከትሎ ነው።

    ሄዝቦላህ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ለቴህራን ያለውን አጋርነት ለመግለጽ በሚል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ጀምሯል።

    እስራኤል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሊባኖስ ባካሄደችው ዘመቻ ከ1000 በላይ ሊባኖሳውያን መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    እስራኤል በተጨማሪም ደቡባዊ ሊባኖስን የመቆጣጠር ፍላገት እንዳላት በመግለጽ በሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ የእግረኛ ጦሯን አሰማርታለች።

    እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ
  18. የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስተሮች የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ ሊወያዩ ነው

    የፈረንሳይ መንግሥት የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስቴሮች ዛሬ ተገናኝተው በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ እንደሚመክሩ አስታወቀ።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አገራት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ይህም በመላው ዓለም የኤነርጂ አቅርቦት በማስተጓጎሉ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ ጨምሯል።

    ከዚህም አገር ተያይዞ የምግብ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ይታያል የሚል ፍራቻ በየአገራቱ እየተስተዋለ ነው።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በበኩላቸው ዛሬ ከተለያዩ የንግድ ማኅበረሰቦች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተገናኝተው በጦርነቱ ተጽዕኖ ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    ኪር ስታርመር የሚያገኟቸው የቢዝነስ ማኅበረሰብ አባላት ከፍተኛ የኢነርጂ፣ የመርከብ ጭነት እና የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊዎችን መሆኑ ተጠቅሷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢራን ጦርነት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫናን ያነሳሉ ተብሏል።

    በለንደን የሚገኝ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  19. ትራምፕ በኢራን ለረዥም ጊዜ ሲፈልጓቸው የነበሩ ዒላማዎች መመታታቸውን እና መውደማቸውን ተናገሩ

    እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በኢራን የሚገኙ “በርካታ ዒላማዎች” መውደማቸውን ገለጹ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ “በኢራን ትልቅ ቀን ነው። ለረዥም ጊዜ ስንፈልጋቸው የነበሩ በርካታ ዒላማዎች በታላቁ፣ በዓለም ላይ ካለው ምርጡ እና አውዳሚው ጦራችን ተመትተዋል፤ ወድመዋል።

    ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጦሩ በኢራን የሚገኙ ከ9 ሺህ በላይ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጾ ነበር።

  20. ትራምፕ 'ከኢራን ዩራኒየም ለማውጣት' ዘመቻ እያሰቡ ነው - ዎል ስትሪት ጆርናል

    የአሜሪካ ጦር ጄቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን 1,000 ፓውንድ ዩራኒየም ለማውጣት የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ እያሰቡ ነው ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ስማቸው ያልተጠቀሱ የደህንነት ባለሥልጣናትን የሚጠቅሰው የዎል ስትሪት ዘገባ፣ ይህ ዘመቻ "የአሜሪካን ወታደሮች ለቀናት ወይም ከዚያ በላይ አገሪቱ ውስጥ ሊያስቆያቸው ይችላል።"

    ትራምፕ እስካሁን ውሳኔ ላይ ባይደርሱም ግን "ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት፣ ሃሳቡ በአጠቃላይ ክፍት ነው፣ ምክንያቱም ይህ ሃሳብ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳትሰራ ለመከላከል ያላቸውን ዋና ዓላማ ለማሳካት ይረዳል።"

    ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ዋይት ሐውስንና ፔንታጎንን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ወደ ክልሉ የተሰማሩ ወታደሮች "በኢስፋሃን የኑክሌር ጣቢያ ላይ በኢራን ከፍተኛ የበለፀገችውን ዩራኒየምን ለማነጣጠር በሚደረገው ተልዕኮ ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ" ነገር ግን እነዚህ ወታደሮች የዃርግ ደሴትን ለመያዝ ወይም የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ለመጠበቅ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

    ኒውዮርክ ታይምስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደዘገበው ትራምፕ "በኢስፋሃን ውስጥ በሚገኝ ተራራ ስር በብዛት ተከማችተው እንደሚገኙ የሚታመኑ ቦምብ ለማምረት የቀረቡ የኒውክሌር ቁሶችን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት" የሚያስችል ዘመቻ ለማካሄድ "በግልጽ እያሰቡ ነው"።

    ሁለቱም የዜና አውታሮች ዘመቻው ውስብስብ እና ከፍተኛ አደጋ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ።