ትራምፕ ከማክሰኞ በፊት ሆርሙዝ የማይከፈት ከሆነ ኢራን "ሲኦል" እንደምትሆን አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም ዛቱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ከማክሰኞ በፊት የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ አገሪቱን “ሲኦል” እንደሚያደርጉ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም አስጠነቀቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ የኢራን ድልድዮች እና የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ለመምታት ዛቱ

    በቴህራን ምዕራባዊ ክፍል፣ ካራጅ በግንባታ ላይ የነበረ ድልድይ በአየር ድብደባ ምክንያት ለሁለት ተከፍሏል

    የፎቶው ባለመብት, X/Araghchi

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን ምዕራባዊ ክፍል፣ ካራጅ በግንባታ ላይ የነበረ ድልድይ በአየር ድብደባ ምክንያት ለሁለት ተከፍሏል

    ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በኢራን የቀሩትን መሠረተ ልማቶች "ማውደም ገና አልጀመረም” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የአሜሪካን ጦር “ታላቅ እና እጅግ ኃይለኛ” ሲሉ አሞካሽተዋል።

    አክለውም በቀጣይ “ድልድዮችን ከዚያም የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን” ዒላማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት በቴህራን ምዕራባዊ ክፍል፣ ካራጅ በግንባታ ላይ የነበረ ድልድይ በአየር ድብደባ ምክንያት ለሁለት ከተከፈለ ወዲህ ነው።

    በጥቃቱ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ 100 ያህል ደግሞ መጎዳታቸው ተገልጿል።

    “የአዲሱ መንግሥት አመራር ምን መደረግ እንዳለበት ያውቃል። ይህም በፍጥነት መሆን አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በድልድዩ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ግንባታው ያልተጠናቀቀ ድልድይን ጨምሮ፣ የሲቪሎች መሠረተ ልማቶችን ማጥቃት፤ ኢራናውያን እጃቸውን እንዲሰጡ አያደርግም” ብለዋል።

  2. የመንግሥታቱ ድርጅት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ሊሰጥ ነው

    የጸጥታው ምክር ቤት (ከሌላ ስብሰባ ላይ ተወሰደ ፎቶ)

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የጸጥታው ምክር ቤት (ከሌላ ስብሰባ ላይ ተወሰደ ፎቶ)

    የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል።

    የምክር ቤቱ ተለዋጭ ፕሬዚዳንት የሆነችው ባህሬን ቢያንስ ለስድስት ወራት ያህል በሆርሙዝ ባህር ዳርቻ የመሸጋገሪያ መንገዶችን ለማስጠበቅ “አስፈላጊ እና ከሁኔታዎች ጋር የሚመጣጠን ሁሉንም የመከላከያ ዘዴዎች መጠቀም" የሚፈቅደውን የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች።

    የውሳኔ ሃሳቡ በመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 7 መሠረት የወታደራዊ ኃይል መጠቀም የሚጠይቅ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ሩሲያ እና ቻይና በድርድሩ ወቅት በመቃወማቸው እንዲወጣ ተደርጓል።

    ይኹን እንጂ የውሳኔ ሃሰቡ ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ቃላት አሁንም ቤይጂንግን እና ሞስኮን ስለሚያሳስቧቸው ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ሊጠቀሙ ይችላሉ ተብሏል።

    ከዚህ ቀደም በቀረቡ ረቂቆች ላይ ኢራንን የሚያወግዙ እና ወሽመጡን የሚጠቅሱ ቃላት በመኖራቸው ድምጸ ተዓቅቦ አድርገው ነበር።

  3. የኢራን ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ምክንያት መዘጋታቸው ተገለጸ

    ኢራን በዓለማችን 10ኛዋ ብረት አምራች አገር ናት
    የምስሉ መግለጫ, ኢራን በዓለማችን 10ኛዋ ብረት አምራች አገር ናት

    የኢራን ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎች በአሜሪካ እና በእስራኤል በተደጋጋሚ በተፈፀሙ የአየር ድብደባዎች ምክንያት መዘጋታቸውን ኩባንያዎቹ አስታወቁ።

    “የመጀመሪያ ግምታችን እነዚህን ክፍሎች እንደገና ማስጀመር ቢያንስ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንደሚወስድ ነው” ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢራን የሚገኘው የኩዜስታን የብረት ኩባንያ የኦፕሬሽን ምክትል ኃላፊ ሜህራን ፓክቢን ለኢራን መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    የሞባራኬህ ብረት ኩባንያ በመሃል አገሪቱ የሚገኘው ማምረቻዎቹ "ከፍተኛ የሆነ ጥቃት በመፈጸሙ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል" ብሏል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቃቱ ባለፈው ሳምንት አርብ መፈጸሙን ዘግበዋል።

    በፋብሪካዎቹ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በኢራን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ጨምረው ተናግረዋል።

    ከዓለም ብረታ ብረት ማህበር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኢራን በዓለም አቀፍ ደረጃ 10ኛዋ ትልቋ የብረት አምራች አገር ነች።

    ብረትን በአገር ውስጥ ለግንባታና ለማኑፋክቸሪንግ ከመጠቀም በተጨማሪ ወደተለያዩ የዓለም አገራት ትልካለች።

    የፋብሪካዎቹ ምርት ማቆም ለዓመታት በተጣለው ማዕቀብ በተጎዳው የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የአቅርቦት ሰንሰለቶች እና ንግዶች ላይ ከፍተኛ አንድምታ ሊኖረው ይችላል።

    ቢቢሲ የእስራኤልን የመከላከያ እና የአሜሪካን ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ስለ ጥቃቱ አስተያየት ጠይቋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ "እስራኤል በኢራን ውስጥ ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎችን፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና የሲቪል የኒውክሌር ጣቢያዎችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መትታለች። እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመተባበር እርምጃ መውሰዷን ገልጻለች" ብለዋል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል የደህንነት ምንጭ ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ ጥቃቶቹ በኢራን ኢኮኖሚ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ጉዳት ያስከትላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የብረት ፋብሪካዎቹ ከኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል።

    የአብዮታዊ ዘቡ ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ከአሜሪካ ጋር የተገናኙ የብረት እና የአሉሚኒየም ተቋማትን ዒላማ እንዳደረገ ተናግሯል።

    ሐሙስ ዕለት የእስራኤል ጦር ከኢራን በርካታ ሚሳዔሎች መወንጨፋቸውን ሲገልጽ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ደግሞ ጦሯ ከኢራን የተተኮሱ 19 ሚሳዔሎችን እና 26 ድሮኖችን "አክሽፏል" ብላለች።

  4. ትራምፕ ቴህራን አቅራቢያ የሚገኝ ድልድይ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠው “ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ይቀጥላል” ሲሉ አስጠነቀቁ

    የአሜሪካን ጥቃትን ተከትሎ ለሁለት የተቆረጠው ድልድይ

    የፎቶው ባለመብት, X/Mamlekate

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካን ጥቃትን ተከትሎ ለሁለት የተቆረጠው ድልድይ

    ሐሙስ ዕለት በመካከለኛው ምሥራቅ በግዝፈቱ ቀዳሚ ነው የተባለ በቴህራን አቅራቢያ የሚገኝ ድልድይ ላይ ጥቃት በመፈጸም በከፊል ማውደሟን ዶናልድ ትራምፕ አረጋገጡ።

    ድልድዩ ካራጅ ከተማን ከቴህራን ጋር የሚያገናኝ ነበር የተባለ ሲሆን በግንባታ ላይ የነበረ እንደሆነም ተገልጿል።

    በጥቃቱ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ 100 ያህል ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ግንባታው ያልተጠናቀቀ ድልድዮችን ጨምሮ፣ የሲቪሎች መሠረተ ልማቶችን ማጥቃት፤ ኢራናውያን እጃቸውን እንዲሰጡ አያደርግም” ብለዋል።

    አራግቺ በካራጅ ላይ የተፈጸመው ጥቃት “በግራ መጋባት ውስጥ ያለው ጠላት መሸነፍን እና የሞራል ውድቀትን ነው የሚያሳየው” ካሉ በኋላ “የማይጠገነው ውድመት” “የአሜሪካን አቋም የሚጎዳ ነው” ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ወደ "የድንጋይ ዘመን" እንደሚመልሱ በመግለጽ የሰጡትን አስተያየት በሚመለከትም አራግቺ በሌላ ልጥፍ ላይ በዚያን ጊዜ እና አሁን መካከል ያለው ልዩነት "በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ምንም ነዳጅ ዘይት ወይም ጋዝ የሚቀዳው አለመኖሩ ነው" ብለዋል።

  5. ሆርሙዝን ለማስከፈት “የሚያስችል ማንኛውም” እርምጃ እንደሚወሰድ የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

    የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬቬት ኩፐር

    የፎቶው ባለመብት, Pool

    የምስሉ መግለጫ, የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬቬት ኩፐር

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬቬት ኩፐር በዓለም ላይ ያሉ አገራት ዳግም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት “ማንኛውም የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የተባበረ እርምጃ” ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ሚኒስትሯ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከ40 በላይ አገራት ወሳኝ የሆነውን የባሕር መተላለፊያን ለማስከፈት በሚደረግ ጥረት ላይ ለመሳተፍ መተባበራቸውን ተናግረዋል።

    ኢራን ወሽመጡን ሙሉ በሙሉ ከዘጋች በኋላ በዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

    ዩናይትድ ኪንግደም በዛሬው ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት ያለመ ጉባዔ አስተናግዳለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩፐር በተደጋጋሚ ኢራን "የዓለም ምጣኔ ሀብትን ለማገት" የዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት መስመር የሆነውን ወሽመጥ "በግዴለሽነት" ዘግታለች በማለት ኮንነዋል።

    አክለውም ይህ የኢራን እርምጃ በዩኬ የነዳጅን፣ በአፍሪካ የአፈር ማዳበሪያ እና በእስያ የጋዝ ዋጋ ላይ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት እስከ 2000 የሚደርሱ መርከቦች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ መንቀሳቀስ ሳይችሉ መቆማቸውን ተናግሯል።

  6. ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ ዋነኛው የነዳጅ እጥረት መቼ ነበር የተከሰተው?

    ነዳጅ መቅጃ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለዓለም የነዳጅ እና ኃይል አቅርቦት መሠረት የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የአገራትን ምጣኔ ሃብት ወዳልተጠበቀ ቀውስ እየወሰደ ይገኛል።

    አንድ ወር ባለፈው የኢራን ጦርነት ምክንያት የተከሰተው ምስቅልቅል ዓለም በአውሮፓውያኑ በ1970 ከገጠማት ቀውስ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች መታየት ጀምረዋል።

    በአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ መላው ዓለምን ያናወጠው የነዳጅ ቀውስ በምን ምክንያት ነበር የተከሰተው? አሁን ከተከሰተው የነዳጅ እጥረት ጋርስ እንዴት ይነጻጸራል? ዝርዝሩን እዚህ ያንቡ አሁን ያጋጠመው ከቀደመው ምን ያህል የከፋ ነው?

  7. ሰባት ሚሊዮን ኢራናውያን አገራቸውን ለመከላከል መሰለፋቸውን አፈ ጉባኤው ተናገሩ

    ኢራን ሠራዊት አባል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሰባት ሚሊዮን ኢራናውያን አገራቸውን ለመከላከል በፈቃደኝነት ለወታደራዊ አገልግሎት ከሠራዊቱ ጎን መሰለፋቸውን የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ ተናገሩ።

    አፈ ጉባኤው የአገሪቱ መንግሥት ባካሄደው “ከፍተኛ ብሔራዊ ዘመቻ” በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢራናውያን “ታጥቀው አገራቸውን ለመከላከል ቁርጠኝነታቸውን አሳውቀዋል” ብለዋል።

    "ከዚህ በፊትም አድርገነዋል፤ አሁንም ልንደግመው ዝግጁ ነን. . . መላውን ኢራናውያንን ነው የምትገጥሙት” በማለት እስራኤል እና አሜሪካንን “ሞክሩት” ብለዋቸዋል።

    በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያቸላው አፈ ጉባኤው ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየተካሄደ ያለው የድርድር ጥረት ውጤት ካላስገኘ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት በሚፈጸሙት ጥቃቶች “ኢራን ከፍተኛ ውድመት” ይገጥማታል ብለው ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።

    አሁን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ጠመንጃ በማንሳት ጠላትን ሊፋላሙ እንደተዘጋጁ የገለጹት አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ በኢራን መንግሥት ውስጥ ለመነጋገር የሚሆኑ ሰው እና ቀጣዩ የአገሪቱ መሪ ይሆናሉ እያለች አሜሪካ በተደጋጋሚ የምትጠቅሳቸው ባለሥልጣን ናቸው።

    በተጨማሪም የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሃታሚ፤ የአገሪቱ ሠራዊት የሚሰነዘር የጠላት ጥቃትን ለመከላከል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንዲሆን አዝዘዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በዛሬው ዕለትም የቀጠለ ሲሆን፣ ከቴህራን በስተምዕራብ የምትገኘው ካራጅ ከተማ “ክፉኛ መመታቷን” እና በከተማዋ የሚገኝ ቁልፍ ድልድይ ዒላማ መደረጉን ምንጮች ለቢቢሲ የፋርስ ቋንቋ ተናግረዋል።

    በተመሳሳይ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራን ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ወደ ግዛቶቻቸው ማስወንጨፍ መቀጠሏን አስታውቀዋል።

  8. የተባበሩት መንግሥታተ ዋና ፀሐፊ አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ

    አንቶኒዮ ጉታሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የተበባሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ዘንድ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ።

    “በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር እና በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሰፊ ጦርነት አፋፍ ላይ ነን” ብለዋል።

    እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ጠቅሰው፣ ሰዎች ከነዳጅ እና ከምግብ ዋጋ መጨመር ጋር እየታገሉ መሆኑን ተናግረዋል።

    “የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ሲዘጋ በዓለም ላይ በጣም ድሃ እና ተጋላጭ የሆኑት መላወስ አይችሉም” ብለዋል።

    አለመግባባቶች "በሰላማዊ መንገድ" እንዲፈቱ ጥሪ ያቀረቡት ዋና ፀሐፊው፣ "የኒውክሌር ተቋማትን ጨምሮ" የሲቪል መሠረተ ልማቶች "መከበር እና መጠበቅ" እንዳለባቸው ተናግረዋል።

    አክለውም “መልዕክቴ ግልፅ ነው፤ ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለእስራኤል፣ ከፍተኛ የሰው ልጅ ስቃይ እያደረሰ ያለውን እና አስከፊ የኢኮኖሚ መዘዝ የሚያስከትለውን ጦርነት ለማቆም ጊዜው አሁን ነው።”

    "ኢራናውያን ደግሞ፣ ጎረቤቶቻችሁን ማጥቃት አቁሙ" ብለዋል ጉቴሬዝ።

  9. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

    ጄነራል ሞሐማድ አሊ ፋታሊዛድህ

    የፎቶው ባለመብት, Fars

    የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ሞሐማድ አሊ ፋታሊዛድህ

    በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ውስጥ የሚገኘው ፋትሂን የተባለው ክፍል አዛዥ የሆኑት ጄነራል ሞሐማድ አሊ ፋታሊዛድህ መገደላቸውን የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ጠቅሶ የቢቢሲ ፋርስ ቋንቋ አገልግሎት ዘገበ።

    ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሰው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንዳሳወቁት ጄነራሉ የተገደሉት በአሜሪካ እና በእስራኤል እየተፈጸመ ባለው ጥቃት ትናንት ረቡዕ ነው።

    ምንጮቹ ጨምረውም ጄነራል ሞሐማድ አሊ ፋታሊዛድህ ቀደም ሲል የአብዮታዊ ዘቡ እግረኛ ሠራዊት ክፍል አዛዥ እንዲሁም ባሲጅ የተባለው የሚሊሻ ጦር ፋትሂን የተባለው ክፍል አዛዥ ነበሩ።

    የቻይናው ዢንዋ የዜና ወኪል በበኩሉ ከኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ማዘዣ ጋር ግንኙነት ያለውን ዴፋ የተባለውን የኢራን ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።

    በተጨማሪም የኢራን መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ምንጮችም ከፍተኛው የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ መገደላቸውን እየተናገሩ ነው።

    ይህ በጄነራል ሞሐማድ አሊ ፋታሊዛድህ የሚመራው ፋትሂን የተባለው የአብዮታዊ ዘቡ ልዩ ክፍል በሶሪያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበረ አንዳንድ ምንጮች አመልክተዋል።

    በተጨማሪም በአብዮታዊ ዘቡ የእግረኛ ጦር ውስጥ የሚገኘው የክፍሉ አባላት የተለየ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ እና በመንግሥት ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችን በመቆጣጠርም ይሳተፋሉ።

    እስካሁን ስለ ከፍተኛ የጦር ጄነራሉ መገደል ከኢራንም ሆነ ከእስራኤል በኩል የተባለ ነገር የለም።

  10. ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ያለመ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው

    የተፈጥሮ ጋዝ የሚያጓጉዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዩናይትድ ኪንግደም 30 አገራት የሚሳተፉበት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት ያለመ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው።

    ጉባዔው የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበትን ይህንን የባሕር መስመር ለማስከፈት የሚኖሩ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮች ላይ ይነጋገራል ተብሎ እጠበቃል።

    ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ ጦርነት ከከፈቱባት ወዲህ በወሽመጡ ላይ የሚንቀሳቀሱ በርካታ መርከቦች ላይ ጥቃት ሰንዝራለች።

    በወሽመጡ ላይ የሚደረገው የመርከብ እንቅስቃሴ በዚህ የተነሳ ክፉኛ መስተጓጎሉ ተገልጿል።

    ረቡዕ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መተላለፊያውን ዳግም ለማስከፈት “ቢዘገዩም ወኔያቸውን ማጠናከር አለባቸው" ብለዋል።

    ትራምፕ አጋሮቻቸውን ሆርሙዝን ማስከፈት “አስቀድመው ሊያደርጉት ይገባ ነበር” ያሉ ሲሆን፣ አክለውም “ወደ ወሽመጡ ሄዱ፤ እና ውሰዱ፤ ተከላከሉ። ለራሳችሁ ተጠቀሙበት” ብለዋል።

    ዋሽንግተን በተደጋጋሚ አጋሮቿን ወሽመጡን ለመከላከል ወይም ጦርነቱ ለመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም በማለት ስትኮንን ቆይታለች።

    ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች አገራት ይህንን የዋሽንግተን ትችት ተከትሎ ወሽመጡን ለመጠበቅ በጦርነቱ ውስጥ ሳይሳተፉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲመለከቱ አስገድዷቸዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቬት ኩፐር ሐሙስ ዕለት በበይነ መረብ የሚካሄደውን ጉባዔ ይመራሉ ተብሏል።

    ጉባዔው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ኢራን በንግድ መርከቦች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታቆም የፈረሙ አገራትን ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል።

    የአገራቱ መግለጫ በተወሰኑ የባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች ድጋፍ አግኝቶ ነበር።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥቃት ከከፈቱባቸው አገራት ወይም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ውጪ ወሽመጡ ለሌሎች መርከቦች ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።

    ኒውዝሩም አፍሪካ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ቃል አቀባዩ እስማኤል ባግሃዒ፣ "ከባለሥልጣኖቻችን ጋር አስፈላጊው ትብብር ከተደረገ በኋላ" መርከቦች እንዲያልፉ ይደረጋሉ ብለዋል።

  11. ሩሲያ የኢራን ጦርነት እንዲቋጭ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሩሲያ የኢራን ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጾ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀጣናው መሪዎች ጋር መነጋገር መቀጠላቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ እንደተናገሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    “ፕሬዝዳንቱ እነዚህን ግንኙነቶች ቀጥለዋል፤ በሆነ መንገድ አገልግሎታችን ከተፈለገ በእርግጥም በተቻለ ፍጥነት ወታደራዊው ሁኔታ ወደ ሰላም እንዲሸጋገር ለማረጋገጥ አስተዋጾአችንን ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉ ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ አባልነት ለማስወጣት እያሰቡ እንደሆነ ስለመናገራቸው ለሩሲያው ቃል አቀባይ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፤ ሩሲያ ኔቶን የምትመለከተው እንደ ጠበኛ ጥምረት እንደሆነ በመግለጽ ምላሽ መስጠታቸው ሮይተርስ ዘግቧል።

  12. የኢራን ጦር ዋና አዛዥ የአገሪቱ ሠራዊት ለማንኛውም የጠላት ጥቃት እንዲዘጋጅ አዘዙ

    የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሃታሚ

    የፎቶው ባለመብት, tasnim

    የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሃታሚ፤ ሠራዊቱ አመራሮች “የጠላትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥንቃቄ” እንዲከታተሉ እና ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመከላከል እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲዘጋጁ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተዘገበ።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒው ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጠላት በመሬት ዘመቻ ለመክፈት የሚሞክር ከሆነ “አንድም ሰው መትረፍ የለበትም” ሲሉ ለሠራዊቱ አዛዦች ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ዋና አዛዡ በመላው ኢራን ከሚገኙ የጦር አየር መከላከያ እንዲሁም የምድር፣ አየር እና ባሕር ኃይሎች አመራሮች ጋር እንደተነጋገሩ ዘገባው ያመለክታል። የጠላትን ጠበኛ ድርጊቶች ለመጋፈጥ እንዲቻል የኢራን ጦር ጥቃት ለመፈጸም እና ለመከላከል ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

    “የጦርነት ደመና ከአገራችን ላይ መነሳት አለበት፤ የሁሉም ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባል። ምክንያቱም አንድ ቦታ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሆኖ ሕዝባችን ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ጦር አዛዡ ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ውስጥ ኢራን “በኃይለኛው እንደሚመቱ” ከተናገሩ በኋላ ነው። አሜሪካ እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ኢራን ደሴቶች ልታሰማራ ተችላለች የሚለው ስጋትም መናፈስ ከጀመረ ሰንብቷል።

    ትራምፕ ትናንት ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ጦር በኢራን ሊያሳካ የሚፈልጋቸው “ዋነኛ ስትራቴጂክ ግቦች ሊጠናቀቁ እንደተቃረቡ” አንስተዋል። አክለውም ግን በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ኢራን ላይ “እጅግ ኃይለኛ” የሆነ ጥቃት በመፈጸም የጀመሩትን ተግባር “በጣም በፍጥነት” እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል።

  13. ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ ማስወጣት ይችላሉ?

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንዲቋቋም እገዛ ካደረገችበት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንደሚያስወጡ ዝተዋል። ፕሬዝዳንቱ ግን ይህንን ዓይነቱን ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ሲነገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአውሮፓውያኑ 2017 ለመጀሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸውንም በፊት በተደጋጋሚ ኔቶን “የወረቀት ላይ ነብር” በማለት ያጣጥሉት ነበር። “ያረጀ” ሲሉ የሚጠሩት ይህ ጥምረት የአሜሪካን “ሀብት እያስወጣ” መሆኑንም ይናገሩ ነበር።

    በ2019 ደግሞ “በዚህ ዛቻቸው ላይ ወደ እርምጃ ለመግባት እየተዘጋጁ” መሆኑን የሚያሳይ “ግልጽ ምልክት” አሳይተው እንደነበር የቀድሞው የኔቶ ዋጋ ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ በሳተሙት መጽሐፍ ላይ ከትበዋል።

    የጥምረቱን ወታደራዊ ወጪ ሲተቹ የቆዩት ትራምፕ፤ አገራት ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርታቸው ውስጥ ሁለት በመቶውን መከላከያ ላይ ማዋል እንዳለባቸው በሚያዝዘው በአውሮፓውያኑ 2014 የወጣ የኔቶ “መመሪያ” ደስተኛ እንዳልሆኑም ገልጸዋል።

    ይህ መመሪያ ከወጣ በኋላ ሁሉም አባል አገራት በሚባል ደረጃ ወታደራዊ አቅማቸው ላይ የሚያውሉትን በጀት ጨምረዋል። ከፊሉ ይህንን እርምጃ የወሰዱት በትራምፕ ዛቻ ምክንያት ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሩሲያ በኩል እየጨመረ በመጣው ስጋት የተነሳ እንደሆነ የቢቢሲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና ዘገቢ ሊስ ዱሴት ትገልጻለች።

    ኔቶን ለቅቆ የመውጣት ጉዳይ ግን በፕሬዝዳንቱ ብቻ የሚተላለፍ ውሳኔ አይደለም። ፕሬዝዳንቱ የሴኔቱን ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሳያገኙ ወይም በኮንግረስ ሕግ ሳይጸድቅ በተናጠል ከኔቶ መውጣት አይችሉም።

    ይህንን አሠራር የዘረጋው ሕግ በ2024 ሲጸድቅ ድጋፍ ከሰጡት አንዱ አሁን የኢራንን ጦርነት የሚደግፉት የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ናቸው።

    ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት ፎክስ ኒውስ ላይ ቀርበው አሜሪካ የጥምረቱ አባል መሆኗ “አሁንም ለዓላማዋ እየጠቀመ” መሆን እና አለመሆኑን “መልሶ እንደሚመረምር” ተናግረዋል። ሩቢዮ አክለውም ኔቶን “አሜሪካ አውሮፓን ለመደገፍ እንዲሁ የተቀመጠችበት” ጥምረት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

    በአውሮፓውያኑ 2026 መጀመሪያ ላይ ትራምፕ አሜሪካ ኔቶ እርምጃ እንዲወስድ ባታደርግ ኖሮ ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ትቆጣጠር ነበር ብለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2011 አሜሪካ ላይ የ9/11 ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ኔቶ በአንቀጽ 5 መሠረት ለአሜሪካ መጠነ ሰፊ ድጋፍ አድርጓል። ይህ አንቀጽ በአንድ አባል አገር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት እንደሚቆጠር ይደነግጋል። በዚህም የኔቶ ወታደራዊ አቅም በአንቀጽ 5 መሠረት ጥቅም ላይ ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

  14. ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ “አድቃቂ” እና “ሠፊ” ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠነቀቀች

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ፤ አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩት “ትንሽ” ዒላማዎች ላይ እንደነበር በመግለጽ ኢራን “አድቃቂ፣ ሠፊ፣ እና አውዳሚ” ጥቃቶችን እንደምትፈጽም አስጠነቀቁ።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ባለው ታስኒም የዜና ወኪል ላይ የወጣው መግለጫ፤ አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ አቅም እና መሣሪያ በተመለከተ ያላቸው መረጃ “ያልተሟላ” እንደሆነ ጠቅሷል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም የኢራን ወታደራዊ ምርት “የሚካሄደው ጭራሹኑ በማታውቁት ቦታ ነው” ብለዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን የመሣሪያ ክምችት በአብዛኛው እንደደመሰሱ የገለጹበትን ንግግር ቃል አቀባዩ ውድቅ አድርገዋል

    አሜሪካ እና እስራኤል “ለቀሰቀሱት ጥቃት ዋጋ መክፈል አለባቸው” ብለዋል።

  15. የኢራን ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ ሕዝብ "የጠላትነት ስሜት የለንም" ሲሉ ይፋዊ ደብዳቤ ጻፉ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, WANA/Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ኢራን በአሜሪካ ሕዝብ ላይ “የጠላትነት ስሜት የላትም” አሉ።

    አገራቸው “ወረራ ቢፈጸምባትም ጦርነት ቀስቅሳ እንደማታውቅ” የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ “ተደጋጋሚ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ጫና” ሲደርስባት ቢቆይም ሁሌም “በመንግሥታት እና በሚመሩት ሕዝብ መካከል ግልጽ ልዩነት እንደምታሰምር” ተናግረዋል።

    ኢራንን ስጋት ፈጣሪ አድርጎ መሳል “ከታሪካዊ እውነታም ሆነ አሁን ከሚታይ ሀቅ ጋርም የሚጣጣም እንዳልሆነ” በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

    የኢራን ሕዝብ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ወይም በጎረቤት አገራት ሕዝቦች ላይ መጥፎ ፍላጎት እንደሌላቸውም ሲሉም ጠቅሰዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ግንኙነት ከጅምሩ እንደ አሁኑ የሻከረ እንዳልነበረ እና አሜሪካ በአውሮፓውያኑ “1935 መፈንቅለ መንግሥት” ሲደረግ ባሳየችው “ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት” እንደተቃረነ በማንሳት ከስሰዋል።

    አሜሪካ በኢራን ዙሪያ “ከፍተና ቁጥር ያለው ኃይሏን” ማስፈሯን አስታውሰው፤ “ከእነዚህ የጦር ሰፈሮች የተከፈተው የቅርቡ የአሜሪካ ጥቃት ይህ ዓይነቱ ወታደራዊ ሰፈራ ምን ያህል አስጊ እንደሆነ አሳይቷል” ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን ይህንን ደብዳቤያቸውን የጻፉት፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “አዲሱ የኢራን አገዛዝ ፕሬዝዳንት” የተኩስ አቁም ጠይቀዋል ካሉ በኋላ ነው።በኢራኑ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ውስጥ ግን ሊደረስ የሚችል የተኩስ አቁምን በተመለከተ የተጠቀሰ ነገር የለም።

  16. ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ከስምምነት የማይደረስ ከሆነ ኢራንን መሠረተ ልማቶች ክፉኛ እንደሚመቱ ከዛቱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ዋነኛው ድፍድፍ ነዳጅ ብሬንት ዋጋ በአምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቶ ወደ 106 ዶላር ደርሷል።

    ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ ለዓለም የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ወሳኝ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ከሚያስችል ይልቅ የጦርነቱን መቀጠል የሚያመለክት ነገር መናገራቸው ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በንግግራቸው ከመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት የሚፈልጉ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት እንዲሆን ለማድረግ መሪነቱን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

    ጦርነት የተከፈተባት ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት ሆርሙዝን መዝጋቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከመጨመሩም በላይ በዓለም ላይ የአቅርቦት እጥረት ተከስቷል።

    የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ትራምፕ በንግግራቸው ላይ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው የሚካሄደው ጦርነት በቶሎ የሚያበቃበትን ሁኔታ በተመለከተ ምንም ዓይነት ተስፋ ባለመስጠታቸው በነዳጅ ገበያው ላይ አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደሚከፈት እና መስመሩ ለአሜሪካ፣ ለእስራኤል እና ለአጋሮቻቸው ዝግ ሆኖ እንደሚቀጥል ከማሳወቋ በተጨማሪ የባሕር መተላለፊያውን የበለጠ ለመቆጣጠር የሚያስችላትን አዲስ ሕግ አውጥታለች።

  17. የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን “ምን ማሳካት እንደሚፈለግ ግልጽ አይደለም” አሉ

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግን” እንደሚደግፉ ቢገልጹም “ከዚያ በዘለለ ምን ማሳካት እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም” ሲሉ ጥያቄያቸውን አስተጋቡ።

    በኢራን “ምን ማሳካት እንደሚፈለግ ግልጽ አይደለም” ያሉት አልባኔዝ ጦርነቱ “በምን ሁኔታ እንደሚያከትምም በውል አይታወቅም” በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኔዝ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካውያን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

    ጦርነቱ መቼ እንደሚያከትም ትራምፕ የጊዜ ገደብ አስቀምጠው እንደሆነ የተጠየቁት አልባኔዝ፤ “ይሄ ከመጀመሩ በፊት አውስትራሊያ አስተያየቷን አልተጠየቀችም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

    አክለውም “የተባባሰ ነገር ማየት እንደማንፈልግ በግልጽ ተናግሬያለሁ። እንዴት ያልቃል የሚለው ላይም የጠራ መረጃ መኖር አለበት” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው በጦርነቱ “ቀጥተኛ ተሳታፊ” እንዳልሆነች ጠቅሰው “ነገር ግን አውስትራሊያውያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

  18. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚቀጥለው ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ውስጥ ኢራንን በኃይለኛው እንደሚመቱ ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ኢራን ላይ “እጅግ ኃይለኛ” የሆነ ጥቃት በመፈጸም የጀመሩትን ተግባር “በጣም በፍጥነት” እንደሚያጠናቅቁ አስታወቁ።

    ትራምፕ ትናንት ምሽት ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር የአሜሪካ ጦር በኢራን ጦርነት ሊያሳካ የፈለጋቸው ግቦች ላይ ለመድረስ መቃረቡን ገልጸዋል። ጦርነቱ መቼ ይጠናቀቃል ለሚለው ግን የጊዜ ሰሌዳ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ትራምፕ ባደረጉት ንግግር፤ በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ውሽመጥ በኩል የሚያልፍ ነዳጅ የሚረከቡ አገራት “ድፍረት” በማሳየት ወሳኙን መተላለፊያ እንዲቆጣጠሩ ጠይቀዋል።

    ትራምፕ 20 ደቂቃ ገደማ የፈጀው የዋይት ሀውስ ንግግራቸው፤ አሜሪካ በዚህ ጦርነት የያዘቻቸው “ዋነኛ ስትራቴጂክ ግቦች ሊጠናቀቁ እንደተቃረቡ” ተናግረዋል። የኢራን ባሕር ኃይል የድሮን እና ባለስቲክ ሚሳኤል ጦሮች “ተደምስሰዋል” ብለዋል።

    “በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ፤ በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት በሚሆን ጊዜ ውስጥ እጅግ በኃይለኛው እንመታቸዋለን” ሲሉ ዝተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን አመራር ጋር “እየተካሄደ ነው” ስላሉት ንግግር ዝርዝር መረጃዎች ከመስጠት ተቆጥበዋል። ድርድርሩ ፍሬ አልባ የሚሆን ከሆነ የኢራንን የኢነርጂ መሠረተ ልማት እንደሚመቱም ጠቁመዋል።

    “ስምምነት ላይ ካልተደረሰ እያንዳንዱን የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ በጣም በኃይለኛው እንመታለን፤ ምናልባትም ተመሳሳይ ጊዜ ላይ” ብለዋል።

    “ምንም እንኳ ከሁሉም አንጻር ቀላሉ ዒላማ ቢሆንም ነዳጃቸውን አልመታንም፤ ምክንያቱም የመትረፍ ወይም መልሶ የመገንባት ትንሽም እንኳ ዕድል አይሰጣቸውም” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ንግግራቸው አስቀድሞ የኢራን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቃለች በማለት ጽፈው ነበር። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቶሎ በሰጠው ምላሽ የፕሬዝዳንቱን ገለጻ “ሐሰት እና መሠረተ ቢስ” ብሎታል።

    ትናንቱ ንግግራቸው ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ የአሜሪካ አጋሮች የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል። “ቢዘገይም ድፍረት አሳዩ” እንዲሁም “እንዲሁ ወደ ወሽመጡ ሄዳችሁ ያዙት” ብለዋል።

    አገራቸውን ከኔቶ የማስወጣት ሐሳብ እንዳላቸው ሲገልጹ የነበሩት ትራምፕ፤ በዚህ ንግግራቸው ከወታደራዊው ጥምረት ጋር ወደፊት ስለሚኖረው ሁኔታ አልጠቀሱም።

  19. አሜሪካ ተኩስ ለማቆም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ቅድመ ሁኔታ አቀረበች

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ ወር ያለፈው ጦርነት የሚቆምበት መንገድን በተመለከተ ከሁሉም ወገን የተለያየ እና የሚቃረን አስተያየት እየተሰነዘረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ጥቃቶች እና የአጸፋ ጥቃቱ ቀጥሏል።

    ትራምፕ ጦርነቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚቆም መናገራቸውን ተከትሎ ኢራን ድርድር ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቧን ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ከኢራን በኩል ተቃራኒ ዜና ወጥቷል።

    የኢራን ቴሌቪዥን ዛሬ ከሰዓት በኋላ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን በኩል የድርድር ጥያቄ ቀርቧል መባሉን “ሐሰት እና መሠረተ ቢስ” ነው መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።

    አሜሪካ እና እስራኤል እያካሄዱት ባለው ጥቃት ኢራን ከባድ ውድመት ቢደርስባትም የአጸፋ ጥቃቷ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ከባድ ፍርሃትን አስፍኗል።

    በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የዓለም ነዳጅ የሚተለላፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋቷ በአብዛኛው ዓለም ክፍል ውስጥ የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ንረት ተከስቷል።

    በዚህም ምክንያት የጦርነቱ ቀስቃሾች አሜሪካ እና አስራኤል እየተወቀሱ ሲሆን፣ ኢራን የባሕር መተላለፊያውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የምትከፍት ከሆነ አሜሪካ ተኩስ ለማቆም እንደምትስማማ እየተዘገበ ነው።

    በተጨማሪም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ “በአሸማጋዮች” በኩል ከኢራን ጋር ንግግር እያደረጉ መሆናቸውን እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ላይ ኢራን የአሜሪካን ቅድመ ሁኔታን እንድትቀበል በምሥጢር መልዕክት እንደተላለፈላት ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ የሆነው አክሲዮስ እንደዘገበው ተኩስ ለማቆም በምላሹ የሆርሙዝ መተላለፊያን ለማስከፈት ንግግር እየተካሄደ ነው።

    ኢራን ግን ከተኩስ አቁም ይልቅ ዘላቂ ጦርነት የማቆም ዋስትና እዲሰጣት በመጠየቅ ሌሎችንም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።

  20. በቴህራን በሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት ደረሰ

    ጉዳት የደረሰበት ቤተክርስቲያን በከፊል

    የፎቶው ባለመብት, Russian Embassy in Iran

    የምስሉ መግለጫ, ጉዳት የደረሰበት ቤተክርስቲያን በከፊል

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ዛሬ በተፈጸመ ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ጉዳት እንደደረሰበት በአገሪቱ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታወቀ።

    ኤምባሲው “ቴህራን በሚገኘው የቅዱስ ኒኮላስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ሁለት ጊዜ ጥቃት ተፈጽሞ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ዋና ሕንጻ የእንግዶች ማረፊያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።

    የሩሲያ ኤምባሲ ከፊል ጣሪያው የፈረሰ ሕንጻ እና የተሰባበሩ መስኮቶችን የሚያሳዩ ምሥሎችንም ከመልዕክቱ ጋር አብሮ አጋርቷል።

    በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ለክርስቲያኖች ዋነኛ የሆነው የትንሳዔ በዓል እየተቃረበ ባለበት ጊዜ መሆኑ “የአሜሪካ እና የእስራኤል ወደታራዊ ጀብደኝነት በኢራን የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን የሚሰባሰቡበትን ስፍራ አሳጥቷቸዋል” ሲል ኤምባሲው ወቅሷል።

    የቅዱስ ኒኮላስ ካቴድራል በሩሲያዊው የሥነ ሕንጻ ባለሙያ የተነደፈ ሲሆን፣ በኢራን ብሔራዊ የቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንደ አገሪቱ ቅርስ ተመዝግቧል።

    የሩሲያ ኤምባሲ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት የሲቪል መሠረተ ልማቶችን፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ዒላማ እያደረገ መሆኑን በመገልጽ አውግዞታል።