ተጨማሪ ወታደሮቿ እና የጦር መርከቧ ወደ ባሕረ ሰላጤው የደረሱት አሜሪካ የእግረኛ ዘመቻ ለማካሄድ መዘጋጀቷ ተነገረ

ቅዳሜ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች እና አንድ የጦር መርከቧ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የደረሱት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን በኢራን ውስጥ ለሳምንታት የሚቆይ የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ከኢራን ያሉ ነገሮች “በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ነው” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በስልክ በሰጡት አጭር ቃለ ምልልስ ከኢራን ጋር “ሁኔታዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ከቴህራን ጋር መነጋገራቸውን እና አገሪቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ያስቀመጡትን የሰዓታት ገደብ በአምስት ቀናት ማራዘማቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ይህንን ቢሉም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገ ምንም ዓይነት ንግግር አለመኖሩን በመግለጽ አስተባብሏል።

    ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ “ለአምስት ቀን ያህል እንጠብቃለን፤ እና ያ እንዴት እንደሚሄድ እናያለን፤ ሁኔታዎች ጥሩ የሚሄዱ ከሆነ በስምምነት በእንቋጨዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ያ ካልሆነ ግን ድብደባችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ትራምፕ ኢራን “ድርድር ማድረግ በጣም ነው የሚፈልጉት፤ እኛም ከስምምነት መድረስ እንፈልጋለን” ብለዋል።

    አክለውም “ምናልባት በስልክ ዛሬም ንግግራችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ከቴህራን ጋር ያላቸው ንግግር መቀጠሉን አስረድተዋል።

    “በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አጋሮች” ያሏቸው አገራት “በውይይታችን ውስጥ በጣም የምናስባቸው ይሆናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ትራምፕ የኢራን ጦርነት እንዲያበቃ ከስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ የነዳጅ ዘይት ዋጋ “በፍጥነት ይቀንሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል።

    ትራምፕ ለጋዜጠኞች “ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል አለን” ያሉ ሲሆን፤ አክለውም “ያ ግን ለምንም ነገር ዋስትና አይሰጥም። ምንም ዋስትና እየሰጠሁ አይደለም” ብለዋል።

    ትራምፕ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለማቆም በ15 ነጥቦች ላይ መነጋገራቸውን አብራርተው፣ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎቿን እንድትተው “አንደኛው፣ ሁለተኛው እና ሦስተኛው ነጥቦች” መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ ትራምፕ “በጣም ወሳኝ የሆነ የስርዓት ለውጥ” ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

  2. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአሜሪካ ጋር ንግግር አለመደረጉን ገለጸ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል ንግግር ስለመደረጉ የተናገሩትን አስተባበለ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በጦርነቱ የኢራን ዓላማ ከመሳካቱ በፊት ማንኛውንም ዓይነት ድርድር ውድቅ የማድረግ አቋም ይከተላል” ማለቱን ዘግቧል።

    ኤስኤንኤን የተባለ ከፋርስ የዜና ወኪል ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በጉዳዩ ላይ መረጃ ያላቸው ምንጮችን በመጥቀስ “ድርድር መኖሩን አስተባብለዋል” ሲል ዘግቧል።

    የሚዲያ ገጹ ጨምሮም እኚሁ ምንጭ የሆርሙዝ ወሽመጥ “ጦርነት ለከፈቱብን ዝግ ነው” ማለታቸውን ገልጿል።

    የምንጩ ማንነት ወይንም በኢራን መንግሥት ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት አልተጠቀሰም።

    የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪልም በተመሳሳይ ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ተጠቅሞ ተመሳሳይ ዘገባ አቅርቧል።

    ፋርስ የዜና ወኪል “ከትራምፕ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምንም ዓይነት ግንኙነት አልተፈጠረም” ያለ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከአቋማቸው “አፈግፍገዋል” ብሏል።

    ታስኒም በበኩሉ "ምንም ድርድር" እየተካሄደ አለመሆኑን ዘግቧል።

  3. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር የትራምፕን ውሳኔ አደነቁ

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, EPA Shutterstock

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ትራምፕ ለኢራን አስቀምጠውት የነበረውን ቀነ ገደብ በአምስት ቀን ማራዘማቸውን አደነቀ።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ቃል አቀባይ “ውጤታማ የሆነ ንግግር ሁሉ ይደነቃል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት “ለጦርነቱ የሚገኝ ፈጣን መፍትሄ ዓለም አቀፋዊ ጥቅም እንዳለው ሁልጊዜ እንናገራለን” ብሏል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም “የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በተለይ ዳግም መከፈት አለበት” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ ካስቀመጡ በኋላ ተደረገ ያሉት ውጤታማ ንግግርን ተከትሎ ለውጦች ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው የአገራቸው ጦር ሠራዊት በቴህራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ማዘዛቸውን ገልጸዋል።

    ይህም ጥቃቱን ለአምስት ቀናት የሚያዘገየው እንደሆነ እና ቀጣይ ውሳኔያቸው እየተካሄደ ባለው ንግግር ላይ እንደሚመሠረት አስታውቀዋል።

  4. የኢራን መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ “አፈገፈጉ” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን ፋርስ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳችን ምንጭን ጠቅሶ ከትራምፕ ጋር “ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት የለም” ሲል ዘግቧል።

    ለዜና ወኪሉ መረጃ የሰጡት ምንጩ አክለውም “ዒላማዎቻችን በምዕራብ እስያ የሚገኙ የኃይል ማመንጫዎችን ሊያካትቱ እንደሚችሉ ሲሰሙ አፈግፍገዋል" ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ እንድትከፍት ካለበለዚያ ግን የኃይል ማመንጫዎቿን "እንደሚያወድሙ" ዝተው ነበር።

    ዛሬ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ከማብቃቱ በፊት ባለፉት ሁለት ቀናት ከኢራን ጋር "በጣም ጥሩ እና ውጤታማ" ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ጽፈዋል።

    ጨምረውም ጦራቸው በቴህራን የኃይል ማመንጫዎች ላይ "ለቀጣይ አምስት ቀናት" ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጸም ማዘዛቸውን አመልክተዋል።

    በሚቀጥሉት ቀናት የሚያደረጉ ንግግሮችን መሠረት በማድረግ ቀጣይ ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

  5. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ በአምስት ቀናት አራዘሙ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቴህራን ላይ በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም አስቀምጠውት የነበረውን የ48 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ወደ አምስት ቀን አራዘሙ።

    ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ግጭት ከኢራን ጋር “ሙሉ በሙሉ እና አጠቃላይ መፍትሔ” መድረስን በተመለከተ “ውጤታማ ውይይቶች” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "በኢራን የኃይል ማመንጫዎች እና የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን ሁሉ ለሌላ ጊዜ አስተላልፋለሁ" ብለዋል።

    ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓትት ውስጥ ካልከፈተች የኃይል ማመንጫዎቿን ለማጥቃት ዝተው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ለመጪዎቹ አምስት ቀናት እርምጃውን ማዘግየታቸውን ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ከኢራን ጋር ባለፉት ሁለት ቀናት “በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው አለመረጋጋት ሙሉ እና አጠቃላይ ግጭት መፍትሔ ላይ በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ንግግር አድርገናል” ብለዋል።

    ትራምፕ እንዳሉት ከኢራን ጋር በተደረገው እና በዚህ ሳምንትም በሚቀጥለው ገንቢ እንዲሁም ዝርዝር ውይይት መነሻ በማድረግ የአገራቸው ጦር ሠራዊት በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ማዘዛቸውን ገልጸዋል። ይህም ጥቃቱን ለአምስት ቀናት የሚያዘገየው እንደሆነ እና ቀጣይ ውሳኔያቸው እየተካሄደ ባለው ንግግር ላይ እንደሚመሠረት አስታውቀዋል።

  6. ቻይና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ያለው ግጭት እንዳሳሰባት ገለጸች

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊያን ዢያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በመካከለኛው ምሥራቅ የተሳተፉ ሁሉም አካላት ከቀውስ “አዙሪት” ወጥተው ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ቃል አቀባዩን ሊያን ዢያን ጠቀቅሶ እነደዘገበው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት እያደረጉ ያለው ጫና የተነሳ “ግጭቱ እየተካረረ የሚሄድ ከሆነ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ ይችላል። ይህም ቀጣናውን በአጠቃላይ ወደ ቀውስ ጎትቶ ሊያስገባ ይችላል” ብለዋል።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “ጦርነቱ አስቀድሞም መጀመር አልነበረበትም” ሲሉ ተናግረዋል።

  7. አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እንዳትመታ ሩሲያ አስጠነቀቀች

    ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በሩሲያ በተገነባው የኢራን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ላይ የምትፈጽመው ማንኛውም ጥቃት "ሊጠገን የማይችል" መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ሞስኮ አስጠነቀቀች።

    የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ የማይከፈት ከሆነ የኢራንን የኒውክሌር ማመንጫዎች “እንደሚያወድሙ” ስለመዛታቸው እንደተጠየቁ የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    ቃል አቀባዩ ምላሽ ሲሰጡ “አስከፊ በሚባል ደረጃ የተወጠረው” የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ ሊፈታ የሚችለው በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

    ፔስኮቭ አክለውም፤ በኒውክሌር ተቋማት ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት "እጅግ አደገኛ እንዲሁም ሊጠገን በማይችል መዘዝ የተሞላ" እንደሚሆን ገልጸዋል። ሩሲያ ይህንን በተመለከተ "ተገቢ የሆኑ ምልክቶችን" ለአሜሪካ ማስተላለፏንም ጠቅሰዋል።

  8. ዩኬ በኢራን ዒላማ እንደምትደረግ የሚጠቁም “ምንም ግምገማ” እንደሌለ የብሪታኒያው መሪ ተናገሩ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር አገራቸው የኢራን ጥቃት ዒላማ መሆኗን የሚያሳይ “ምንም ግምገማ” አለመኖሩን ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ዕለት ባሠራጨው መረጃ የኢራን “ሚሳዔሎች ለንደን፣ ፓሪስ እና በርሊን” ይደሳሉ ካለ በኋላ ነው። ኢራን የምታስወነጭፈው ሚሳዔል ለንደን ለመድረስ ከ4,300 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይኖርበታል።

    የእስራኤል ጦር በኤክስ ገጹ ይህንን ያለው፤ ኢራን ሁለት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ወደ የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የጋራ ወታደራዊ ሰፈር ዲዬጎ ጋርሺያ ማስወንጨፏን ተከትሎ ነው።

    ከኢራን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ 3,800 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው ጦር ሰፈር የተወነጨፉት ሚሳዔሎች ዒላማቸውን አልመቱም።

    ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ የኢራን ሚሳዔሎች የሚጓዙት ርቀት ዩናይትድ ኪንግደም ይደርስ እንደሆነ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር፤ መንግሥታቸው “የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሁሌም ግምገማ እንደሚያካሄድ” ገልጸዋል።

    “በዚህ ረገድ በኢራን ዒላማ እየተደረግን እንደሆነ የሚያሳይ ጭራሽ ምንም ግምገማ የለም” ብለዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ጦርነት ማርገብ እንደሚገባ የጠቀሱት ስታርመር፤ “ወደ ጦርነቱ ተስበው ሳይገቡ” የብሪታኒያ ጥቅሞች እና ዜጎችን መከላከል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

  9. ኢራን በምድር ወረራ ከተፈጸመባት “በመላው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ” የባሕር ፈንጂ እንደምታጠምድ አስጠነቀቀች

    የኢራን የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የኢራን መከላከያ ምክር ቤት፤ በአገሪቱ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻዎች እና ደሴቶች ላይ ወረራ የሚፈጸም ከሆነ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ መተላለፊያ ተቋርጦ የባሕር ፈንጂ እንደሚቀበርበት አስጠነቀቀ።

    የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ለማድረግ የኻርግ ደሴትን የመውረር ወይም የመዝጋት ዕቅድን እያጤነ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የምድር ጦር ወታደሮቻቸውን ሊያሰማሩ አቅደውበታል የተባለው የኻርግ ደሴት፤ ኢራን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ 90 በመቶው ይተላለፍበታል።

    ይህ ዓይነቱ ዘመቻ የሚከናወነው የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ ያለውን የኢራን ወታደራዊ አቅምን ይበልጥ ካዳከመ በኋላ እንደሚሆን ምንጮች መናገራቸውን የአክሲዮስ ዘገባ ያሳያል።

    ዛሬ ባወጣው መግለጫ ይህንን ዕቅድ የጠቀሰው የኢራን መከላከያ ምክር ቤት፤ በምድር ወረራ የሚፈጸም ከሆነ “በመላው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ” የባሕር ውስጥ ፈንጂ እንደሚቀበር ዝቷል።

    “የኢራንን ባሕር ዳርቻዎች ወይም ደሴቶችን ዒላማ የማድረግ ማንኛውም ሙከራ፤ በተፈጥሮ እንዲሁም በሚታወቀው ወታደራዊ ልምድ መሠረት ሁሉም መተላለፊያዎች…የፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና ሁሉም የባሕር ዳርቻዎች ፈንጂ እንዲቀበርባቸው ያደርጋል” ብሏል።

    “ከባሕር ዳርቻ የሚለቀቁ ተንሳፋፊ ፈንጂዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት የባሕር ፈንጂዎች” እንደሚቀበሩም በመግለጫው አስጠንቅቋል።

    “በዚህ አካሄድ መላው ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ለረጅም ጊዜ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይሆናል” ሲልም አክሏል። ይህ ለመሆኑም “ኃላፊነቱን የሚወስዱት አጥቂዎቹ” ናቸው ብሏል።

    “በ1980ዎቹ ከ100 በላይ የባሕር ፈንጂ አምካኞች ጥቂት የባሕር ላይ ፈንጂዎችን ለማስወገድ እንዳልቻሉ መዘንጋት አይገባም” ሲል የሚወስደው እርምጃ የሚኖረውን መዘዝ ጠቅሷል።

    የኢራን መከላከያ ምክር ቤት አክሎም “ጠብ ጫሪ ያልሆኑ አገራት” በሆርሙዝ ወሽመጥ ማለፍ ሚችሉበት “ብቸኛ መንገድ ከኢራን ጋር መቀናጀት” እንደሆነ ገልጿል።

    ኻርግ ደሴት

    የፎቶው ባለመብት, Gallo Images/Orbital Horizon/Copernicus Sentinel Data 2024

    የምስሉ መግለጫ, ኻርግ ደሴት ኢራን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ 90 በመቶው ይተላለፍበታል
  10. የእስራኤል ጦር ከኢራን እና ከሄዝቦላህ ጋር “የበርካታ ሳምንታት ውጊያ" ይቀረናል አለ

    እስራኤል በፈጸመችው አየር ጥቃት ደቡባዊ እና ማዕከላዊ ሊባኖስን የሚያገናኘውን ዋነኛ ድልድይ አውድማለች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በፈጸመችው አየር ጥቃት ደቡባዊ እና ማዕከላዊ ሊባኖስን የሚያገናኘውን ዋነኛ ድልድይ አውድማለች

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ከኢራን እና ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር በሚደረገው ጦርነት “የበርካታ ሳምንታት ውጊያ" ይቀረናል አለ።

    የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ኤፊ ዴፍሪን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ኢራን እና ሄዝቦላህ ላይ የተጨማሪ በርካታ ሳምንታት ውጊያ እንደምንጋፈጥ እንጠብቃለን” ብለዋል።

    የመከላከያ ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ኢያል ዛሚር እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የምታካሂደው ዘመቻ እንዲራዘም የሚያደርግ ዕቅድ እንዳጸደቁ ተገልጿል።

    ዋና አዛዡ “ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ገና መጀመሩ ነው። በኢራን ዘመቻ መጨረሻ ሄዝቦላህ ብቻውን እና ተነጥሎ ይቀራል” ብለዋል። “ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ የተራዘመ ነው፤ ለዚህም ተዘጋጅተናል” ሲሉም አክለዋል።

    አሁን በጸደቀው ዕቅድ መሠረት፤ የእስራል ጦር ወደ ሊባኖስ ገብቶ የከፈተውን “ውስን ዒላማ ያለው የምድር ዘመቻ እና ጥቃቶች ለማሳደግ” መዘጋጀቱን ዛሚር ጠቅሰዋል።

    “ስጋቶቹ ከድንበር ተገፍተው እስከሚርቁ ድረስ አናቆምም፤ ለሰሜን እስራኤል ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ደኅንነት ይረጋገጣል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ይህ ዕቅድ መጽደቁ የተሰማው እስራኤል ሊባኖስ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ትፈጽማለች የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የቴህራን አጋር የሆነው ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ሮኬቶችን ተኩሷል።

    እስራኤል ይህንን ተከትሎ ሊባኖስ ውስጥ በከፈተችው ጥቃት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ 118 ሕጻናት እና 40 የጤና ሠራተኞች ይኙበታል።

  11. በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን መምታት ጭምር ጠረጴዛው ላይ መሆኑ ገለጹ

    የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ዋልትዝ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልትዝ፤ ኢራንን በተመለከተ የኒውክሌር ኃይል ተቋማትን መደብደብን ጨምሮ የትኛውም አማራጭ “ከጠረጴዛው ውጪ” አይደለም አሉ።

    አምባሳደሩ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ከሆነው ሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ትራምፕ የኢራንን የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች “እንደሚያወድሙ” ስለማስጠንቀቃቸው ተጠይቀዋል። ዋልትዝ ምላሽ ሲሰጡ፤ “ለፕሬዝዳንቱ፤ ምንም ነገርን ከጠረጴዛው ውጪ አላደርገውም፤ በተለይም ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ [ቀርቤ]” ብለዋል።

    “የኢራን አብዮታዊ ዘብ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የአውሮፓ አገራት ጭምር ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጇል” ያሉት አምባሳደሩ፤ ወታደራዊ ኃይሉ “በአገሪቱ ከፍተኛ የኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ ኢኮኖሚ እና በርካታ የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ ቁጥጥር እንዳለው መረዳት አስፈላጊ ይመስለኛል” ብለዋል።

    "ስለዚህም ወታደራዊ አቅማቸውን እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ መሠረታቸውን እስከምናዳክም ድረስ፣ ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛው ላይ መሆን አለባቸው፤ ፕሬዝዳንቱም ይህንን በግልጽ አስታውቀዋል" ብለዋል።

  12. የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች የሚመቱ ከሆነ በእኩል ደረጃ የአጸፋ ጥቃት እንደሚፈጸም አስጠነቀቀ

    የኢራን ሚሳዔል ሲወነጨፍ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኢራን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ጥቃት የሚፈጸምባቸው ከሆነ፤ የእስራኤል የኃይል ማመንጫዎች እና በቀጣናው አገራት ለሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ኤሌክትሪክ የሚያቀርቡ ተቋማት ላይ የአጸፋ ጥቃት እንደሚያደርስ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስታወቀ።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው አብዮታዊ ዘቡ ያወጣው መግለጫ፤ በቀጣናው የሚገኙ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ተገልጾ የነበረውን ዛቻ አላካተተም። እነዚህ ማጣሪያዎች ለባሕረ ሰላጤው አገራት የሚጠጣ ውሃ በማቅረብ ረገድ ወሳኝ ናቸው።

    በወታደራዊ ኃይሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ የወጣው መግለጫ፤ “ውሸታም የሆኑት... የአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ የአብዮታዊ ዘቡ የውሃ ማጣሪያ ተቋማትን ለማጥቃት እና በቀጣናው ባሉ አገራት ህዝቦች ላይ ችግር ለመፍጠር አቅዷል በማለት ከስሰዋል" ብሏል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን በ48 ሰአታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለሁሉም መርከቦች "ሙሉ በሙሉ ክፍት" ካላደረገች የኢራን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የጥቃት ዒላማ እንደሚያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ለትራምፕ ማስጠንቀቂያ በሰጠው ምላሽ፤ “ለማንኛውም አይነት ዛቻ በእኩል ደረጃ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ ነን […] የኤሌክትሪክ ማመንጫን ከመታችሁ፣ እኛም የኤሌክትሪክ ማመንጫን እንመታለን" ብሏል።

  13. የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም መሪዎች የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት አስፈላጊነት ላይ መስማማታቸው ተገለጸ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት በኢራን ስለተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት አስፈላጊነት ተወያዩ።

    ከሦስት ሳምንት በፊት ጦርነት የተከፈተባት ኢራን በርካታ መርከቦችን ከሚያስተናግዱ የዓለም የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው ሆርሙዝን ወሽመጥን ዘግታለች። ይህንን ተከትሎ በአካባቢው ይደረግ የነበረው የመርከብ ጉዞ በ95 በመቶ ቀንሷል።

    ሁለቱ መሪዎች እሁድ ምሽት ባደረጉት የስልክ ንግግር “በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታ መወያየታቸውን” የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

    በተለይም “ለዓለም የመርከብ ጉዞን ለማስጀመር የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን አስፈላጊነት” እንደተነጋገሩ አስረድተዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም፤ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት የዓለም ኢነርጂ ገበያ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተስማምተዋል” ብለዋል።

    ስታርመር እና ትራምፕ “በቅርቡ በድጋሚ ለመነጋገር እንደተስማሙም” ተገልጿል።

  14. የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን “ዛቻ አንድነታችንን ያጠናክረዋል” አሉ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Iran's Presidential website/WANA/Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ የማትከፍት ከሆነ የኃይል ማመንጫዎቿን እንደሚያወድሙ መታዛቸውን ተከትሎ፤ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን “ዛቻ እና ሽብር የሚያጠናክሩት አንድነታችንን ብቻ ነው” አሉ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የተዘጋው ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ እንዲከፈት የሰጡት ማስጠንቀቂያ ከ24 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ቢቀረውም ከቴህራን በኩል መለሳለስ አልታየም። የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ አገሪቱ የኃይል ማመንጫዎች ጥቃት የሚፈጸምባቸው ከሆነ በቀጠናው የሚገኙ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች፣ የኢነርጂ እና የነዳጅ ዘይት ተቋማት እንደ “ሕጋዊ ዒላማዎች” ይቆጠራሉ ብለዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያንም በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “የሆርሙዝ ወሽመጥ መሬታችንን ከሚደፍሩት በስተቀር ለሁሉም ክፍት ነው” ብለዋል።

    የአሜሪካን ዛቻ “ኢራንን ከካርታው ላይ የማጥፋት ቅዥት” ሲሉ የጠሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ ማስፈራሪያ “ታሪክ ሰሪ ከሆነው የህዝብ ፈቃድ ተቃራኒ የሆነ ተስፋ መቁረጥን” ያሳያል ብለዋል። ፔዜሽኪያን አክለውም፤ “የማይረቡ ዛቻዎችን ጦር ሜዳ ላይ በጽናት እንመክታለን” በማለት ጽፈዋል።