ኢራን ከጠላት ጋር ተባብረዋል ያለቻቸውን ዜጎቿን ንብረት መውረስ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የኢራን መንግሥት “ከጠላት” ጋር ግንኙነት ያላቸው እና የእስላማዊ ሪፐብሊኩ ተቃዋሚዎች ናቸው ያላቸውን ሰዎች ንብረት መውረስ መጀመሩን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
መንግሥት ጠላት ካላቸው አገራት ጋር በማበር ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ እና መረጃን ያቀበሉ በውጭ የሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ንብረት ላይ ነው በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ የተላለፈው።
ዘገባዎች ስማቸው በግለጽ ያልተጠቀሱ ሁለት ሰዎች ንብረት በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ መወረሱን አመልክተዋል። የቀረበባቸው ክስም ከአገሪቱ ከወጡ በኋላ በውጭ አገራት ሆነው “ከጠላት ጋር በመተባበር ፀረ-ኢራን የሆኑ ተግባራትን መፈጸም” የሚል ነው።
ለኢራን መንግሥት እና የአብዮታዊው ዘብ ቅርብ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን ንብረታቸው የተወረሰ ሰዎችን ስም እና ምሥል በማውጣት የዘገቡ ሲሆን፣ እርምጃውንም አወድሰዋል።
ሌላኛው የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል “ሚዛን” እንደዘገበው “ከውጭ የስለላ ተቋማት ጋር በመገናኘት በኢራን ውስጥ የሽብር ተግባራት እንዲፈጸሙ” አድርጓል የተባለ ግለሰብ እና የዘመዶቹ ንብረት እንዲወረስ ተደርጓል።
የኢራን የሕግ እና የደኅንነት ተቋማት በተደጋጋሚ ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮችን መቅረጽ እና ለመገናኛ ብዙኃን አሳልፎ መስጠት “በአገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚፈጸም ወንጀል ማስረጃ” እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።






















